ህገ መንግስታዊ ትንታኔ እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ:- የአማራ ህዝብ እንጁን ወደ መሳሪያ ለምን ሰደደ?

ሸንቁጥ አየለ

ህገ መንግስታዊ ትንታኔ እንደ ቅድመ ማስጠንቀቂያ:- የአማራ ህዝብ እንጁን ወደ መሳሪያ ለምን ሰደደ?
የአማራ ህዝብ እንጁን ወደ መሳሪያ ለምን ሰደደ?

ይሄ ህገ መንግስታዊ ትንታኔ ከአምስት አመት ብኋላም እንኳን አሁንም ለወያኔ መንግስት ግሩም የቅድመ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ነዉ:: ይሄን ህገ መንግስታዊ ትንታኔ የጻፍኩት ከዛሬ አምስት አመት በፊት ነበር::ጉራፋርዳ በመከራ እሚጠበሱት ወገኖቼ መሃከል ቁጭ ብዬ መጻፍ ጀምሬ አዲስ አበባ ላይ ጨርሼ ለበርካታ የግል ሚዲያዎቼ በተኜዉ ነበር:: ጽሁፉን ያወጣዉ ግን በተመስገን ደሳለኝ የሚመራዉ ፍትህ ጋዜጣ ብቻ ነበር::

በዚህ ህገ መንግስታዊ ትንታኔ ዉስጥ አሁን ሀገሪቱ ካላት 106 ህገመንግስታዊ አንቀጾች ዉስጥ ከ50 በላይ አንቀጾች በአንድ ጊዜ ሲጣሱ እና ሀገመንግስቱም ሲፈርስ በግልጽ ይስተዋላል:: ይሄ ህገመንግስታዊ አንቀጽ ከተጻፈ ከአራት አመት ብኋላ የአማራ ህዝብ ” እግዚአብሄር እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል..” የሚለዉን መዝሙር ጀምሯል::

ግን ይሄ ጅማሮዉ ነዉ:: በጣም እጅግ ጥቂት ጅማሮ:: እናም የዚህ ህገ መንግስታዊ ትንታኔ ቅድመ ማስጠንቀቂያነት ገና ጅማሮዉ ነዉ ፍንትዉ ያለዉ:: የሆነዉ ሆኖ የአማራ ህዝብ እጁን ለምን ወደ መሳሪያ ሰደደ? የሚለዉን ጥያቄ ከመመለሱም በላይ አሁንም ለወያኔ መንግስት የሚበጅ ግሩም ቅድመ ማስጠንቀቂያ የያዘ መልዕክት ነዉ::

ወያኔ ግን ሰይጣናዊ የሆነዉን ጸረ አማራ ስራዉን አሁንም ቀጥሏል:: በእስር ቤት ያሉ አማሮችን አይናቸዉን ያጠፋል:: ጆሯቸዉን ያበላሻል:: እጅና እግራቸዉን ከጥቅም ዉጭ ያደርጋል:: መራቢያ የሰዉነት ክፍላቸዉን ከጥቅም ዉጭ እንዲሆን ቁርጠኛ የዘር ማጥፋት ስራዉን ያከናዉናል:: ቡሽቲዎችን በማሰማራት ኢሰበአዊ ስራዎችን በጸረ አማራ መንፈስ እንዲፈጸምባቸዉ ያደርጋል:: አንድ እስረኛ በመኢአድነት ቢያዝ: በግንቦት ሰባትነት ቢያዝ: በሰማያዊነት ቢያዝ: በአንድነት ፓርቲ አባልነት ቢያዝ: የሆነ ጥፋት አጥፍቶ ቢያዝ የሚቀጠቀጠዉ እና የዘር ማጥፋት የሚደርስበት በአማራ እነቱ ተፈርጆ ነዉ:: አይኑ እንዲጠፋ: ጆሮዉ እንዲደነቁር: የመራቢያ ፍሬዉ እንዲኮላሽ : እግር እና እጁ እንዲሰባብር እና አካል ጉዳተኛ እንዲሆን የሚደረገዉ የአማራ ዘሩ እየተጠራ ነዉ::

ሌላዉ ቀርቶ ከወያኔ ጋር ተባብረዉ የአማራን ህዝብ ሲያስፈጁ የነበሩ እና ትልልቅ ባለስልጣናት የነበሩ አማራ የወያኔ መሳሪያዎች ከወያኔ ጋር ሲጣሉ የሚደርስባቸዉ መከራ እና ስቃይ አማራነታቸዉ እየተቆጠረ ነዉ::ይሄም እጅግ ታላቅ መከራ እና ስቃይ ከዚህ ህገ መንግስታዊ ትንታኔ ጋር ተዳምሮ ሲሰላ ወያኔ ምንም አይነት ቅድመ ማስጠንቀቂያ እንደማያስተምራት ግልጽ ነዉ:: ሁሉንም ጸረ አማራ ስራዎችን አሁንም በአማራ ላይ ማከናወኑን የቀጠለዉ ሰይጣናዊ ሀይል ” እግዚአብሄር እጆቼን ሰልፍ ያስተምራል..” የሚለዉን መዝሙር እየዘመረ እጆቹን ወደ መሳሪያ የሰደደዉ የአማራ ህዝብ ቁጣም ገና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሊሆነዉ አልቻለም:: ከጅማሮዉ እስከ ፍጻሜዉ ግን በፍንትዉታ መልክ እዚህ ህገመንግስታዊ ትንታኔ እና አንደምታዉ ዉስጥ ታጭቆ የሚገኘዉ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለወያኔ ብቻ ሳይሆን ለመላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ነዉ::

መልካም ንባብ::


ዜጎችን ከኢትዮጵያ ወደ ኢትዮጵያ የማባረር ሂደት ህገመንግስታዊ አንደምታ እና ትዉፊታዊ እሴቱ
በሸንቁጥ አየለ ሚያዝያ/2004 ዓም (አአ)

በዘራቸዉ አማሮች የሆኑ አርሶ አደር ዜጎች ከቤንች ማጅ ዞን ከጉራ ፋርዳ ወረዳ ሀብት ካፈሩበት ፤ በህጋዊነት መሬት ይዘዉ እየገበሩ እያረሱ ከኖሩበት ቀያቸዉ አገራችሁ አይደለም፤ ደን ጨፍጭፋችሁዋል፤ ሀብታም እየሆናችሁ ባካባቢዉ ነዋሪ ላይ ተፅዕኖ ፈጥራችሁዋል በሚሉ ሰበቦች እንዲባረሩ እየተደረጉ መሆኑን ልዩ ልዩ ሚዲያዎች በስፋትና በጥልቀት እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡ የአሜሪካ ድምፅ፤ ጀርመን ድምፅ ፤ ሪፖርተር ጋዜጣ፤ አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ ፍትህ ጋዜጣና ልሎችም ሚዲያዎች የተፈናቀሉ ሰዎችን ጭምር እያቀረቡ ነገሩን በስፋት ለህዝብ አቅርበዉ ህዝብም በጉዳዩ ላይ መያዬት ከጀመረ ሰነባበተ፡፡

