ዐፄ ቴዎድሮስና ደናቁርት አንባቢ ተችዎቻቸው!

ዐፄ ቴዎድሮስና ደናቁርት አንባቢ ተችዎቻቸው!

ዐፄ ቴዎድሮስና ደናቁርት አንባቢ ተችዎቻቸው! ክፍል አንድ

Amsalu Gebrekidan Argaw
 ዛሬ ሚያዚያ 6, 2008ዓ.ም. ዐፄ ቴዎድሮስ የዛሬ 148 ዓመት “ተማርኬ የሐበሻ ንጉሥ ተማረከ! ተብሎ እራሴን ሀገሬንና ሕዝቤን ከማዋርድ ስም ከምሰብር ሞት ይሻለኛል!” ብለው ለሚወዷት ሀገራቸውና ሕዝቧ ክብርና ኩራት ሲሉ ተማርከው በጠላት እጅ ከመውደቅ እራሳቸውን አጥፍተው የጀግና እረፍትን ቢያርፉ መርጠው እራሳቸውን ያጠፉበት የሚታሰብበት ዕለት ነው፡፡

“ዐፄ ቴዎድሮስ ለምን ይተቻሉ! ፈጽሞ መተቸት የለባቸው!” ለማለት አይደለም አነሣሴ፡፡ ነገር ግን ዐፄ ቴዎድሮስን መተቸቱ እንዲህ ቀላል ነገር መስሏቸው ደራሲ ነኝ፣ የታሪክ ጻሐፊ ነኝ፣ የታሪክ ተመራማሪ ወይም አጥኝ ነኝ፣ ምንትስ ነኝ እያሉ ዐፄ ቴዎድሮስን ለመተቸት እጅግ ጥልቅ መረዳትን ጥልቅ ዕይታንና አስተውሎትን እንደሚጠይቅ ጥቂትም እንኳ ሳይረዱ በማንም ላይ በለመደ አፋቸው በግልብ ዕይታቸው ዐፄ ቴዎድሮስን ጨካኝና አረመኔ እንደሆኑ አድርገው ማብጠልጠላቸው ስሕተት ከመሆኑም በላይ ትንሽ የሚያበሳጭም በመሆኑ እነኝህ ግለሰቦች መሳሳታቸውን ለማስገንዘብና ሙቶቹ እንደ ሙትነታቸው ቢያመልጡም በሕይዎት ላሉቱና ለቢጤዎቻቸው ዐፄ ቴዎድሮስ እንዴት እንደሚነበቡ እንደሚታዩና ሰው እንደመሆናቸውም ከትችት አያመልጡምና ሲተቹ እንዴት እንደሚተቹ መንገዱን ለማሳየት ነው የዚህ ጽሑፍ ዓላማ፡፡

ዐፄ ቴዎድሮስ በብዙ ምክንያቶች የባዕዳኑም የባንዶቹም ኢላማ ሆነው እንደቆዩ ይታወቃል፡፡ የባዕዳኑ ዓላማ የሆነው፡- ስማቸውን ለማጉደፍ አስበው በጻፏቸው መጻሕፍትም ሳይቀር አምልጧቸው በሰጧቸው ምስክርነቶች ሳይቀር ማረጋገጥ እንደሚቻለው ዐፄ ቴዎድሮስ በዓለም ከነበሩት ነገሥታት ለየት የሚያደርጓቸው የሚደነቁ በርካታ ነገሮች ስላሏቸው በብሔራዊ ጀግናነት ተወስደው ለሐበሻ ሕዝብ አርዓያና የወኔ ስንቅ እንዳይሆኑ በማሰብ፣ ሐበሻን ብሔራዊ ጀግና ማሳጣትን ዓላማ ባደረገ ተልእኮ ዐፄ ቴዎድሮስን በተመለከተ እውነትነት ያለውን ድርጊት አጋነው፣ ሐሰት የሆነውን ደግሞ ፈጥረው ስማቸውን ለማጥፋት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ቀላል ምሳሌ ለመስጠት፡- አብረው የነበሩትና በአካል የሚያውቋቸው ምዕራባዊያን ስለ ገጽታቸው ሲጽፉ ፍጹም ተቃራኒ የሆነ መረጃ ሰጥተዋል፡፡ ዱፍተን የተባለው ጸሐፊ “አፍንጫቸው የሮማዊያን ቅርጽ አለው” ሲል ዶክተር ብላንክ ደግሞ “አፍንጫቸው ደፍጣጣ” ነው ብሏል፡፡ ምዕራባዊያኑ ለራሳቸው ዓላማ ፈጥረው ከሚያወሩት ውጪ ሐሜቱንም የረኛ ወሬውንም ስለሚጽፉ በቋንቋ መግባባት አለመቻል ችግርም መስሎ የታያቸውንና ግምታቸውን ስለሚጽፉ መጻሕፍቶቻቸው በበርካታ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃዎች ለመሞላት ይገደዳሉ፡፡
የሀገር ውስጥ ባንዶች ደግሞ በግልብ ዕይታቸው ስለ ዐፄ ቴዎድሮስ ባላቸው የተሳሳተ ግንዛቤ በጥላቻ ተመርዘው የተቀሩት ደግሞ እራሳቸውን በጎሳና ጎጥ አጥረውና አደንቁረው እራሳቸውን ለምዕራባዊያኑ ቀጥረው የዐፄ ቴዎድሮስን ስም የሚያክፋፉ ስም የሚያጠፉ ናቸው፡፡ ሁቱንም አንድ የሚያደርጋቸው መገለጫ ግን ለዚህች ሀገር አንድነትና ሕልውና ዴንታ ቢሶች ምን ቢፈጠር የማይገዳቸው መሆናቸው ነው፡፡
ሁሉም የዐፄ ቴዎድሮስ ወቃሽ ከሳሾች የባንዳነት ሰብእና ያላቸው ከንቱ ዜጎች ናቸው፡፡ ከዚህች ሀገር እሴቶች በተጻራሪ ከቆሙ ኃይሎች ክብርና ሞገስ ሲፈልጉ፣ ለመወዳጀትና ፍርፋሪ ለመልቀም ሲያምራቸው የሚያደርጉት ነገር ቢኖር ዐፄ ቴዎድሮስን በአደባባይ በመዝለፍ በመዘርጠጥ በመንቀፍ የመሥዋዕት በግ አድርገው ማግኘት የፈለጉትን ነገር ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፡፡

እነኝህ ግለሰቦችና አካላት በዐፄ ቴዎድሮስ ላይ ከሚፈጽሙት ጥቃት አንድ ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልግ፡- ዐፄ ቴዎድሮስ ትውልዳቸው በሚገባ የሚታወቅ ሆኖ እያለ “ቅማንት ናቸው!” እያሉ አማራን በማበሳጨት በአማራ ላይ ሥነልቡናዊ ጥቃት ለማድረስ ይሞክራሉ፡፡ “ለመሆኑ ማን ቢወልድ ማን ነው ቅማንት የሚሆኑት?” ሲባሉ ግን ወሬያቸው ሐሰት እንደመሆኑ መጠን እስካሁን የሚሰጡት ምላሽ የላቸውም፡፡ ወደፊት ግን ምናልባት አዲስ የትውልድ ኃረግ ይፈጥሩላቸው ይሆናል፡፡

አለቃ ገሪማ ታፈረ የዐፄ ቴዎድሮስን ትውልድ አስተዳደጋቸውን በሰፊው አትተዋል፡፡ የዐፄ ቴዎድሮስ አባት “ደጃዝማች” ኃይሉ የደጃዝማች ወልደጊዮርጊስ ልጅ ናቸው፡፡ እናታቸው ወ/ሮ አትጠገብ ደግሞ አባታቸው ራስ ወዳጆ ናቸው፡፡ ራሳቸው ዐፄ ቴዎድሮስም ለንግሥት ቪክቶሪያ በ7355ዓ.ዓ. በዘመነ ሉቃስ ጥቅምት 20 በጻፉት ደብዳቤ ላይ “… እስተ ዛሬ ድረስ አባቶቸ ነገሥታቱ ፈጣሪያችነን ቢበድሉት መንግሥታቸውን ለጋላና ለቱርክ አሳልፎ ሰጥቶባቸው ነበረ፡፡ ዛሬ ግን እኔ ከተወለድሁ ፈጣሪየ ካመድ አንሥቶ ኃይል ሰጥቶ ባባቶቸ መንግሥት አቆመኝ፡፡ በእግዚአብሔር ኃይል ጋሎችን አስለቀቅኋቸው፡፡ ቱርኮች ግን ያባቴን መሬት ልቀቁ ብላቸው እምቢ ብለውኝ በእግዚአብሔር ኃይል ይኸው ልታገል ነኝ…”
በማለት የነገሥታት ዘር ያላቸው መሆናቸውን በዘመነ መሳፍንት ከነገሥታቱ ተነጥቆ የነበረውን የአባቶቻቸውን መንግሥትና ኃይል ማስመለሳቸውን ተናገሩ እንጅ ቅማንት ስለሆንኩ ከነገሥታቱ ዘር ውጭ ነኝ አላሉም፡፡ ቋረኛ መባላቸውም ቋራ የአባታቸው በኋላም የወንድማቸው የደጃች ክንፉ ኃይሉ ግዛት ስለሆነና እሳቸውም በልጅነታቸው ሔደው ከወንድማቸው ጋር ሆነው ያደጉበት ሀገር ስለሆነ እንጅ ተወልደው አድገውበት ወይም ቋራ ካሉ ቅማንቶች ስለሚወለዱ አይደለም፡፡ አባታቸውና ወንድማቸው ቋራ ግዛታቸው የሆነው የቋራ ቅማንት ተወላጅ ስለሆኑ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሌላኛው አጎታቸው ደጃዝማች ማሩ የደንቢያ ገዥ ነበሩና፡፡