ስለተባረሩ ሰዎች ክልሉ በመገናኛ ብዙሃን የተለያዩና የሚቃረኑ መግለጫዎችን ሲሰጥ ይሰማል ፡፡ የፌደራል መንግሰትም በጉዳዩ ላይ ያለዉን አቁዋም ግልፅ አድርጎ አስቀምጦአል፡፡ ከመንግስት ወገንም ሆነ ከተለያዪ አካላት ድርጊቱን በመደገፍና በመቃወም የተለያዩ መግለጫዎች ቢሰጡም የህገ መንግስቱ የባለስልጣናትን ስነ ባህሪና ድርጊት ገዥነት ብሎም የዉሳኔያቸዉ ብቸኛ መሰረት ሊሆን እንደሚገባዉ በጥልቀትና በስፋት ሲተነተን አይስተዋልም፡፡ የዜጎች ከኢትዮጵያ ወደ ኢትዮጵያ የመባረር ጉዳይ መሰፈርና መለካት ያለበት ሀገሪቱ ካላት ህገመንግስት ማዕቀፍ አንፃር ብቻ እንጅ ፖለቲከኞች፤ ባለስልጣኖች ወይም ተቃዋሚዎች ከሚሰጡት ትንታኔ አንፃር ሊሆን አይገባም፡፡ ስለዚህ የዚህ ፅሁፍ ዋና አላማ ይህ ድርጊት ከህገ መንግስቱ አንፃር ምን አንደምታ አለዉ ? ለመፃኢቱ ኢትዮጵያስ ምን ትዉፊታዊ እሴት ሊያወርስ ይችላል? የሚሉት ነጥቦችን በተወሰነ ደረጃ ለመዳሰስ መሞከር ነዉ፡፡

1. በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የመኖር መብት

በህገ መንግሰቱ መሰረት ወላጆቹ ወይም ከወላጆቹ አንዱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነዉ (አንቀፅ 6/1) ፡፡ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ደግሞ በህገ መንግሰቱ የተቀዳጃቸዉ መብቶች አሉት፡፡ እነሱም በህግ ይጠበቁለታል፡፡ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ከፈቃዱ ዉጭ ዜግነቱ ሊገፈፍ አይችልም (አንቀጽ 33/1 )፡፡ ደግሞም ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የኢትዮጵያ ዜግነት የሚያስገኘዉን መብት፤ ጥበቃና ጥቅም የማግኘት መብት አለዉ (አንቀጽ 33/2).፡፡ ህገ መንግስቱ ለማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የመዘዋወር ነፃነት በአንቀፅ 32 አጎናፅፎአል፡፡

ወላይታ ፤ ሲዳማ ፤ አማራ ፤ ኦሮሞ ፤ ሶማሊ፤ ሐረሪ ፤ ትግሬ ወይም ሌላ ብሄር ሳይጠቅስ ስለ መዘዋወር ነፃነት እንዲህ ይላል፡-ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ወይም በህጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ዉስጥ የሚገኝ የዉጭ ዜጋ በመረጠዉ የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖርያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገዉ ጊዜ ከሀገር የመዉጣት ነፃነት አለዉ ፡፡ ሆኖም የደቡብ ክልል መንግሰት ከሰሜን አማራ የመጡ ሰዎች ከክልሉ እንዲባረሩ በደብዳቤ ሲያዝ ከላይ የተጠቀሱ ህገ መንግስታዊ አንቀፆችን ያገናዘባቸዉ አይመስልም፡፡ አንድ ሰዉ ከኢትዮጵያ ከየትኛዉም አቅጣጫ ቢመጣም በአንድ የክልል ሀላፊ በተሰጠ የደብዳቤ ትዕዛዝ የዜግነት ህገመንግስታዊ መብቱ ሊጣስ አይገባም፡፡

ደግሞም የክልሉ ፖለቲከኞች ሲናገሩ እንደሚደመጠዉ ክልሉ ያባረራቸዉ ህገ ወጥ የሆኑትን ከሰሜን አማራ የመጡ ዜጎችን ነዉ፡፡ለምሆኑ አንድ ዜጋ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሲንቀሳቀስ ህዊ ያልሆነ ዜጋ ሊያስብለዉና ከዚያ ክልል እንዲባረር የሚያስደርገዉ ምን ህገ መንግስታዊ አንቀፅ አለ ? ህገ መንግሰቱ የዜጎችን የመዘዋወርና መኖሪያን እና ስራን የመምረጥ መብትን አረጋግጦአል፡፡ አንድ ዜጋ ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል ሲሄድ የክልሉን እና የአካባቢዉን አስፈላጊ ህጎች እንዲያሙዋላ ይጠዬቃል እንጅ ከሌላ አካባቢ መጣህ ተብሎ ከአካባቢዉ አይባረርም፡፡ ምንም እንኩዋን ክልሉ ህጋዊነት የሌላቸዉን አባረርሁ ብሎ ቢናገርም የተባረሩት ዜጎች ደግሞ ግብር የገበሩበትን ካርኒ ሁሉ ሲያቀርቡ ተስተዉለዋል፡፡ ሆኖም ዋናዉ ጥያቄ አንድ ክልል ከሌላ ክልል የመጣ ኢትዮጵያዊ ዜጋን የማባረር ህገ መንግስታዊ ስልጣን አለዉ ወይ ? የሚለዉ ጉዳይ ነዉ ፡፡

2. የዜጎች ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች

የማንኛዉም ኢትዮጵያዊ የኢኮኖሚ የማህበራዊና የባህል መብቶች ሊከበሩለት እንደሚገባ በህገ መንግስቱ በአንቀጥፅ 43 ስር እንዲህ ሲል ተብራርቶአል፡-

o ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ዉስጥ በማንኛዉም ኢኮኖሚዊያ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያዉ የመረጠዉን ስራ የመስራት መብት አለዉ (43/1)

o ሁሉም ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያዉን ስራዉንና ሙያዉን የመምረጥ መብት አለዉ (43/2)

o መንግሰት ለስራ አጦችና ለችግረኞች ስራ ለመፍጠር የሚያስችል ፖሊሲ ይከተላል (43/6)

o መንግስት ዜጎች ጠቃሚ ስራ የማግኘት ዕድላቸዉ እየሰፋ እንዲሄድ ለማድረግ አስፈላጊ እርምጃዎችን ይወስዳል (43/7)

o ገበሬዎችና ዘላን ኢትዮጵያዉያን በየጊዜዉ እየተሻሻለ የሚሄድ ኑሮ ለመኖር የሚያስችላቸዉና ለምርት ካደረጉት አስተዋፅኦ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ተገቢ ዋጋ ለምርት ዉጤቶቻቸዉ የማግኘት መብት አላቸዉ፡፡ መንግስት የኢኮኖሚና የማህበራዊ የልማት ፖሊሲዎችን በሚተልምበት ጊዜ በዚህ መርህ መመራት አለበት (43/8)

ሆኖም ይህን የመሰለዉ ዉብ የህገመንግስት ክፍል ጉራ ፋርዳን አገራችን ብለዉ በአካባቢዉ ለብዙ ጊዜ ሰፍረዉ ይኖሩ እነበሩ ዜጎች ጋ ሲደርስ ክፉኛ ተጥሶአል፡፡ ግብርና ሙያን መርጠዉ & በጥረታቸዉና በጉልበታቸዉ ድህነትን አሸንፈዉ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ በትጋት እየተሳተፉ ያሉ ዜጎችን ለማፈናቀል ከተሰጡ ምክንያቶች አንዱ ሀብታም እየሆናችሁ በአካባቢዉ ማህበረሰብ ላይ ጫና ታመጣላችሁ የሚል ነዉ፡፡ እናም አማሮቹ ገበሬዎች ይህ ህገ መንግስታዊነት ቀርቶ የልማት ፅንሰ ሀሳብ ሊገልፀዉ በማይችል ህሳቤና ሰበብ ከኢትዮጵያ ወደ ኢትዮጵያ ይባረራሉ፡፡