ዐፄ ቴዎድሮስ ካህናቱን አንግሡኝ ብለው ከካህናቱ ጋራ ንግሥናው እንደሚገባቸው ሙግት በገጠሙ ጊዜ ካህናቱ “የነጋሢነት ዘር ካለዎት ይንገሩንና” ሲሏቸው ትውልዳቸውን በመዘርዘር ከማረጋገጥ ይልቅ አቡነ ሰላማ ባቀረቡት አጠቃላይ በሆነ የመከራከሪያ ነጥብ ለመርታት የመረጡት ዐፄ ቴዎድሮስ ትውልዳቸውን በሚዘረዝሩበት ወቅት ካህናቱ “አይ! አንዲህማ ከሆነ ከእርስዎ ይልቅ ለንጉሥነት የእነ እከሌ የእነ እከሌ ልጆች ይቀርባሉና እነሱ በሕይዎት እያሉ ንግሥናው ራቅ ላሉት ለእርስዎ አይገባም!” ብለው ሕጉን ሥርዓተ ነገሥቱን በመጥቀስ እንደሚረቷቸው ስለገባቸው እንጅ ቅማንት ስለሆኑና የነጋሢነት ትውልድ ስላልነበራቸው አይደለም ትውልዳቸውን በመዘርዘር ለመሞገት ያልፈለጉት፡፡ ከዐፄ ቴዎድሮስ እጅግ የበዛ የተጋፋጭነት ባሕርያቸው የተነሣ ንግሥናውን በጉልበት መውሰዳቸው ካልቀረ ቅማንት ቢሆኑ ኖሮ ቅማንትነታቸውን ሳይፈሩና ሳያፍሩ ይገልጹ ነበር እንጅ የሌላቸውን የነጋሢነት ዘር አለኝ ብለው በሐሰት ለመሞገት ባልፈለጉም ነበር፡፡

ጨካኝ አረመኔ ናቸው እየተባለ ወደሚሰነዘረው ትችት ስንመለስ እርግጥ ነው ዐፄ ቴዎድሮስ የጭካኔ እርምጃዎችን ወስደዋል፡፡ ይሄንን በማድረጋቸው ግን ተሳስተዋል ወይም ጨካኝ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ አከራካሪው ጉዳይ የጭካኔ ተግባር ፈጽመዋል አልፈጸሙም የሚለው አይደለም፡፡ ደናቁርት የዐፄ ቴዎድሮስ አንባቢ ተችዎቻቸው ያላዩትና ሊያዩት ሊረዱት ያልቻሉት ጉዳይ ዐፄ ቴዎድሮስ እነዚያን የጭካኔ ተግባሮች ሲፈጽሙ የጭካኔውን ተግባር እንዲፈጽሙ ያስገደዳቸው በቂና አሳማኝ ምክንያት ነበሯቸው ወይ? በቂና አሳማኝ ምክንያቶች ካላቸውስ እሳቸውን ጨካኝ ብሎ መፈረጅ ይቻላል ወይ? እነዚያን የጭካኔ እርምጃዎች ከመውሰድ ሌላ የተለየ አማራጭና የተለየ አማራጭ የተባለውን አማራጭ በመውሰድ ፍላጎታቸውን እንዲያሟሉ የሚያስችላቸው ጊዜና ሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ነበሯቸው ወይ? የሚሉ ወሳኝ ነጥቦችን ነው፡፡

ተራው ዜጋ በግልብ ስሜት ተነሥቶ እንዲህ ቢል ባልደነቀኝ፡፡ እኔ የተማርኩ ነኝ፣ እኔ ታሪክ አጥኚ ተመራማሪ ንኝ፣ እኔ ነገሮችን ጠልቄ መመልከት የምችል ባለ ንስር ዓይን ተቺ ሐያሲ ነኝ ወዘተረፈ. እያሉ እራሳቸውን አንቱ ብለው ለራሳቸው ከፍ ያለ ቦታ ከሚሰጡ ግለሰቦች ግን እንዲህ ዓይነት ግምት ውስጥ ሊጥላቸው፣ የብስለት የማስተዋል የመማራቸውን ጥልቀትና ጥብቀት ትዝብት ላይ ሊጥል የሚችልን ሐሳብ ትችትና ወቀሳ ሲሰነዝሩ ማየት እጅግ ያሳፍራል፡፡
ዐፄ ቴዎድሮስ ማን እንደሆኑ ለመረዳት ብሎም ለመፈረጅ ከላይ ደናቁርቱ አንባቢ ተችዎቻቸው ያላዩዋቸውንና ሊያዩዋቸው ያልቻሏቸውን ነጥቦች በዝርዝር ማየት ይኖርብናል፡፡ ስለሆነም እያንዳንዳቸውን እንመልከት፡-
ዐፄ ቴዎድሮስ እነዚያን የጭካኔ ተግባሮች ሲፈጽሙ የጭካኔውን ተግባር እንዲፈጽሙ ያስገደዳቸው በቂና አሳማኝ ምክንያት ነበሯቸው ወይ?፡-

ዐፄ ቴዎድሮስ ሲፈጥራቸው ከዓላማ ጋር የተፈጠሩ ሰው ነበሩ፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያ ንጉሥ ለመሆን የፈለጉት በሕዝብ ላይ ገዥ ሆነው በድሎት ተቀማጥለው ለመኖር እንዳልሆነ ሕይዎታቸው የሚያረጋግጠው ሀቅ ነው፡፡ ንጉሥ ከሆኑም በኋላ እስከ ሕልፈታቸው ድረስ ጫማ የሚባል አያውቁም ነበር፡፡ በጊዜው ጫማ ስላልነበረ አይደለም በዘመኑ እንኳን ንጉሡ መኳንንቱ ያለ ጫማ አይሔዱም ነበር፡፡ እሳቸው ግን ሕልማቸው ፍላጎታቸው ርእያቸው የግል ምቾትና ድሎት ሳይሆን ትልቅ የነበረችውንና የወደቀችውን ሀገራቸውን ከወደቀችበት አንሥተው ወደነበረ ክብሯ ታላቅነቷ በመመለስ ሥራ ሠርቶ የማለፍ ጽኑ ዓላማ ስለሆነ የነፍስ ጥሪያቸው ካልጠፋ ልብስ የነገሡ ለትና የሕልፈታቸው ዋዜማ ላይ ከለበሱት ሙሉ የንጉሥ የክብር ልብስ በስተቀር እራሳቸውን እንደንጉሥ ሳያከብሩ ከውጭ ሀገራት መንግሥታት በስጦታ የሚመጣላቸውን ልብስና ጫማ ሳይነኩት በአንዲት ጥብቆና በባዶ እግራቸው እንደኳተኑ “ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን!” የሚሏትን ታዋቂ መሪ ቃል አንግበው ሲጥሩ ሲግሩ የሚገነዘባቸው የሚረዳቸው አጥተው ያለፉ የምርጥና ድንቅ ሰብእና ባለቤት፣ ያለጊዜያቸው የተፈጠሩ ብርቅየ የአፍሪካ አብሪ ኮከብ ናቸው፡፡

የጫማ ምቾት ሳያምራቸው ሳያስፈልጋቸው ቀርቶ አይደለም፡፡ እንዲመቻቸው እንዲደላቸው ስላልፈለጉ እንጅ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ምቾትና ድሎት ከዓላማ ያዘናጋል ያሳንፋል ነው፡፡ ለስንፍናና ለመዘናጋት ብቸኛ ምክንያቶች ናቸው ባይባልም ትክክለኛ ዕይታ ነው፡፡ እንቅልፍ የማያስተኛ ዓላማ፣ አቅድ፣ ርእይ፣ ሕልም ይዘዋልና በምቾት ወይም በድሎት ምክንያት በሚመጣ መዘናጋትና ስንፍና ለቀቂቃም መስነፍ መዘናጋት ስለማይፈልጉ ይሄንን ለመከላከል በባዶ እግርና በአንዲት ጥብቆ እየኖሩ መፍጋትን መረጡ፡፡ የዓላማ ጽናትና ቁርጠኝነት ከዚህ ጀምሮ ይለካል ይመዘናል፡፡

ንጉሥ ሆነው ሳለ እራሳቸውን እንደ ንጉሥ ያለማኖራቸው ባሕርያቸው ከነገሥታቶቻችን ልዩውና ብቸኛው ሳያደርጋቸው አይቀርም፡፡ በእርግጥ የዐፄ ፋሲል ልጅ ዐፄ ዮሐንስ 2ኛም (ጻድቁ ዮሐንስ) በግብር የሚሰበሰበውን የድሀን ገንዘብ አልበላም ብለው ቀን ሲፈርዱ እየዋሉ (የመንግሥት ሥራን ሲሠሩ እየዋሉ) ሌት ሰሌን በመስፋት የሰፉትን ሰሌን እየሸጡ በሚያገኙት ገንዘብ ነበር እራሳቸውን ያስተዳድሩ የነበሩት፡፡ ይሁንና ዐፄ ቴዎድሮስ ይለያሉ፡፡ ከተራው ሕዝብ የተለየ ኑሮን መኖር አይፈለጉም፡፡ የተራውን ሕዝብ ኑሮ ተጋርተው መኖርን ነው የመረጡት፡፡

ዐፄ ቴዎድሮስ ገና ከጠዋቱ ከዓላማና ብርቅየ ርእይ ወይም ሕልምን የሰነቁ ለመሆናቸው አንድ ምሳሌ ብጠቅስ ይበቃል፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ሽፍታ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ የሚያስጠጋቸው ቢያጡ፣ በተነገረላቸው ትንቢት ምክንያት አሳዳጃቸው ቢበዛባቸው ነው የሸፈቱት እንጅ ዘርፎ ቀምቶ ከመብላት ሌላ ምንም ዓላማ እንደሌለው ተራ ሽፍታ ዘርፈው ቀምተው ለመብላት በማሰብ አልነበረም የሸፈቱት፡፡ ይሄንን ስል ዘርፈው ቀምተው አልበሉም ማለቴ አይደለም፡፡ የሚበሉት አልነበራቸውምና ማንን እንደሚዘርፉና እንደሚቀሙ በመለየት ዘርፈው ቀምተው በልተዋል፡፡

ከሽፍትነት ዘመናቸው የሚገርመውና የዓላማ ሰው ሆነው የተፈጠሩ እንደሆኑ የሚያሳየው፡- በቂ ኃይል የለኝም ብለው ሳይፈሩና ለነፍሳቸው ሳይሳሱ ከአራት መቶ የማይበልጡ ተዋጊዎችን ይዘው ወራሪውን ኃይል ለመመከት መድፍና ዘመናዊ የጦር መሣሪያ የታጠቀውን የቱርክንና የግብጽን ወራሪ ጦር ገዳሪፍና ስናር ድረስ ተጉዘው እየገጠሙ በተደጋጋሚ ድል እያደረጉ ያባርሩ ድንበራችንንም ያስከብሩ የነበሩ ጀግናና አስቀናቂ ሰው ናቸው፡፡

ያን ጊዜ ገና ሱዳን የምትባል ሀገር አልተፈጠረችም ነበር፡፡ ቅኝ ገዥዋ የሱዳን ፈጣሪ እንግሊዝ ገና አልገባችም ነበርና፡፡ እናም ያ ዐፄ ቴዎድሮስ የግብጽንና የቱርክን ወራሪ ኃይል ልቀቁ እያሉ በወረራ ሰፍረውበት ያሉት ስናር ገዳሪፍና አካባቢው በኢትዮጵያ ማዕከላዊው መንግሥት መዳከም ምክንያት ርቆ ተረስቶ ተዘንግቶ የነበረ መሬት ስለሆነና ይሄንን አጋጣሚ ተጠቅመው መወረራ ስለያዙት ነው ዐፄ ቴዎድሮስ ልቀቁ ቢሏቸው አልለቅ ስላሉ አስቀድሞ በሽፍትነት ዘመናቸው በኋላም በንጉሥነት ዘመናቸው ለማስለቀቅ ሲዋደቁ የነበሩት፡፡

በሽፍትነት ዘመናቸው ከግብጽና ቱርክ ጦር ጋር ባደረጓቸው ጦርነቶች የተሸነፉት በአንደኛው ብቻ ነው፡፡ ይሄም ሽንፈት ሀገሪቱ ምን ዓይነት ጠላት እንደተጋፈጠችና ያንዣበበውን አደጋ እንዲረዱ አስችሏቸው ዕድሜ ዘመናቸውን ያለ እንቅልፍ ተግተው እዲሠሩ አስገድዷቸዋል፡፡ ይሄንን ብርቱ ክንዳቸውን ገና በሽፍትነት ዘመናቸው በቂ ኃይል ሳይኖራቸው ደጋግሞ የቀመሰው ወራሪ ኃይል ዐፄ ቴዎድሮስ እያየሉ ሔደው ንጉሥ እንደሆኑ ሲያውቅ ሀገራችንን ወሮ ዓላማውን የማሳካት ፍላጎቱን እውን ማድረግ በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን ፈጽሞ ሊያስበው የማይችለው ነገር ሆኖበት የወረራ ዓላማውን

ለመፈጸም የዐፄ ቴዎድሮስ የንግሥና ዘመን እስኪፈጸም ተሰብስቦ ለመቀመጥ ተገዶ ነበር፡፡
እሳቸው እንዳረፉ ግን “ዕድሌ አሁን ነው!” ብሎ በመነሣት ግስግሶ በመምጣት ሀገር መያዝና መውጋት ገበሬውን መዝረፍ ማፈናቀል ጀመረ ይህ የግብጽና የቱርክ ወራሪ ኃይል ከዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ጋር 10 ጊዜያት በላይ ያህል ተዋግቷል፡፡ የሚገርመው ነገር በፊት በዐፄ ቴዎድሮስ ዘመን ዐፄ ቴዎድሮስ ካርቱምና ስናር ድረስ እየተጓዙ በግብጽና ቱርክ ወራሪ ኃይል ላይ ይወስዱት በነበረው እርምጃ ተነቃቅተውና ተበረታትተው ኃይል በማደራጀት ለነጻነታቸው ይታገሉ የነበሩትን መሐዲስቶች ወይም ደርቡሾች የቱርክና የግብጽ ጦር ከበው አስጨንቀው በያዙበትና የድል አፋፍ ላይ በደረሱበት ወቅት የተከበበው ወራሪ ኃይል የድረሱልኝ ጥሪ አሰማ፡፡

እንግሊዝ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛን ተከቦ ጭንቅ ላይ ያለውንና እኛን ለመውረር በመገስገስ ላይ የነበረውን ወራሪ ኃይል እንዲደርሱለት፤ ይሄንን ካደረጉ ግብጾቹ ምጽዋን እንደሚለቁላቸው ስላግባቧቸው በባንዳነት አድረው ለንግሥና ላበቋት እንግሊዝ “ምንጊዜም ቢሆን መታዘዝ አለብኝ!” ብለው የሚያስቡት ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ የቱርክና የግብጽ ወራሪ ጦር የወረራ ዓላማ ጣናንና አካባቢውን በመቆጣጠር የዐባይን የውኃ ዋስትና ማረጋገጥና የባሕር ጠረፋችንን መንጠቅ ወይም መቆጣጠር እንደሆነ እያወቁ እንዲሁም እንግሊዝ አድርጉ ያለችውን ቢያደርጉ ደርቡሾች የእኛ ጎረቤት እንደመሆናቸው እርምጃቸው በጉርብትናችን በወደፊት ግንኙነታችንና በአካባቢያዊ የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ጉዳይ ላይ ምን ሊፈጥር እንደሚችል ፈጽሞ መገመት ያልቻሉት የፖለቲካ (የእምነተ አሥተዳደር) ጥበብና እውቀት መሀይሙ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ጦር ልከው ለነጻነታቸው የሚዋጉትን ደርቡሾቹን ወይም መሐዲስቶቹን ወግተው የተከበበውን ወራሪ ኃይል በማስለቀቅ በሀገራችን በኩል አሻግረው ወደ ሀገራቸው ሸኟቸው፡፡ እንግሊዞች ግን ግብጾች ምጽዋን ይለቁላቹሀል እንዳሉት ምጽዋን አስለቅቀው ሳያስረክቡን ቀሩ፡፡