የክልሉ መንግሰት በአንቀፅ 43/8 እንደተደነገገዉ እነዚህን አርሶ አደሮች ሊያበረታታ እና ኑሮአችዉም እንዲሻሻል ማገዝ ሲገባዉ ከቤታቸዉ ገፍትሮ በማስወጣት ያፈሩትን ሀብት እንኩዋን በቅጡ ለማደራጀት ጊዜ ሳይሰጣቸዉ አስገድዶ ያባርራቸዋል፡፡ ይህን ጉዳይ ሪፖርተር ጋዜጣ፤ አዲስ አድማስ ጋዜጣ፤ ፍትህ ጋዜጣ በስፋት የዘገቡት ሲሆን የዉጭ ሚዲያዎች የነገሩን ክብደት አፍታትተዉና አብራርተዉ ለማቅረብ የተፈናቃዮችን ምስክርነት እያጣቀሱ አቅርበዉታል፡፡ ጉዳዩን  በቅርበት የሚከታተለዉ፤ ለተፈናቃዮችም መጠለያ በመስጠት፤ የተለያዩ የተቃዉሞ መግለጫዎችን በማዉጣት፤ለጠቅላይ ሚኒስትሩም የተቃዉሞና የተማፅኖ ደብዳቤ በመፃፍ የሰዎች መባረር እንዲቆም የጠዬቀዉ ብሎም ግንባር ቀደሙን ሀገራዊ ሚና እየተወጣ ያለዉ ተቃዋሚዉ የፖለቲካ ፓርቲ የሆነዉ መኢአድ ደግሞ በቢሮዉ ለተፈናቃዮች መጠለያ ከመስጠት እስከ ምግብ ማቅረብ ተራምዶም ተፈናቃይ ገበሬዎችን በቻለዉ ሁሉ ለመርዳት ሲረባረብ ተስተዉሏል፡፡

ለምሆኑ በጥረታቸዉ ሀብት ያፈሩ ሰዎችን ፤ የዜግነት መብታቸዉን ተጠቅመዉ በሀገሪቱ ተዘዋዉረዉ ግብርናን ስራ አድርገዉ በመምረጥ በግብርና ላይ የተሰማሩ ዜጎችን ከሀገራቸዉ ማባረር ነዉ የሚገባዉ ወይስ በኢኮኖሚ እንዲጎለብቱ ፤ በባህል እንዲጠናከሩ በልዩልዩ ፖሊሲዎች መደገፍ ነዉ ተገቢዉ ህገ መንግስታዊ ትዕዛዝ? ዜጎች በመረጡት አካባቢ ለመኖር እና በመረጡት ስራ ለመተዳደር ተዘዋዉረዉም የተሻላቸዉን አካባቢ መርጠዉ መኖር መጀመራቸዉ ህጋዊ አካሄድ መሆኑን የክልሉ መንግስት ለምንድነዉ የማይቀበለዉ?

ክልሉ የሚሰጣቸዉ ምክንያቶች በሙሉ በህገ መንግስቱ መነፅር ሲቃኙ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብት ¾ሚንዱ እንጂ በምንም መልኩ ህገ መንግስታዊ መሰረት የላቸዉም፡፡ እንደሚታወቀዉ ህገ መንግስቱ የህጎች ሁሉ የበላይ (አንቀፅ 9/1) መሆኑ u=ታወጅም ይህ ህገመንግስት አሁን እተፈናቀሉት ሰዎች ላይ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶአል፡፡ ከሰሜን አማራ የመጡ ዜጎች ደቡብ ኢትዮጵያን ስለተቆጣጠሩት ወደ መጡበት እንመልሳቸዉ ማለት ከላይ ያዬንዉን የዜግነት መብት መንጠቅ ስለሆነ ህገ መንግሰቱንም መናድ ነዉ፡፡ ለምሆኑ ክልሉ ከህገ መንግሰቱ በላይ የሆነ ተጠይቅና ህግ መፍጠር ይችላል ወይ ? ወይስ ህግ አስፈፃሚዊ የመንግስት አካል በመሰለዉና ያዋጣኛል ባለዉ መልክ ብድግ እያለ ህገ መንግስቱ ዉስጥ የቆሙ መሰረታዊ የህግ መርሆችን ሳያገናዝብ የራሱን አስተዳደራዊ ትንታኔዎች መስጠት ይችላል ወይ?

ዛፍ ሲመነጥሩ ስለተገኙ ተባረሩ የሚለዉ ሰበብ በህገመንግስቱ ዉስጥ ከተዘረዘሩት የዜጎች መብት ጋር ሊሄድ የሚችል ጉዳይ አይደለም፡፡ ከሰሜን አማራ የመጡ ሰዎች ዛፍ ሲመነጥሩ ብሎ መናገር ምን ማለት ነዉ? አማራ ስለሆኑ ዛፍ ምንጠራ ይወዳሉ ማለት ነዉ? ነዉ ወይስ ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ ገበሬ የተለዬ የዛፍ አጥፊነት ባህሪ አላቸዉ ማለት ነዉ? ነዉ ወይስ የአማራ ገበሬዎች እንደ እብድ ዛፍ የማዉደም ስነል ልቦና አላቸዉ ማለት ነዉ? ደግሞስ በሽህ የሚቆጠሩ ሰዎች በህብረት ተመካክረዉ ዛፍ ምንጠራ ላይ ይሳተፋሉ ማለት ነዉ?
ምናልባትም ከመሃላቸዉ ጥፋተኛ ከተገኘ በአካባቢዉ ህግ እንደማንኛዉም አርሶ አደር ፍርድቤት ቀርቦ መቀጣትና መታረም እናዳለበት እሙን ነዉ ፡፡ ሆኖም ከሰሜን አማራ የመጣ ዜጋ ስለሆነና ዛፍ ሲመነጥር ስለተገኘ ወደ ሰሜን አማራ መልሱት ማለት የዜጎችን ህገመንግስታዊ መብት መጣስ ነዉ፡፡

ህገ መንግሰቱም ለአካባቢ ጥበቃ ህጋዊ አካሄዶችን አንደሚከተለዉ በአንቀፅ 92 አስቀምጦአል፤-
o መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ንፁህና ጤናማ አካባቢ እንዲኖር የመጣር ሀላፊነት አለበት (92/1)
o የህዝብን የአካባቢ ደህንነት የሚመለከት ፖሊሲና ፕሮግራም በሚነደፍበትና ስራ ላይ በሚዉልበት ጊዜ የሚመለከተዉ ህዝብ ሁሉ ሀሳቡን እንዲገልፅ መደረግ አለበት (92/3)

o መንግስትና ዜጎችች አካባቢያቸዉን የመንከባከብ ግዴታ አለባቸዉ(92/4)
እንግዲህ ህገ መንግስቱ አንድ የተረዳዉ ነገር አለ፡፡ የማህበረሰብና የዜጎች ተሳትፎ በሚወጡ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ላይ ወሳኝ መሆኑን፡፡ ይህም ማለት የህዝቡ ተሳትፎ ከሌለ በማህበረሰቡ ዘንድ ስለሚወጡ ፖሊሲዎች የግንዛቤ ዝቅተኝነት ሊኖር ስለሚችል ማህበረሰቡን በፖሊሲ ቀረጻ ላይ በማሳተፍ ፕሮጋራሞችን የራሱ እንዲያደርጋቸዉና አካባቢዉን የመንከባከብ ግዴታም እንዳለበት እንዲረዳ የማድረግ ስራ መሰራት እንዳለበት ያስረዳል ፤ የህጎች የበላይም ነዉና ያዛል፡፡

ይህ አስተሳሰብ ደግሞ በተሳትፎአዊ የልማት ሳይንስም ተቀባይነት ያገኘ አስተሳሰብ ነዉ፡፡ በሁሉ ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች ቀረፃ ላይ ህዝቡ ይሳተፍ የሚለዉ የዘመናችን ቁልፍ መርህ እሆነ መጥቶዋል፡፡ ያን ጊዜም ህዝብ የሚከናወኑ ልማቶችን እና ስራዎችን የራሱ የማድረግና በአካባቢም ሆነ በልማት ስራዎች ላይ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ጥፋትን እንዳያመጣ ይሆናል፡፡

ሆኖም ዜጎች አንድ ጠፋት ሲያጠፉ ማባረር ያዉም ከሰሜን አማራ የመጡ በሚል ህሳቤ ተነሳስቶ አባር የሚል አንደምታና ታሳቢን በህገ መንግሰቱ ዉስጥ አንድም ቦታ የለም፡፡ ለአማሮቹ አርሶ አደሮች ቤንች ማጂ ከአካቢዉ ነዋሪዎች እኩል አገራቸዉ ስላልሆነ ደን ሲያወድሙና ዛፍ ሲቆርጡ ስለተገኙ ወደ መጡበት ይመለሱ የሚለዉ አስተሳሰብና ትንታኔ የሀገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ ህግ በሆነዉ ህገ መንግሰት አንድም ተደጋፊነት የለዉም፡፡ አገራችን ደቡብ ኢትዮጵያም፤ ኦሮሚያም ትግራይም ፤ሶማሊያ ክልልም፤ አፋርም ፤ ጋምቤላም ነዉ ብለዉ ለሚያምኑ ዜጎች ከሰሜን አማራ የመጡ ሰዎች በሚል ህሳቤ በሀይል ወደ ክልላቸዉ ማባረር ተገቢ ነዉ የሚል ህሳቤን የቁዋጠረ ህገ መንግስታዊ ስንኝ አንድም ቦታ የለም፡፡

ደግሞሞ ይህ አይነት አስተሳሰብ በህገ መንግስቱ ከተደነገጉ ህጎች በላይ ጎልቶ ከወጣ በበርካታ ኢትዮጵያዉን ላይ ምን አይነት ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚለዉን ጣጣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በዉል የሚረዳዉ ጉዳይ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ብቸኛዉ የፓርላማ ተመራጭ የሆኑ ክቡር አቶ ግርማ ሰይፉ የሰዎቹን መባረር አስመልክተዉ ጥያቄ ሲጠይቁ የሚከተለዉን ጥልቅና የተሰደረ ሀሳብን ለመላዉ ኢትዮጵያዊ ባለአዕምሮ ሁሉ አካፍለዋል ‘ እንደሚታወቀዉ ክልላቸዉ አዲስ አበባ ባይሆንም በርካታ ኢትዮጵያዉያን በአዲስ አባባ እየኖሩና ኢንቨስት እያደረጉ ነዉ፡፡

ወደፊትም በርካቶች ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ እና አዲስ አበባ የእኔ ነዉ የሚል ወገን ድንገት ብድግ ብሎ ወደ ክልላችሁ ወጡ ቢልስ?’ የእኝህን ሰዉ ጥያቄ በነፃ ልቦና ብሎም በአርቆ አስተዋይ ህሊናዉ የመረመረ ባለአዕምሮ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ደግሞ ጥያቄያቸዉን ሰፋ አድርጎ በህሊናዉ ነገ የራሱን እጣ ፋንታ እያሰላሰለ ለምሆኑ ዛሬ በአማሮቹ ላይ የደረሰዉ ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ አማራ ክልል መባረር ምን አይነት የትዉልድ ትዉፊታዊ እሴትን ያወርሰን ይሆን እያለ በሀሳብ ሳይናጥ አይቀርም፡፡ ማህበረሰብ የማይናጥና የማይናወጥ የህግ መሰረት ላይ ቆሞ እጣፋንታዉን በግልፅ የህግ መርሆዎች መዳኘት እስካልቻለ ድረስ እዉነትም በሃሳብ መናጡ መቆሚያ የሚኖረዉ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሌላዉ ቀርቶ ዛሬ እጁ ላይ ጉልበትና ሀይል ተባብረዉ የገቡለት ወገን እንኩዋን በተሰደረ የህግ መሰረት ላይ ስለመቆሙ እርግጠኛ ካልሆነ በሰመመን መናጡና መናወጡ አይቀርም፡፡ የህግ ፈላስዉ ጆን ሎክ እንደሚለዉ ማህበረሰብ በህግ ማዕቀፍ ስነባህሪዉና ድርጊቱ ካልተመራና ካልተገዛ የአራዊት ባህሪ አለዉ፡፡

ዜጎች በግዳጅ ከአገራችዉ ኢትዮጵያ ወደ ሌላዉ የኢትዮጵያ ክፍል ክልላችሁ ካልሆነዉ ክልላቸሁ ወደ ሆነዉ ተብለዉ ሲገፈተሩ የሚኖረዉን ጫና ፤ የስነልቦና ቀዉስ ፤ የንብረት ብክነት እና ተያያዥ ጉዳዮችን በንፁህ ልቦናዉ እያሰበ የሚደመም የአዳም ልጅ በህሊናዉ የሚርመሰመስበት መሰረታዊ ተጠይቅ የጆን ሎክ ህሳቤን እየፈተሸ በመቀመጫዉ ላይ ቁልቁል በሚያሰጥም ጥቁር ራዕይ ከመጻኢዉ ትዉልዱ ጋር እያወጋ መባተት ብቻ ነዉ፡፡
ዜጎች ቤንች ማጂ ዞን መኖሪያ ፍለጋ ያቀኑት ወይም በቤንች ማጅ ኖረዉ ሀብት ያፈሩት ኢትዮጵያዊ ዜግነታቸዉን ተመርኩዘዉ እንዲሁም መንግሰት የሚባለዉን ተቁዋም ታምነዉ ነዉ፡፡ መንግሰት ደግሞ በህገ መንግሰቱ በአንቀፅ 89 እንደተገለፀዉ የዜጎችን ኢኮኖሚያዊ እርምጃቸዉን የመደገፍ ግዴታ አለበት፡-

o መንግስት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሀገሪቱ የተጠራቀመ እዉቀትና ሀብት ተጠቃሚዎች የሚሆኑበትን መንገድ የመቀዬስ ሀላፊነት አለበት (89/1)

o መንግስት መሬትን እና የተፈጥሮ ሀብትን በህዝብ ስም በይዞታዉ ስር በማድረግ ለህዝቡ ጥቅምና እድገት እንዲዉሉ ማድረግ አለበት(89/5)

የፌደራል መንግስት በግልፅ እንዳመነዉ በአካባቢዉ ሊኖር ለፈለገ ዜጋ ብቁ የሚሆን ባዶና ሰፊ ስፈራ በጉራ ፋርዳ ወረዳ አለ፡፡ ምናልባትም ዜጎች ህገመንግስታዊ መብታቸዉን ተጠቅመዉ ወደ አካባቢዉ መኖሪያ ፍለጋ የሚሄዱት በተናጠል፤ ለልማት በማይመችና ባልተደራጀ ሁኔታ እንኩዋን ቢሆን መንግሰት ማድረግ ያለበት ሁኔታዎችን ለዜጎች ማመቻቸትና ዜጎችም የሚሰጣቸዉን መመሪያ ተከትለዉ በተሻለ ሁኔታ እንዲሰፍሩ አቅጣጫ ማሲያዝ እንጅ ህገ መንግስታዊ መብታቸዉን ጥሶ ወደ መጣቸውሁበት ጥፉልኝ ማለት ህገ መንግስቱን መናድ ነዉ፡፡