የግብጽና የቱርክ ወራሪ ኃይል የጋራ ጠላታችን በመሆኑ በተቻለን መጠንም ልንረዳቸው ይገባ ነበር፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ይሄንን ታሳቢ በማድረግ የሀገሬ ክፍል መሬቴ ነው ብለውም ስለሚያምኑ ነበር ገና በሽፍትነት ዘመናቸው ሳይቀር እዚያ ድረስ እየሔዱ ይዋጉ የነበሩት፡፡ በሽፍትነት ዘመናቸው እንድሪስ የተባለን የጎሳ መሪ አነቃቅነውና አሳምነው ሱዳን ወደ ውስጥ የዘጠኝ ቀን ጉዞ ያህል እየተጓዙ ዓረቦቹን ወግተውና ዘርፈው ይመለሱ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ዐፄ ቴዎድሮስ ካለፉ በኋላ በዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ዘመን ደርቡሾች ወይም መሐዲስቶች ኃይል ገንብተው ለራሳቸው ነጻነት ሲሉ ወራሪውን የግብጽና የቱርክ ጦር መውጋታቸው ለኛ በጣም ጠቃሚ ነበረ፡፡ ከእኛ ሳይደርስ እዚያው ይገታልን ነበርና፡፡ እነሱ እዚያው ከገቱት ካቆሙት እነሱን አልፎ እኛን ለመውረር ስለማይችል ደርቡሾቹ ይሄንን ማድረጋቸው እኛን በጣም ይጠቅም ነበር፡፡
ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ግን ይሄንን ያህል ብስለቱ አርቆ ማሰቡ ግራ ቀኝ ማገናዘቡ አልነበራቸውምና ደርቡሾቹ ወራሪውን የቱርክና የግብጽ ጦር እየወጉ ከበው ይዘው ድል ሊያደርጉ በተቃረቡበት ወቅት እንደዚያ ዓይነት አንጀት ቆራጭ ስሕተት ፈጸሙ፡፡ በዚህ እርምጃቸውም ዐፄ ቴዎድሮስ ሩቅ አስበው በዚያ ከሚኖሩ ወገኖች ጋር ፈጥረውት የነበረውን ወዳጅነት አፈረሱት፡፡ ወዳጅ የነበሩት ደርቡሾቹም ወደ ጠላትነት ተለወጡና የተፈጸመባቸውን ጥቃት በቀል በተደጋጋሚ እስከ ጎንደር ከተማ ድረስ እየገቡ ሀገራችንን አቃጠሉ ዘረፉ ሕዝብ ፈጁ፡፡ ዐፄ ተብየው የሞቱትም የተፈጸመባቸውን ግፍ ሊረሱት ካልቻሉትና የበቀል እርምጃ ጥቃት ደጋግመው ከወሰዱት ከነኝሁ ደርቡሾች ጋር አርቀው ማሰብ ባለመቻላቸው በፈጠሩት ስሕተት በገዛ እጃቸው ጠላት ፈጥረው ከነሱ ጋር ባደረጉት ውጊያ ነው፡፡

“ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ይህ ሊፈጠር እንደሚችል ከበፊቱም መገመት አያቅታቸውም ከድንቁርና ወይም ካለመብሰል አይደለም እርምጃውን የወሰዱት” ከተባለ እንግዲያውስ ደርቡሾች የበቀል እርምጃ እንውሰድ ቢሉ በቅርብ የሚያገኙት የጎንደርን ሕዝብ ስለሆነ የጎንደር ሕዝብ እንዲያልቅ ደርቡሾቹ የበቀል እርምጃውን በጎንደር ላይ እንዲወስዱ ያደረጉት ሰይጣናዊ ሸር ነው ሊሆን የሚችለው፡፡ ከሰብእናቸው የምንረዳውም ይሄንኑ ነውና፡፡ ጣሊያን ባሕረ ምድርን (ኤርትራን) ወሮ እየያዘ እሱን ማስወጣት ሲኖርባቸው አዲስ ጠላት ፈጥረው ሀገር አስፈጁ ጣሊያንን ካጠገባቸው አስቀምጠው ደርቡሽን እከላከላለሁ ሲሉ ፍጻሜያቸው ሆነ ለሀገራችንም ሁለት ጠንቀኛ ጠላቶች ተክለውልን ሞቱ፡፡ ይሄንን ቁርሾ በመያዝ ነው ሱዳኖች ሐበሻን ታሪካዊ ጠላት አድርገው ነክሰው የያዙንና ሀገራችንን ሰላምና ደኅንነት ለማሳጣት ታጥቀው መሥራት የጀመሩት፡፡ ጣሊያንም ምን እንደሠራን የምታውቁት ነው፡፡ ይሄ ሁሉ የሆነው በእሳቸው ሸረኛ ወይም የድንቁርና ሥራ ነው፡፡
እኝህ ሰው ዐፄ ቴዎድሮስ በሽፍትነት በነበሩበት ቦታ ቢሆኑ ኖሮ እንደ ዐፄ ቴዎድሮስ ሔደው ሊዋጉ ይቅርና በኋላ ላይ በዐፄ ቴዎድሮስ ወይም በሀገር ላይ ክህደት ሲፈጽሙ እንዳየናቸው የሀገርን ጥቅም አሳልፈው በመስጠት ጥቅሜ የሚሉትን ለማስጠበቅ ሲዶልቱ የሚገኙ በነበሩ፡፡ ምን ለማለት ፈልጌ ነው እንደ እኒህ ምናምንቴ ሁሉ ዐፄ ቴዎድሮስ ሥልጣን ተጠምተው ለሥልጣን የተዋደቁ አልነበሩም ዓላማ ርእይ ሕልም ነበራቸው፡፡
ዓላማቸው አንድም ሁለትም ነው፡፡ በዚያ የሽፍትነት ዘመናቸው ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ጠላት ምን ዓይነት ዘመናዊ መሣሪያና የጥፋት ዓላማ ታጥቆ ሊውጣት አሰፍስፎ እየጠበቀ እንዳለ በዓይናቸው በብረቱ ዓይተው አረጋግጠዋል፡፡ ይሄንን የጠላት ኃይል በራስ ደጃዝማች ወይም በመሳፍንት ተከፋፍሎ እርስ በእርሱ እየተፋጀ እየተላለቀ ባለና ለሥልጣኔ ባዕድ በሆነ ሕዝብ መመከትና የሀገሪቱን ነጻነት ህልውና መጠበቅ ፈጽሞ እንደማይቻል በሚገባ ገብቷቸዋል፡፡ ገብቷቸዋል ብቻ ሳይሆን ዕድሜ ዘመናቸውን ሙሉ ዕንቅልፍ ነስቷቸው ዘልቋል፡፡

ስለዚህ ይህ በመሳፍንት ተከፋፍሎ በጠላትነት እየተያየ እየተፈላለገ ይጫረስ የነበረ ሕዝብ አንድ ግንባር መፍጠር እንዳለበት የተረዱት ገና ከጠዋቱ ነበር፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ መሳፍንቱን ደምስሶ ኢትዮጵያን በማዕከላዊ ወይም በአሐዳዊ መንግሥት ስር እንድትተዳደር የማድረግ ዓላማን የሰነቁበት ሦስት ዐበይት ምክንያቶች ናቸው 1ኛው. በመሳፍንቱ ተከፋፍሎ እርስ በእርስ በመሀከላቸው ለመዝረፍና ለማስገበር በየጊዜው በሚነሣው ጦርነት የሚያልቀው የሕዝብ እልቂት ሀገርን እጅግ የሚጎዳ የሚያደቅ በመሆኑ ለዚህ ቀውስ መቋጫ ለማበጀት፡፡ 2ኛው. ከላይ እንደጠቆምኩት ኢትዮጵያ በማዕከላዊ መንግሥት ካልተዳደረችና ሕዝቡ በአንድ ካልተባበረ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት ካልገነባች በስተቀር አሰፍስፈው ያሉ ጠላቶቿን መመከት ነጻነቷንና የግዛት አንድነቷን መጠበቅ እንደማትችል ጠንቅቀው ስለተረዱ 3ኛው. “ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን!” የሚሉትን ሕልም ርእይ ለማሳካትና ኢትዮጵያን በቀደመው ክብሯ፣ ታላቅነቷ፣ ገናንነቷ፣ ግንባር ቀደም የሥልጣኔ ተሰላፊነቷ ላይ መልሶ ለማስቀመጥ የቀደመው የግዛት አካሏ በአሐዳዊ አስተዳደር መሆኑና ከተጋረጠበት የመበታተን አደጋ የግድ መውጣት ስላለበት ናቸው፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ግን ይሄ እሳቸው የተረዱትን አደጋ መሳፍንቱ የተረዱና ሊረዱም የሚፈልጉ አለመሆናቸው ነበር፡፡ በወቅቱ የነበሩት መሳፍንት ዐፄ ቴዎድሮስ የሚያስቡትን ማሰብ መገንዘብ መረዳት የማይችሉ፣ የሰማይና የመሬት ያህል የአስተሳሰብ የብስለት የማስተዋል አርቆ የማሰብ ልዩነትና እርቀት የነበራቸው በመሆኑና ፈቃደኞች ሆነው ባለመገኘታቸው ይህ የግድ መሳካት ያለበትን ርእይ፣ ሕልም፣ ዓላማ የቻሉትን ያህል አቅም ጉልበታቸው ከሚፈቅድላቸው በላይ ሔደው በኃይል መሳፍንቱን አስወግደው ኢትዮጵያን በአሐዳዊ አሥተዳደር ለማሥተዳደር ታጥቀው ቆርጠው ተነሡ፡፡