ህገ መንግስቱ በየትኛዉም የሀገሪቱ ክፍል በሚገኝ ሀብት ለመበልጸግና ለመጠቀም ለዜጎች ሁሉ ፈቅዶ ሳለ የአንድ ክልል ሰዎች ወደ አንድ አካባቢ ሲሄዱ አንዴ ሀብታም ሆነዉ በአካባቢዉ ነዋሪ ላይ ተፅዕኖ አመጡ ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ደን ጨፈጨፉ ስለዚህም ወደ ሰሜን አማራ ይመለሱ ማለት አንድም ህገመንግስታዊ መሰረት የሌለዉ ዉሳኔ ነዉ፡፡ ደግሞስ ክልሉ የዜጎችን ህገ መንግስትዊ መብት ገፎ ሰዎቹ በአካባቢዉ እንዳይኖሩ የሚያባርራቸዉ በምን ስልጣኑ ነዉ?

3. በብሄር ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት

የተለያዩ ሚዲያዎችና በድርጊቱ ላይ ተቃዉሞአቸዉን ያሰሙ አካላት ተበዳዮችን እየጠዬቁና እያነጋገሩ ሁኔታዉን እንዳቀረቡት እነዚህ ተፈናቃዮች መብታቸዉን ለመጠዬቅ ወደ ተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትና ልዩ ልዩ ፍርድ ቤቶች ሲንከራተቱ የገጠማቸዉ ሁኔታ እጅግ ዉስብስብ እንደሆነ ተብራርቶ ቀርቦአል፡፡ እንዲያዉም የእስር፤ የማስፈራራት እና የማጉላላት ዕጣ ፋንታ ሁሉ ደረሰብን የሚለዉን እሮሮአቸዉን የአሜሪካ ድምፅ ፤ የጀርመን ድምፅ ፤ የተለያዩ ነፃና ገለልተኛ የግል ሚዲያዎች እንዲሁም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በስፋት አቅርበዉታል፡፡ ህገ መንግሰቱ ግን እንዲህ ይላል፤- ማንኛዉም ሰዉ ሰበዓዊ በመሆኑ የማይደፈርና የማይገሰስ በህይወት የመኖር የአካል ደህንነትና የነፃነት መብት አለዉ (አንቀፅ 14)፡፡ ማንኛዉም ሰዉ በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ መብት አለዉ(አንቀፅ 16)፡፡ በህግ ከተደነገገዉ ስርዓት ዉጭ ማንኛዉም ሰዉ ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን አያጣም(17/1)፡፡ ማንኛዉም ሰዉ በህግ ከተደነገገዉ ዉጭ ሊያዝ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም (17/2)፡፡

ሆኖም እነዚህ ሁሉ ህጎች ተጥሰዉ አላግባብ መታሰር ፤ድብደባ ፤ ወከባ ፤ ንብረት ማቃጠል እና ከሀገራቸዉ መባረር ሲገጥማቸዉ ይህን ህገ መንግሰት ለማስጠበቅ የቆመ ሀይል ሁሉ ለምን በርቀት ቆሞ ያስተዉላል ? ከሰሜን አማራ የመጡ ሰዎች የሚለዉ ትንታኔስ በዉስጡ ምን ይዞአል?

በክልሉ ባለስልጣናት የሚሰጠዉ መግለጫ የዘር ጉዳይ እንዳለበት በግልፅ የሚያመላክት ሆኖ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ የደቡብ ክልል ዋና ሀላፊ ከሰሜን አማራ የመጡ ሰዎች ሲሉ ያስተላለፉት ትዕዛዝ ይሄንኑ የዘር ጉዳይ ያመለክታል፡፡ ሆኖም ህገ መንግስቱ ምንም አይነት መድሎና መገለል ዘርን መሰረት አድርጎ ሊደረግ እንደማይገባ እንዲህ ያብራራል፡- ሁሉም ሰዎች በህግ ፊት እኩል ናቸዉ፡፡ በመካከላቸዉ ማንኛዉም ዓይነት ልዩነት ሳደረግ በህግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡ በዚህ ረገድ በዘር በብሄር በብሄረሰብ በቀለም በፆታ በቁዋንቁዋ በሀይማኖት በፖለቲካ በማህበራዊ አመጣጥ በሀብት በትዉልድ ወይም በሌላ አቁዋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸዉ (አንቀፅ 25) .

ደግሞም አንድ አካል ከህገ መንግሰቱ ወይም ከህጎች አንዱን ጥሶ ቢገኝ ማናኛዉም ሀላፊና የህዝብ ተመራጭ ሀላፊነቱን ሲያጎድል ተጠያቂ ይሆናል (አንቀፅ 12/2) ፡፡ እንዲሁም የመንግስት አሰራር ለህዝብ ግልፅ በሆነ ሁኔታ መከናወን አለበት (አንቀፅ 12/1) ፡፡ እናም ዜጎች ሲበደሉ ፤ህግ አለ አግባብ ሲፈርስና ሲናድ አፋጣኝ እርምጃ መዉሰድ ተገቢ ሆኖ ሳለ ሁሉም አካላት ነገሩን እንዳላዬ አይተዉ ያለፉት ስለምን ይሆን?

በህገ መንግሰቱ በአንቀፅ 18 ኢሰበአዊ አያያዝ ስለመከልከሉ አንዲህ ይላል ፡-ማንኛዉም ሰዉ ጭካኔ ከተሞላበት ኢሰበአዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለዉ (18/1)፡፡ ሆኖም ከቤንች ማጅ እየተባረሩ ያሉ አማሮች ይህ ሁሉ ህገመንግስታዊ መብታችዉ መጣሱን ልዩ ልዩ ሚዲያዎች እራሳቸዉ ተበዳዮቹን እያጣቀሱ አቅርበዋል፡፡ ለምሳሌም አንዱን አርሶ አደር ከአካባቢዉ እንዲለቅ ሲጠዬቅ ከአንዱ ቤት ወደ አንዱ ቤት ሲዘዋወር ስለተገኘ በዱላ ተቀጥቅጦ በደረሰበት ድብደባም አቀሉን ስቶ ከመኪና ላይ ወድቆ መሞቱን የአሜሪካን ድምፅ የተበዳይ ቤተሰቦችን እያነጋገረ ዜናዉን አቅርቦአል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ አለም አቀፍ የሰበኣዊ መብቶችንና ስምምነቶችን ተቀብላ በህገ መንግስት አፅድቃቸዋለች፡፡ ከእነዚህ ስምምነቶች ዉስጥ አንዱ ዜጎች በኑሮአቸዉ ላይ ጉዳት የሚያስከትል ድረጊት ተፈፅሞባቸዉ ቢገኝ እንደ ዘር ማጥፋት ወንጀል የሚወስደዉ ነዉ የሚለዉ ህግ ይገኝበታል፡፡ እንዲሁም በስብእና ላይ ስለሚፈፀሙ ወንጀሎች በህገ መንግስቱ በአንቀፅ 28 ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸዉ አለም አቀፍ ስምምነቶች ተግባራዊ እንደሚደረጉ ያትታል፡፡ ሆኖም ይህ ሁሉ ህግና አንቀፅ እያለ እነዚህ ዜጎች ለምን መብታቸዉ ይሄን ያህል ተጣሰ? በፈለጉት አካባቢ ለመኖር የተጎናፀፉት የዜግነት መብታችዉስ ለምን ይነጠቃል?

4. የንብረት መብት

ምደረ ክርስቲያን በመላዉ ኢትዮጵያ ፋሲካን በአል እያከበረ ባለበት ሌሊት፤ ቅዳሴና ዝማሬ ለአምላኩ ለክርስቶስ እያቀረበ ባለበት የትንሳኤ በአል ፤ ፆሙን በደስታ እየፈሰከ ባለቤት ሌሊት የሰባት ተፈናቃይ አርሶ አደሮች ቤት በእሳት ሲጋይ ማደሩን መኢአድ ሰሞኑን ባወጣዉ መግለጫዉ ጠቅሶ ይህ ጉዳይም እንዲቆም አሳስቦአል፡፡ ክርስቲያን የሆኑ ሰዎች በበዓለ ፋሲካ ከቤታቸዉ ተፈናቅለዉ ባሉበት ሁኔታ ቤታቸዉና ንብረታቸዉ በእሳት ሲቃጠል ሌሎች ወገኖችም ወጥተዉ በመመልከታቸዉ ብቻ የእስር እንግልት እንደደረሰባቸዉም በመግለጫዉ ላይ ተብራርቶ ተገልፆአል፡፡

አዲስ አድማስ ፤ ሪፖርተር፤ ፍትህና እና ሌሎች ሚዲያዎች ደግሞ በጥልቀት እንደዘገቡትና ሰፋሪዎችም እንደገለፁላቸዉ ‘ ንብረታችሁን ያፈራችሁት እዚሁ ስለሆነ ንብረታችሁን ትታችሁ ዉጡ ተብሎ ተነግሮን ባዶ እጃችንን እንድንወጣ ተደርገናል፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ በአጭር ጊዜ ዉጡ ስንባል ንብረታችንን ቦታ ቦታ የምናሲዝበት ጊዜ ይሰጠን ብለን ስንጠይቅ ንብረታችሁን ከፈለጋችሁ ዋጡት ወይም አቃጥሉት የሚል መልስ ተሰጥቶን ከአካባቢዉ አንዲትም ንብረት ሳንይዝ እንድንወጣ ተደርጎእ፡፡’ ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ሆኖም ህገ መንግሰቱ የንብረትን ጥበቃ ጉዳይ በዝርዝር አስፍሮ ለዜጎችም ንብረት ከፍተኛ ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ በአንቀፅ 40 በስፋት ያብራራል፡-

o ማንኛዉም የኢትዮጵያ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት መሆኑ ይከበርለታል (40/1)

o በጉልበት በካፒታል ወይም በፈጠራ ችሎታ የተገኘ ሀብት(40/2 )ሁሉ ንብረት ሲሆን የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግስትና የህዝብ ብቻ ነዉ፡፡ መሬት የማይሸጥና የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ንብረት ነዉ(40/3)

o የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች መሬት በነጻ የማግኘትና ከመሬታቸዉ ያለመነቀል መብታቸዉ የተከበረ ነዉ (40/4)

o ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ በጉልበቱ ወይም በገንዘቡ በመሬቱ ላይ ለሚገነባዉ ቁዋሚ ንብረት ወይም ለሚያርገዉ ቁዋሚ መሻሻል ሙሉ መብት አለዉ፡፡ ይህ መብት የመሸጥ የመለወጥ የማዉረስ የመሬት ተጠቃሚነቱ ሲቁዋረጥ ንብረቱን የማንሳት ባለቤትነቱን የማዛወር ወይም የካሳ ክፍያ የመጠዬቅ መብትን ያካትታለል(40/7)

እንዲያዉም አንቀፅ 26/1 ይህን ጉዳይ ሲያብራራ ማንኛዉም ሰዉ የግል ህይወቱ የመከበር መብት አለዉ፡፡ ይህ መብት መኖርያ ቤቱ ሰዉነቱና ንብርቱን ከመመርመር እንዲሁም በግል ይዞታዉ ያለ ንብረት ከመያዝ የመጠበቅ መብትን ያካትታል ይላል፡፡

እንግዲህ በህገመንግስቱ መሰረት እነዚህ ዜጎች ግልፅ የሆነ የንብረት መብት አላቸዉ፡፡ ሆኖም ደቡብ ኢትዮጵያ ያፈራህዉን ሀብት እዚችዉ ትተሃት ወደ አማራ ክልልህ ነቅለህ ጥፋልኝ የሚለዉ ህሳቢ ህገ መንግስቱን መቃረን ወይም መናድ ነዉ፡፡ ደግሞም እንደ ማንኛዉም ኢትዮጵያዊ አርሶ አደር እነዚህ ሰዎች በዬትኛዉም ክልል መሬት በነፃ የማግኘትና ሀብት የማፈራት መብታቸዉ የተጠበቀ መሆኑን ህገ መንግስቱ በግልፅ ደንግጎአል (40/4)፡፡ ከላይም እንደ ጠቀስንዉ በይትኛዉም የኢትዮጵያ ክፍል ተዘዋዉረዉም መኖር ህገመንግስታዊ መብታቸዉ ነዉና በዬትኛዉም ክልል መርጠዉ መኖር ይችላሉ፡፡ ምናልባትም አንድ ሰዉ ወንጀል ቢሰራ፤ ጥፋት ቢያጠፋ ፍርድ ማግኘት ያለበት በፍርድ ቤቶች ነዉ እንጅ ከሚኖርበት አካባቢ ወይም ሊኖርበት ከመረጠዉ አካባቢ ይባረር የሚል ህግ የለም፡፡ ህጉ አስፈላጊዉን ቅጣት ሁሉ ጥፋቱን ባጠፋዉ ግለሰብ ላይ የሚወስደዉም በፍርድ ቤቶች ሲሆን በፍትሐብሄሩም ሆነ በወንጀል ህጉ ዉስጥ አንድ ዜጋ ጥፋት በማጥፋቱ ከአካባቢዉ ይባረር የሚል አንቀፅ የለም፡፡ ቢኖርም ቅሉ ህገ መንግስቱ የህጎች የበላይ ነዉና ገዥ ሆኖ የሚወጣዉ ህገመንግስቱ ዉስጥ ያለዉ ህሳቤ ይሆናል ማለት ነዉ፡፡

5. ህግ የማግኘት መብት

የአካባቢዉ ካድሬ/ፖሊስ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንኩዋን ሳይይዝ በምን ስልጣኑ ነዉ ዜጎችን ከአንድ አካባቢ የሚያባርረዉ? ፍርድና ዉሳኔን የመስጠት ስልጣንስ አለዉ? ፍርድን ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሊሰጥ የሚችለዉ ፍርድ ቤት ሆኖ ሳለ እንዴት ዜጎች አለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በካድሬ ትዕዛዝ ብቻ ከሀገራቸዉ ይባረራሉ? ለመጭዉ ትዉልድስ ይህ ጥሩ የአስተሳሰብ ቅርስ ነዉ? እርግጥ ነዉ አንድ ወገን የጉልበት ብልጫ ካለዉ ሌላዉን ወገን ተነሳ ፤ተቀመጥ ፤ ተንቆራጥ እናም ተንከባለል ካሰኘዉም ተሰቀል ሊለዉ እና ያሰኘዉን ሊያደርገዉ ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ የሚከሰተዉ ግን የህግ መሰረትና ህሳቤ የሰዎችን ስነባህሪና ድርጊት በማይገዛበትና በማይመራበት ሁኔታ ዉስጥ ብቻ ነዉ፡፡ ሕገ መንግስት ፅፋና ቀርፃ በምትንቀሳቀስ አገር ዉስጥ ግን የሰዎች ስነባህሪና ድርጊተ በህገ መንግስት ህጎች ከዚያም ሲያልፍ ከህገ መንግስቱ በሚፈልቁና በሚወጡ ዝርዝር ህጎች መሰረት መገዛት አለበት፡፡

ህገ መንግስቱ ስለ ነፃ ዳኝነት አካል / አንቀፅ 78/ እና የዳኝነት ስልጣን/ አንቀፅ 79/ በግልፅ አስቀምጦአል፡፡ በየትኛዉም ደረጃ የሚገኝ የዳኝነት አካል ከማንኛዉም የመንግስት አካል ፤ከማንኛዉም ባለስልጣን ፤ እንዲሁም ከማንኛዉም ተፅዕኖ ነፃ ነዉ(አንፅ 79/)፡፡ ለምሆኑ ክልሉ ዜጎችን ከሀገራቸዉ የማባረር ስራ ሲሰራ የትኛዉ ፍርድ ቤት ወስኖለት ነዉ?