እኔ እጅግ የሚገርመኝና የሚደንቀኝ ነገር ቢኖር ዐፄ ቴዎድሮስ በነበራቸው የሰው ኃይል ከዚያ ሁሉ መሳፍንት ጋር መላ ሀገሪቱን እየተዘዋወሩ ተዋግተው “ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ ይሆንልኛል! ይሳካልኛል!” ብለው ማሰባቸውና መነሣታቸው ተነሥተውም ለአንዲት ጊዜም እንኳን ቢሆን ሳይሸነፉ ከእሳቸው እጅግ የበዛ ጦር ያላቸውን መሳፍንት ሁሉ እየደቆሱ እያነከቱ እየሰበሩ የተነሡበትን ዓላማ ማሳካታቸው ነው፡፡ እንደገና ቢፈርስባቸውም ቅሉ፡፡
እንዲህ ዓይነቱን እጅግ ከባድና ከፍተኛ መሥዋዕትነት የሚጠይቅ ርእይ ለማለም የግድ ዐፄ ቴዎድሮስን ሆኖ መፈጠር ይጠቅ ነበር፡፡ ስለ እውነት የተለየ ወደር የሌለው እጅግ የሚያስደንቅ ድፍረትና ጀግንነት ነበራቸው፡፡ የጎንደርን፣ የጎጃምን፣ የወሎን፣ የትግሬን፣ የሸዋን ግዛቶች ጠቅልለዋል በወለጋ በኩልም አሳልፈው ታች አሩሲ ድረስ ሠራዊት ልከው በማስፈር የማይገባቸውን ሕልምና ርእይ አልባ መሳፍንቱን እየቀጠቀጡ እየደቆሱ እየደመሰሱ አንድ አደረጓት፡፡

አንድ አደረኳት ብለው እፎይ ብለው ሳያርፉ ግን የገነቡት አንድነት እንደገና እየፈረሰ ሁለትና ሦስት ዙር ጦርነት መላ ሀገሪቱን እየተዘዋወሩ ከየመሳፍንቱ ጋር መዋጋት ግድ ነበረባቸው፡፡ ይህ የዐፄ ቴዎድሮስ ሀገርን በማዕከላዊ መንግሥት ስር እንድትተዳደር የማድረግ እጅግ አድካሚና ከፍተኛ መሥዋዕትነት የጠየቀ ተልእኮ እንኳንና ለሳቸው ላደረጉት ታሪካቸውን ለሚያነበው ራሱ ምን ያህል አታካችና እልህ አስጨራሽ እጅግ አድካሚ ተልእኮ እንደሆነ መገንዘብ የሚያቅት አይመስለኝም፡፡

የጎጃሙ ደጅ አዝማች ተድላ ጓሉ፣ የሸዋው መሸሻ ሰይፉ፣ የሰቆጣው ዋግ ሹም ገብረመድኅን፣ የትግሬው ደጃዝማች ንጉሤ፣ የሜጫና አገው ምድሩ ብሩ፣ የወሎው ዐመዴ በሽር፣ እዚያው ካጠገባቸውም የወንድማቸው ልጅ ጋረድ ክንፉ ከእነኝህ ከታላላቆቹ ሌላ በየጎጡና በየ አንባው እየሸፈተ እየከዳ ያስቸገራቸው ባላባትም ለቁጥር የሚያታክት ነው፡፡ እነኝህ ሁሉ ዐፄ ቴዎድሮስ ድል አድርገው ሀገሩን ከያዙ በኋላ እንቢ ብሎ በጠፋውና በሞተው ሹም ምትክ እዚያው ካገሩ “ያባቴ ነው ይገባኛል!” የሚለውንና ለማገልገል የፈቀደውን አደራ ጥለውባቸው የሾሟቸውና እንደገና የከዱ ሹማምንት ናቸው፡፡ የትግሬው ገዥ ደጃዝማች ንጉሤማ ጭራሽ “የባሕር ጠረፉንና አገሩን በስጦታ ልስጣቹህና ከቴዎድሮስ አድኑኝ!” እያሉ ፈረንሳይንና ጣሊያንን እጅግ ይማጸኑ ነበር፡፡

ዐፄ ቴዎድሮስን በጭካኔ የሚከሱ ግለሰቦች ከሚያነሡት ክስ አንዱ እነዚህ ከላይ በጠቀስናቸው መሳፍንት ላይ የጨከነ እርምጃ በመውሰዳቸው ነው፡፡ እሳቸው ግን በመሳፍንቱም ሆነ በሕዝቡ ላይ እንደየ ክህደታቸው ጀረጃና ክብደት መጠን እጅ ከመቁረጥ ወደ አንገት ወቁረጥና መስቀል ከዚህ በጅምላ ወደ ማቃጠል እየከበደ በሔደ እርምጃ የመቅጣታቸው ምክንያት አንደኛው፡-

ለከባዱና ለታላቁ ርእይ ማለትም ኢትዮጵያን በማዕከላዊ የመንግሥት አሥተዳደር የምትተዳደር አድርጎ የቀድሞ ታላቅነቷን በመመለስ ጠላቶቿን የምትፈራ፣ ጠላቶቿ የጋረጡባት ፈተና ሥጋት የተጫናት ደካማ ሀገር ሳትሆን ለጠላቶቿ የምታስፈራና በራስ መተማመንን የገነባች ከሥጋት ነጻ ሀገር ለማድረግ ለሚኪያሔደው ታላቅ ድካምና መሥዋዕትነት ለሚጠይቅ ትግል አደራ ታጭተው ከሾሟቸው በኋላ በዚህ ታላቅ ዓላማ ሕልም ላይ ክህደት ፈጽመው ታላቁን ሀገራዊ አደራ ጥለው ለተራ የግል ጥቅማቸውና ዝናቸው ሲሉ ስንት መሥዋዕትነት ከፍለው አንድ ያደረጓትን እንደገና በማፍረሳቸው ይሄንንም ክህደት ደጋግመው በመፈጸማቸው ይህ ክህደት ከቴዎድሮስ ትዕግስት በላይ በመሆኑና ዐፄ ቴዎድሮስ ደግሞ በምንም ተአምር ይህ ሕልም ዓላማ ሳይሳካ እንዲቀርና በተጋረጠው አደጋ ሀገር እንድትጠፋ ስለማይፈቅዱ ስለማይፈልጉ የመሳፍንቱ ክህደት ይኔንን ርእይ ሊያሰናክለው የሚችል መሆኑ ከባድ ሥጋት ላይ እየጣላቸው ስለመጣ መቀጣጫ ሊሆን በሚችል መልኩ በክፉና ሊረሳ በማይችል አገዳደል እነኚሁን በፊት አሸንፈዋቸው ማርከዋቸው የነበሩትን ነገር ግን ደግሞ ለታላቁ ርዕይ አስፈላጊ ስለሆኑ ሠራዊታቸውንና መሪዎቻቸውን ይቅርታ ምሕረት አድርገው የራሳቸውን የጦር መሪዎቻቸውንም ለራሳቸው ሾመውላቸው ለታላቁ ሀገራዊ ዓላማ እንዲረባረቡ አደራ ከተጣለባቸው በኋላ ያንን ያህል ርዕይ በመጣል ክህደት በፈጸሙት ላይ እርምጃውን በመውሰድ ከመንገዳቸው ላይ አስወግደው የኢትዮጵያን ትንሣኤ እውን ለማድረግ ጥረቱን መቀጠል ግድ ስለነበረባቸው ሲሆን፡፡