ከዚህ በተጨማሪም አንቀፅ 37 ስለ ፍትህ የማግኘት መብት ማንኛዉም ሰዉ በፍርድ ሊወሰን የሚገባዉን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በህግ የዳኝነት ስልጣን ለተሰጠዉ አካል የማቅረብና ዉሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለዉ (አንቀጽ 37/1 ) ብሎ ቢናገርም እነዚህ ተፈናቃይ ወገኖች ለተለያዩ ሚዲያዎች ብሶትና በደላቸዉን ያቀረቡት እንደሚከተለዉ ነዉ ፡- ‘ በወረዳም ፤ በዞንም፤ በክልልም ወዳሉ ፍርድ ቤቶች ስንሄድና አቤት ስንል ፍርድ ቤቶች ሊያስተናግዱን አለመፈለጋቸዉ አሳዝኖናል፡፡’ እና ታዲያ ህገ መንግስቱን ማን ይተግብረዉ? ፍርድ ቤት ፍርድ ለመስጠት ካልደፈረ በህገ መንግስት የተሰጠዉን ስልጣን በፖለቲከኞች ዉሳኔ ካስነጠቀ ታዲያ ፍርድ ቤቶችስ ህገ መንግስቱን በመናድ ተባበሩ ማለት አይደለም?

እንደሚታወቀዉ ዜጎች በጋራ የሚኖሩባት ኢትዮጵያ ትፈጠር ዘንዳ መንግስት የብሄሮችን የብሄረሰቦችን የህዝቦችን ማንነት የማክበርና በዚሁ ላይ በመመርኮዝ በመካከላቸዉ እኩልነት አንድነትና ወንድማማችነትን የማጠናከር ግዴታ አለበት (አንቀፅ 88) እንጅ ይህኛዉ ከዚህኛዉ አካባቢ ያኛዉ ከዚኛዉ በማለት ወይም የዚህ አካባቢ ሀብት ለዚህኛዉ ብቻ በማለት ህጋዊ ስራዉን ዘንግቶ በህጋዊነት ያልተሰጠዉን ስራ መስራት የለበትም፡፡

ወይም ሰሞኑን የደቡብ ክልለ ባለስልጣናት እያደረጉት እንዳሉት ከህገመንግስት ያፈነገጠ እርምጃ ከወሰዱ ብሁዋላ የተለያዩና ወጥነት የሌላቸዉን መግለጫዎችን መስጠት ህገ መንግስታዊ አካሄድ አያስብለዉም፡፡ በሚዴያዎች ስለተባረረዉ ሰዉ ቁጥር የተለያዬ ቁጥር ይሰጣል፡፡ የተባረረዉ ሰዉ ቁጥር ስምነት መቶ ነዉ፤ አንዴ ደግሞ ሶስት ሽህ ነዉ :: ሌሎች ምንጮች ደግሞ ሀያ ሁለት ሽህ ወይም ሰባ ስምንት ሽህ ነዉ የሚሉ መረጃዎች ሲኖሩ ክልሉ ግልፅ መረጃ ለኢትዮጵያ ህዝብ እሰካሁን በማስረጃ አስደግፎ ማቅረብ አልቻለም፡፡

ዋናዉ ጥያቄ ግን አስርስ ሆነ አንድ ኢትዮጵያዊን የሚያባርሩት በምን የህግ መሰረት ነዉ ? የሚለዉ ነዉ፡፡ መኢአድ በተለያዬ ወቅት በቢሮዉ እያስጠለለና ምግብ እየመገበ ወደ ሰሜን ሸዋ ብቻ በብዙ አዉቶብስ መኪና የተሸኙት ወገኖች ብዙ ሽህ ናቸዉ:: ከባድ የሆነዉ ስራ ደግሞ ሩቅ ወደ ሆኑት አካባቢዎች እነዚህን ወገኖች ማጓጓዝ ነዉ:: እናም ወደ ጎጃም: ወሎ እና ጎንደርም እንዲሁ እጅግ በርካታ ሽህ ወገኖችን ለመሸኘት መኢአድ ከፍተኛ ትጋት አሳይቷል::

ይሄ እንግዲህ በመኢአድ ብቻ የተደረገ ወገኖችን የማጓጓዝ ጥረት ነዉ:: በብዙ ሽህዎች በእዬ መንገዱ ባክነዉ እና ተዘርፈዉ በርካታ በደል እንደደረሰባቸዉ መረጃዎች አሉ:: በተጨማሪም እስከ አሁን በአአ የቀበሌ መጠለያዎች ዉስጥ በርካታ መቶ ሰዎች እንደተጠለሉ እየታወቀ የደቡብ ክልለ ለምን የተባረሩት አንዴ ሰላሳ ሶስት ናቸዉ አንዴ ንደግሞ ስምነት መቶ ናቸዉ ሌላ ጊዜ ደግሞ ሶስት ሽህ ናቸዉ ወይም ደግሞ ሀያ ሁለት ሽህ ሰዎች ይባረራሉ በማለት እርስ በእርሱ የሚቃረን እና እዉነትን የማድበስበስ ስራ እንደሚሰራ ግልፅ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ሆን ብለዉ የተባረሩት ሰዎች የምስራቅ ጎጃም አማሮች ብቻ ናቸዉ የሚል መግለጫ ሰጥተዋል:: ይሄ ግን ሀሰት ነዉ:: እዉን እንዲህ ያለ ስራ ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ ወገኑ ላይ ሊፈፅመዉ ይቅርና ሲታሰብ እንኩዋን ለህሊና ምቾት ይሰጣል ?