ሁለተኛው ደግሞ፡- መግደል ያው መግደል ሆኖ ሳለ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ መግደላቸው ጨካኝ ስለሆኑ ሳይሆን ሌላ ሰው መግደል ስለማይፈልጉ ነው፡፡ ሰዉ በዚህ መቀጣጫነት ተምሮ እንዳይሳሳትና እሱንም እንዲገድሉት እንዳያደርጋቸው እንዳያስገድዳቸው ስለሚፈልጉ ነበር መቀጣጫ ሊሆን ይችላል ባሉት መንገድ ሁሉ ይገሉ የነበረው፡፡
የሚገርመው ነገር ቢኖር ዐፄ ቴዎድሮስ ማርከውን አሸንፈውት ይቅርታና ምሕረት አድርገውለት ሾመው ካሠማሩት በኋላ እንደገና የከዳቸውን አንዳንዴ እንዲያውም ከሁለትና ሦስት ጊዜ በላይ የከዳቸውንና አልያዝ ብሎ ከአገር አገር እየሸሸ እስከ ሰባት ጊዜ እንዲዘምቱበት እያደረገ ያደከማቸውን ሠራዊትና ሹም፣ በተደጋጋሚ ሽፍታንና ክህደት የፈጸሙትን ሹሞች እየደበቀና የእቀለበ ተባባሪ ሆኖ ያስቸገራቸውን ሕዝብ ለምሳሌ፡-

ድብረ ታቦር ከርብ ጀምሮ እስከ ፍርቃ በር ወታደራቸውን አሰማርተው የተገኘውን ሁሉ 7700 ሰዎችን ሰብስበው በየቤቱ እያጎሩ የታጎሩበትን ቤት በማቃጠል ፈጅተዋል፡፡ ሰው ተቃጥሎ ሳያልቅ ጊዜው ስለመሸ ተራፊው ራቁታቸውን ሜዳ ላይ እየተጠበቁ እንዲያድሩ አዘዙ ሌሊቱን ዝናብ ሲዘንብ ስላደረ ሕፃናትና እመጫቶች ሳይቀሩ በዝናብ ሲደበደቡ አደሩ፡፡ በማግስቱ ሊቃጠሉ ወደሚታጎሩበት ቤት ሰዉ እየተከፈለ ሲገባ አንድ የአምስት ዓመት ሕፃን እናቱን እየጎተተ “ነይ እንደትናንቱ ዝናብ እንዳይመታን ቶሎ ከቤት እንግባ” እያለ ሲያለቅስ እናቱም ስታለቅስ ቴዎድሮስ ዓይተው “ለምን ያለቅሳሉ?” ብለው ጠየቁ ልጁ የተናገረውን ቢነግሯቸው “ፈጣሪየ! ምነው እንዲህ ታደርገኛለህ? ወይ እኔን ቶሎ ግደልና

ፍጥረትህ ይረፍ!” ብለው አልቅሰው ሊቃጠሉ የነበሩትን ሁሉ ማሯቸው፣
ዶክተር ብላንክ ደግሞ እንዲህ ብሎ ጽፏል ጎንደር ከቤተመንግሥቶቹ እየተደበቁ የሚያስቸግሯቸውን ሽፍቶች ለማጥፋት ሲጓዙ አድረው ወገግ ሲል ከከተማው ተራራ ስር ደረሱ ምንም እንኳን በድንገት ለመድረስ አቅደው የመጡ ቢሆንም የጎንደር ነዋሪ ግን ወሬውን ቀድሞ ሰምቶ ስለነበር በመጨነቅና በመሸበር ሴቶች ወጥተው በእልልታና በደስታ ሲቀበሏቸው በፋሲል ግንብ ውስጥ ተሰግስጎ የነበረው ሽፍታ ሸሽቶ ከጎንደር ወጣ፡፡ በየቤቱ በየቤተክርስቲያኑ ሁሉም ቦታ ቢፈተሸ ሊገኙ አልቻሉም እልል እያሉ ምልክት ሰጥተው እንዲሸሹ ያደረጓቸውን ሴቶች ጨምሮ ቤተመንግሥቱንም አብያተክርስቲያናቱንም ቀሳውስቱንም አቃጠሉ ብሏል፡፡ እናም እንዲህ እንዲህ ያለ ተስፋ የሚያስቆርጣቸው ምክንያት ካላገኙና ስሕተቱ ድጋሜ እንዳይከሰት ለማድረግ ከማሰብ በስተቀር ማንንም በክፉ አሟሟት ለመቅጣት ፈልገውም አስበውም አድርገውም አያውቁም፡፡

አንዴ አንዲት ሴትዮ አርባ ክንድ መቀነት ፈትላ አሠርታ ለዐፄ ቴዎድሮስ ስጦታ ሰጠች፡፡ ቴዎድሮስም ስጦታውን ተቀብለው “እንዴት በአርባ ክንድ መቀነት ወሰንሽኝ? እንደ ተራ ሰው ቆጥረሽኝ ነው?” ቢሏት “አይደለም ጃንሆይ! ድሀ ብሆን ነው እንጅ ለእርስዎ መቶ ክንድም አይበቃም!” አለቻቸው በቅንነቷ ተደስተው ሸልመው ሰደዷት፡፡
ይሄንን የሰማች አንዲት ሴት “መልከ ጥፉዋን ያንን ያህል የሸለሙ እኔንማ ቁንጅናየን ሲያዩ የበለጠ ይሸልሙኛል” ብላ ከቴዎድሮስ ዘንድ ቀርባ እጅ ነሳች እሳቸውም “ሙያሽ ምንድን ነው እቱ?” ብለው ጠየቋት፡፡ ሴትዮዋም “ሞያ ማለት ምንድን ነው?” ብላ መልሳ ጠየቀቻቸው፡፡ እሳቸውም “በእጆችሽ ምን ትሠሪባቸዋለሽ?” ብለው መልሰው ጠየቋት፡፡ እሷም “በእጀ እማ እበላበታለው የከተማ ቅሬ (ሴተኛ አዳሪ) ነኝ እንጅ ሥራ የለኝም” አለች፡፡ እሳቸውም “እግዚአብሔር ሁለት እጆች የፈጠረልሽ እንድትሠሪባቸው ነበር ለመብል ብቻ ከሆነ አንድ እጅ ይበቃሻል!” ብላው አንድ እጇን አስቆረጧት፡፡

ለደናቁርቱ የዐፄ ቴዎድሮስ አብባቢዎችና ተችዎች ይሄ ተራ የጭካኔ ተግባር ነው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ከተራ ጨካኝነት ሳይሆን ከብልህ ጥበበኛ መሪነት አኳያ ይሄንን እንዳደረጉት የምንረዳው የዚህች ሴት እጅ መቆረጥ ያመጣውን ለውጥ ስንመለከት ነው፡፡ ይህ ድርጊት እንደተሰማ ዐፄ ቴዎድሮስ “ሥራ ሥሩ! ሞያ ይኑራቹህ!” እያሉ ሽህ ጊዜ ነጋሪት እያስጎሰሙ አዋጅ ቢያስነግሩ ሊመጣ የማይችል ለውጥ በሕዝቡ ዘንድ ተፈጥሯል፡፡ ከዚያ በኋላ ቢያንስ የአንድ ሞያ ባለቤት ያልሆነ ሰው ከሕዝቡ ውስጥ አልነበረም፡፡ የዘመኑ ዘፋኞችም፡-
“ማረስ ይሻላል መገበር፤
እጅ እግር ይዞ ለመኖር፡፡
አላርስም ያሉ አልነግድ፤
ተመለመሉ እንደ ግንድ”

እየተባለ በሕዝቡ ዘንድ ይዘፈን ነበር፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ የሴትዮዋን እጅ የቆረጡበት ምክንያትና ዓላማ ይሄንን ለውጥ ለማምጣት ነበር፡፡ ሴትዮዋ አልተጎዳችም ወይ? ከሆነ ጥያቄው ምንም ጥርጥር የለውም ተጎድታለች፡፡ ነገር ግን መሪ ሲኮን ከተለምዷዊው አስተሳሰብ በተለየ መንገድ ማሰብና ቆራጥ የውሳኔ ሰው መሆን የግድ ይላል፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ እንዲህ ናቸው፡፡ በአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚያስቡ ሰው አይደሉም፡፡ ለሚያደርጉት አንድ ነገር እሱን የሚመዝኑበት አንድ ሽህ አቅጣጫ አላቸው፡፡ እኛ የምናውቀው አንዱንና ተለምዷዊውን ብቻ ስለሆነ የተለየ ነገር ስናይ እንኳን ለወዲያው ማለትም በዚያ ዘመን ለነበሩ ሰዎች በዚህ ዘመን ላለነውም አይገባንም፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ ግን እንዲህ ነው የሚነበቡትና ሊነበቡ የሚገባው፡፡

ቤተክርስቲያን የማቃጠላቸውን ነገር ማየት ያለብን ከዚሁ አንጻር ነው፡፡ በየሔዱበት ሀገር ሁሉ ቤተክርስቲያን ሲያዩ ከፈረሳቸው ወርደው ሳይሳለሙ የማያልፉ ሰው፣ ዳዊት ሳይደግሙ የማይውሉና ለቤተክርስቲያን ህልውና ተጨናቂ ሰው፣ ቤተክርስቲያን በማነጽም ቤተክርስቲያንን የሚያስፋፉ ሰው እንደ አሕዛብ አረማዊያን ቤተክርስቲያንን ሲያቃጥሉ እጅግ ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት ነው እሳቸውን መረዳት እጅግ አስቸጋሪ ነገር ነው፡፡ አስተሳሰባቸው እኛ እንደምናስበው ተለምዷዊ አይደለም፡፡

አንድን ቤተክርስቲያን ሲያቃጥሉ እግዚአብሔርን እንዳገለገሉት ነው እንጅ የሚያምኑት የበደሉት አድርገው ቅንጣት ታክል አይጨነቁም፡፡ ቤተክርስቲያን ሲያቃጥሉ በዚያ ቤተክርስቲያን ሐሳዊያን ደብተሮችና ካህናት የሞሉበት የተቆጣጠሩትና መጠቀሚያ ያደረጉት ከሆነ “የሐሳዊያን ደብተሮችና ካህናትን የተንኮል ሥራ ማለትም አስማት ሟርትና መተትን እሳት ይሽረዋል!” ስለሚባል ከነ ሐሳዊያን ደብተሮቹና ካህናቱ ጋራ ያቃጥሉታል፡፡ ነገሮችን ከብዙ አቅጣጫ ለሚያዩት ለእሳቸው ይሄ ድርጊት ቀላል ነገር ነው፡፡ ለእኛ ግን ከባድ ነው፡፡ የዕይታ ልዩነት ነው የአስተሳሰብ ልዩነታችንን ያመጣው፡፡

ይሁንና ይሄኛው ዶክተር ብላንክ የጻፈው ነገር ግን ጥቂት እውነት ይዞ ያንን እጅግ አጋኖ ያወራው ወሬ ነው፡፡ ምክንያቱም በተአምራት የተረፉ ቢኖሩም የጎንደር አብያተክርስቲያናትና አብያተመንግሥታትን በሙሉ ሊያቃጥል የሞከረው ደርቡሽ ነው፡፡ ከደርቡሽ በፊት ግን ዐፄ ቴዎድሮስ ያቃጠሏቸው ሦስት አራት አብያተክርስቲያናት ቢኖሩም የተቀሩት ግን በጥንታዊ ይዞታቸው ተጠብቀው እንደነበሩ ከሌሎች የታሪክና የቤተክርስቲያን ሰነዶች ማረጋገጥ ይቻላልና፡፡
አንዳንዴ ሳስበው ዛሬም ቢሆን ቤተክርስቲያን እግዚአብሔርን ሳይሆን ሆዱን ጥቅሙን ብሎ በገባው እግዚአብሔርን ጨርሶ በማያውቀው፣ በሐሳዊያን ተብታቢ ደብተሮችና ካህናት፣ በከሀዲያን መናፍቃን፣ በአስመሳይ ምእመናን የተሞላችና እየታወከች ያለችበት ዘመን በመሆኑ ይሄንን ሁሉ ጠንቅና አዋኪ ሰብስቦ እያጎረ የሚያቃጥለው ያስፈልገው ነበር እላለሁ፡፡ ንስሐ ገብቶ የማይመለስና የማይድን ከሆነ መኖሩ ምን ይጠቅማል? የወይኑ ተክል ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስስ “ስለምን መሬቱን ታጎሳቁላለች ቁረጣት!” ሉቃ. 13፤1-9 አልነበረም ያለው? በወይን ጠባቂው (በመልአኩ) ምልጃ የተሰጠንን ተጨማሪ ዕድል የንስሐ ዕድሜ ካልተጠቀምንበትና መሬቱን ማጎሳቆል ብቻ ከሆነ ትርፋችን መኖራችን ምን ይጠቅማል?

በእርግጥ ቤተክርስቲያን መፈተን ጸጋዋ ነው ያለፈተናም ልትኖር አትችልም፡፡ ሰይጣን በዚህች ምድር እስካለ ጊዜ ድረስ ሳይደክምና ሳያርፍ የሚሠራው ሥራ ይሄ ብቻ ነውና በተለያዩ ፈተናዎች ቤተክርስቲያን መፈተኗ አይቀርም፡፡ ከፈተና ነጻ መሆን አይቻልም፡፡ ይሁንና ግን እውነተኞቹ ካህናት ደብተሮችና ምእመናን ፈተና አይቀርምና ብለው ቤተክርስቲያን ስትታወክ በዝምታ መመልከት የለባቸውም፡፡ በዝምታ መመልከት ተባባሪነትና የተጣለብንን አምላካዊ ግዴታ አለመወጣትና በደል ነውና፡፡

ወደ ቀደመው ነገራችን ስንመለስ እናም ምኑንም ባላወቅነውና ባልገባን ጉዳይ ላይ ዐፄ ቴዎድሮስ “ትክክል አይደሉም!” ብሎ በእሳቸው ላይ ለመፍረድ በእሳቸው ቦታ ላይ ተቀምጦ በዚያ ሰዓት ከሥልጣኔ ወደ ኋላ መቅረታችን፣ በዚህ ምክንያት ሥልጣኔ በያዙት ባዕዳን ልንበላ ልንሰለቀጥ መሆናችንን በሚገባ የተረዳና ጉዳዩ እጅግ ያሳሰበው ያስጨነቀው እረፍት የነሣው መሆንን ይጠይቃል፡፡ “እውር ነኝ እባካቹህ ዓይኔን አብሩልኝ!” ሊል በሚልበት ደረጃ ላይ ሆኖ ሥልጣኔን የተጠማ መሆንን ይጠይቃል፡፡ በሀገርና በወገን ፍቅር ተንጨርጭሮ መቃጠልን፣ መነሁለልን ይጠይቃል፡፡

ርእዩ ሳይሳካ ቢቀር ይህች ሀገር ሊገጥማት የሚችለው ፈተና ያስጨነቀው እረፍት የነሳው መሆንን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ መሳፍንት ይህ ርእይ እንዳይሳካ ምን ያህል እንቅፋት እንደሆኑና እንዳወኩ ሀገሪቱ ለጅብ እንድትሰጥ እየሠሩ መሆኑን መረዳትን ይጠይቃል፡፡ በነገራችን ላይ ዐፄ ቴዎድሮስ ይህችን ሀገር በኪነ ብጀታ (በቴክኖሎጂ) እና በሥልጣኔ ለማሳደግ የነበራቸው እጅግ ከፍተኛ ፍላጎትና ጥረት እራሳቸውንም አመራምሮ አፈላስፏቸው የተዋጣላቸው ሜካኒካል ኢንጂኒየር (የአበጃጀት መሐንዲስ) አድርጓቸው እንደነበር ታውቃላቹህ? በከባድ መንኮራኩር እና በእንፋሎት ኃይል የሚሠራ ጀልባ ፈልስፈው ነበር ዐፄ ቴዎድሮስ፡፡

እናም እንደሳቸው ይሄንን ያህል ያልተጨነኩ ያልተጠበብኩ እሳቸውን ያሳሰቧቸው እንቅልፍ የተሷቸው ነገሮች ያልገባኝና ያላስጨነቀኝ ሆኘ “ዐፄ ቴዎድሮስ እንዲህ እንዲህ በማድረጋቸው ጨካኝና አረመኔ ናቸው!” ብየ ብተች ድንቁርናየን እያስመሰከርኩ ካልሆነ በስተቀር አዋቂነቴን ሊያሳይ አይችልም፡፡

ደግሜም እላለሁ የዚህ ዘመን ሰው የሆንን የዚያ ዘመንን ሰው ዐፄ ቴዎድሮስን መረዳት ባለመቻሉና እጅግ በማድከሙ ሊፈርድበት አይገባም፡፡ ከ 148 ዓመታት በኋላም ሳንበስል እንዲያውም ጭራሽ ይባስ ደንቁረን በዚያ ዘመን ያልነበረን አዳዲስ ችግር አምጥተን በዘር በሃይማኖት እየተከፋፈልን በዚያን ያህል መሥዋዕትነት የተሰበሰበችውን ሀገር ለመበተን በመታገል የባሰ ችግር ውስጥ ለመግባት አሰፍስፈን የባሰውን ነገር እያደረገ ነውና፡፡

እናም እየደነቆርን ሔድን እንጅ እየሠለጠንን አልሔድንምና የዚያ ዘመን ሰዎች ሊያስወቅሳቸው የሚችል ድንቁርናና ስሕተት ቢፈጽሙም እኛ ደግሞ የባሰውን እያደረግን ነውና በእነሱ ላይ ምንም ለማለት አፍ የለንም፡፡ አግባብነት በሌለውና በደነቆረ ዕይታ በታወሩ መሳፍንት ለግል ጥቅማቸው እርስ በእርሱ በመጨፋጨፍ እየተላለቀ ያለቀው ሕዝብ ሁሉ ለልማት ውሎ ተገልግለንበት ቢሆን ኖሮ ዛሬ ይህች ሀገር የት በደረሰች ነበር፡፡
ዐፄ ቴዎድሮስ ለወሰዷቸው እርምጃዎች በቂና አሳማኝ ምክንያቶች ካላቸው እሳቸውን ጨካኝ አረመኔ ብሎ መፈረጅ ይቻላል ወይ?፡-

ኧረ መልሱ እንዴት ሆኖ? የሚለው ነው፡፡ ሲጀመር ጨካኝ ማለት ያለምንም አዎንታዊና ፍትሐዊ ምክንያትና ዓላማ አውሬአዊ ባሕርይውን ለማርካት ሲል ብቻ ያለምንም ርሕራሔና ጸጸት እንደ አዶልፍ ሂትለር እንደ ቦኒቶ ሞሶሎኒ በሀገራችንም እንደ ዮዲት ጉዲት፣ ግራኝ አሕመድ፣ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ መለስ ዜናዊ የማሳሰሉት ለዕኩይና ኢፍትሐዊ ጥቅምና ዓላማው ዘግናኝ በሆነ መንገድ በግልጽም ይሁን በስውር የሰው ልጆችን የሚያርድ የሚገድል የሚፈጅ ማለት እንጅ ሀገርንና ሕዝብን ከከፋ አደጋና ጥቃት ለመታደግ አማራጭ ጠፍቶ እንዲነቃ እንዲተባበር ለማድረግ ሲባል መቁረጥና ማቃጠል አይደለም ጨካኝነት፡፡

አረመኔ ማለት ደግሞ ከላይ እንደጠቀስኳቸው ግለሰቦች ያለ “በእግዚአብሔር የማያምን የሞራል (የቅስም) ሕግ የማይገዛው” ማለት በመሆኑ ዐፄ ቴዎድሮስ ክርስቲያንና ለሃይማኖታቸው ተቆርቋሪ ለሞራል (ለቅስም) ሕግጋት ደግሞ ተንገብጋቢ በመሆናቸው ይሄም በደናቁርቱ የተለጠፈባቸው ስም ጨርሶ የማይገባ ነው፡፡

ዐፄ ቴዎድሮስ ጨካኝ ሊባሉ ይችሉ የነበረው ዝም ብለው ያገኙትን ሁሉ ያለ ምክንያት ያለ አዎንታዊ ዓላማ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ በአሰቃቂ አገዳደል እየገደሉ በአገዳደላቸው በመዝናናት እራሳቸውን የሚያስደስቱ ሰው ቢሆኑ ነበር፡፡ እሳቸው ግን ከዚህ ዓይነት ሰብእና እጅግ የራቁ መሆናቸውን ከታሪካቸው የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ ደጋግመው ክህደት በመፈጸማቸው እርምጃውን መውሰድ ባለባቸው ወገኖች ላይ እርምጃውን ሲወስዱ ከሐዘናቸው የተነሣ እንባቸውን መቆጣጠር እያቃታቸው በእንባ እየታጠቡ በሕይዎት መኖራቸውን በመጥላት ነበር እነኛን እርምጃዎች የሚወስዱት፡፡
የሚሰጡት የሚመጸውቱት ባይኖራቸው የለበሱትን አውልቀውና ከሰው ተበድረው የሚሰጡ የሚመጸውቱ መሆናቸው፣ ባለቤታቸው ተዋበች ስታርፍባቸው አልሞተችም ትነሣለች ብለው ሁለት ወር ሙሉ አላስቀብርም ማለታቸው፣ ለድሆች አቤቱታ ቅድሚያ የሚሰጡ መሆናቸው፣ የባሪያ ንግድ እንዲቆም ከማወጃቸውም በላይ የተገዙ ባሮችን ዋጋ እየከፈሉ ነጻ እንዲለቀቁና ጥበብ እንዲማሩ ማድረጋቸው ሰብአዊነት የተሞሉ መሆናቸውን ነው በሚገባ የሚያሳየው፡፡

አንዴ ወሎ በዘመቱ ጊዜ ጮቄ ጨሜ በተባለው ቦታ ሰፍረው ሳለ በአውሮፓ እንደሚዘንበው ያለ በናኝ በረዶ (ስኖው) ዘነበ፡፡ በሰው በእንስሳቱ ላይ ሁሉ እንደ ጭቃ እየተመረገ ተቀመጠ፡፡ በበናኝ በረዶው ምክንያት በርካታ አቅመ ቢሶችና ሕመምተኞች ሞቱ፡፡ መጠጊያ መጠለያ የሌለው ሕዝብ በበረዶው መመታቱን ያዩት ዐፄ ቴዎድሮስ “ሕዝቡ እንደዚያ ያለ ስቃይ ውስጥ ሆኖ እኔ ከድንኳን ውስጥ ተጠልየ አልቀመጥም!” ብለው ከደጅ ወጥተው በናኝ በረዶው ከሚወርድበት ቦታ ላይ ቆሙ፡፡ ሠራዊቱንም “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ! እንበል!” ብለው አዘው እግዚኦታው ሲጀመር በረዶው ቆሞ ፀሐይ ወጣ፡፡

እንግዲህ ዐፄ ቴዎድሮስ ይሄንን ያህል ኃላፊነት የሚሰማቸው፣ የሰውን ችግር የሚጋሩ፣ የሰው ችግር የሚያስጨንቃቸው “ንጉሥ ስለሆንኩ ከድሀው ዜጋ የተለየ ልብስ ሊኖረኝ አይገባም! ጫማም አለደርግም!” ብለው የድሀውን ኑሮ እየኖሩ በቀን አንዴ ብቻ እየተመገቡ ሀገር ለማቅናት ለሀገርና ለሕዝብ ማሰብን ለማስተማር ሲማስኑ ኖረው አንዲት ቀን እፎይ ሳይሉ እንደማሰኑ የተሠውትን ዕንቁ ጨካኝ አረመኔ ብሎ ማለት ምን ይሉታል? ይሄ አባባል ማሰብ መቻልን ያሳያል? እንዲህ ዓይነት ቅን ሰብእና እንኳንና ከንጉሥ ከሃይማኖት መሪም እንኳን ፈጽሞ ማግኘት አይቻልም ባይባልም ከስንት አንድ ሊገኝ ቢችል ነው፡፡ እያየናቸው እኮ ነው አይደለም እንዴ!

እናም እኛ ጥቂቶች ያልገባን ወገኖች ባያድለን ልቡና ማስተዋል ባይኖረን ነው እንጅ ዐፄ ቴዎድሮስ የምንጠላቸው ልንተቻቸው የምንደፍራቸው ሳይሆኑ እጅግ የምንኮራባቸው ብሔራዊ ጀግናችን ናቸው፡፡ ይሄኔ ዐፄ ቴዎድሮስ በምዕራቡ ዓለም ኖረው ያለፉ ሰው ቢሆኑ ኖሮ ምዕራባዊያኑ መላውን ዓለም “ካላመለካቹህልን” እያሉ መቆሚያ መቀመጫ ባሳጡት፣ ለዜጎቻቸው አርአያ ምሳሌ አድርገው በማስጠናት የወኔ፣ የሀገር ፍቅር፣ የጀግንነት፣ የቆራጥነት ስንቅና ምንጭ አድርገው ብዙ ሲጠቀሙባቸው ባየን ነበር፡፡ እኛ ግን ዕንቋችንን ስላላወቅን የጥፋት ኃይሎችም እንዳናውቃቸውና እንዳይገቡን በርትተው እየሠሩ ስለሆነ ልንጠቀምባቸው አልቻልንም፡፡
ቀጣዩን ክፍል ቀጥሎ ከተለጠፈው ይመልከቱ!