ህገ መንግሰቱ ለሴቶች መብት ( አንቀ ፅ 35 ) እና ለህጻናት መብት (አንቀፅ 36) ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸዉ ቢገልፅም የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ እንዲሁም የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ እንደ ዘገቡት ህፃናት ከትምህርት ገበታቸዉ ላይ በጉልበትና በግዳጅ እየተፈናቀሉ፤ ለርሃብና ለጥማት እየተዳረጉ እናቶችም በመንገድ እየወለዱ የእንግዴ ልጃቸዉን ዉሻ እየበላዉ ይባስ ብሎም በሚያልፉበት አካባቢ ያሉ ማህበረሰቦች እንዳያስጠጉዋቸዉ መመሪያ እየተሰጠ በከፍተኛ መከራና ስቃይ ዉስጥ እንዲያልፉ እየተዳረገ ነዉ፡፡

ተፈናቃዮቹ እንደሚተርኩት ትምህርት ቤትና መንገዶችን ሰርተዉ በአካባቢዉ ባለስላጣናት እንዳስመረቁና ለዚህም ታታሪነታቸዉ የምስክር ወረት ሁሉ እንደተሰጣቸዉ ነዉ፡፡ ‘ሆኖም ዛሬ እኛ ባሰራንዉ ት/ቤት ልጆቻችን እንደይማሩበት ተክለከሉ፡፡’ ሲሉ ምሬታቸዉን ለተለያዩ ሚዲያዎች ገልፀዋል፡፡
ዛሬ ሰዉ እንኩዋን በሀገሩ በኢትዮጵያ በሰዉ ሀገር ሄዶ ሀብት አፍርቶ ተከብሮና ታፍሮ ከሰዉ ልጆች ጋር ሁሉ በህብረትና በዉህደት በሚኖርበት ዘመን ዜጎች በኢትዮጵያ ሀብት በማፍራት ተፅዕኖን በአካባቢዉ ማህበረሰብ ላይ ፈጠራችሁ ፤ ዛፍ ጨፈጨፋችሁ ተብለዉ መባረራቸዉ አግባብ ነው ? ህገ መንግስቱስ የሚደግፈዉ እርምጃ ነወይ?

6. ማካካሻ የማግኘት መብት

በቅርቡ በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችና ባለአዕምሮ ሊቃዉንት አስፍተዉና አጥልቀዉ እያራመዱት ያለዉ የህግ ትምህርትን ከኢኮኖሚክስ እንዲሁም የህግ ትምህርትን ከልማት ሳይንስ ጋር በማጋባትና በማዋሃድ የተዋጣለት የማህበረሰብ የእድገት ቀመር ፍለጋና አሰሳን በመጠኑም ቢሆን ያነበበ ባለስልጣንና ፖሊሲ አዉጭ ስለልማት ሲያስብ ወይም ስለ ኢኮኖሚ ልማት ሲጨነቅ አብሮና አጣምሮ የሚያስበዉ ጉዳይ የህጉንም ዘርፍ ነዉ፡፡ ህግ በልማት ጉዞ ላይ ያለዉ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ጫና ተሰፍሮና ተለክቶ አያልቅምና፡፡ በተለይም እንደ ኢትዮጵያ በፍጥነት በልማት የመራመድ ትልም ያለዉ ሀገር ከልማቱ ጋር የህጉን ቅንጅት አጥብቆና አጥልቆ ማስተሳሰር ካልቻለ የልማቱ ፍጥነት ፤ ቀጣነት ብሎም ምሉዕነት መሰናሰኛዉና ዉሉ ለተወሰኑ ግለሰቦች በዉፍረት የሚታይ ለቀሪዉ ደግሞ በብዥታና በቅጥነት የሚስተዋል ጉዳይ እንዳይሆን ተገቢ ትኩረት ለዘርፈ ብዙ ጉዳች መስጠት መልካም ነዉ፡፡

ከሀገራቸዉ ከጉራፋርዳ የተፈናቀሉ ዜጎች ደጋግመዉ ሲናገሩ የሚደመጠዉ ከመሰረቱት መልካምና የተደላደለ ህይወት ወደ ድህነትና ወደ መጥፎ ህይወት እየተገፉ ያሉት ህጉ በልማት ጎዳና ላይ የሚያደርጉትን ግስጋሴ ሊያስከብርላቸዉ ስላልቻለ ነዉ፡፡ በተደላደለ ህይወት ዉስጥ ፤ ድህነትን አሸንፈዉ የተሻለ ዜጎች ለመሆን አፈር ገፍተዉ ደፋ ቀና ይሉ የነበሩ በርካታ ሽህ ዜጎችን ወደ አዘቅታዊ ድህነት መግፋት ህገ መንግሰትቱን መናድ ነዉ፡፡ ልማት ማለት በሁሉም ዜጎች ርብርብ የሚመጣ እንጂ በጥቂት ኢንቨስተሮች የሚመጣ ጉዳይ አይደለም፡፡ በልማት ጎዳና እየገሰገሱ የነበሩ ዜጎችን ከልማት ማናጠብና ወደ ማይጨበጥ ድህነት መምራት ህገ መንግስቱን መጻረር ነዉ፡፡

ምናልባትም ቦታዉ ለልማት ተፈልጎ ከሆነም ዜጎች አላግባብ ልክ ዜጋ እናዳልሆኑ ሁሉ መብታቸዉ ሳይከበርና ካሳ ሳይሰጣቸዉ መባረር የለባቸዉም፡፡ በህገ መንግሰትቱ በአንቀፅ 44 / 2 አንደተብራራዉ መንግስት በሚያካሂዳቸዉ ፕሮግራሞች ምክንያት የተፈናቀሉ ወይም ኑሮአቸዉ የተነካባቸዉ ሰዎች ሁሉ በመንግስት በቂ እርዳታ ወደ ሌላ አካባቢ መዘዋወርን ጨምሮ ተመጣጣኝ የገንዘብ ወይም ሌላ አማራጭ ማካካሻ የማግኘት መብት አላቸዉ፡፡

ሆኖም ከቤንች ማጅ የተባረሩ ዜጎች ይህን እድል ሊያገኙት ይቅርና አቤቱታቸዉን በአግባቡ እህ ብሎ የሰማቸዉ ፍርድ ቤት የለም፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎች እንደተዘገበዉና እነሱም እንዳብራሩት ፤- ‘በአዉቶቡስ እየተጠረዝን በሌሊት ወደ ትዉልድ አገራችሁ እየተባልን እንባረራለን፡፡ አገራችን ከኢትዮጵያ ዉጭ ወዴት ነዉ? ህገመንግሰትቱ የሰጠንን በሁሉም ኢትዮጵያ የመኖር መብት የአካባቢ ባለስልጣኖች እንዳሰኛቸዉ የሚነጥቁን ከሆነ ዋስትናችን ምንድን ነዉ ? ፍርድ ቤቶችስ ምን አይነት ጫና ቢኖርባቸዉ ነዉ የእኛን ጉዳይ እንዳያዩ የወሰኑት?’ እያሉ ተፈናቃዮቹ በርካታ ጥያቄዎችን ያቀርባሉ፡፡ ጥያቄዉ ግን ወደ ልቦና ባይገባም እንኩዋን ቢያንስ ጆሮ ላይ ነጥሮ ቢመለስም ቅሉ የሰዎቹን ጩህት ያደመጣቸዉ የለም፡፡

7.የተፈናቃዮች የፍትህ ጥያቄ

በተለያዩ ሚዲያዎች የተለያዩ ተፈናቃይ አርሶ አደሮች የፍትህ ጥቄያቸዉን በተለያዬ መልክ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ ሆኖም ሲጠቀለልና ሲጨመቅ ፡-‘እኛ ገበሬዎች ነን፡፡ ሰርተን እና አፈር ገፍተን በሀገራችን በኢትዮጵያ መኖር ብቻ ነዉ የምንፈልገዉ፡፡ ጥቄያችንም የተነጠቅንዉ ህገ መንግስታዊ መብታችን ይከበር፤ ሀብታችን ይመለስ፤ ወደ ነበርንበት ቦታችንም እንመለስ፤ ቦታዉን መንግስት ለልማትም ከፈለገዉ ተመጣጣኝ ካሳ ይሰጠንና ሌላ ጋ ያስፍረን፤ እንዲሁም የተቃጠለዉ ቤታችን እና ንብረታችን ተገምቶና ተሰልቶ ካሳ ይሰጠን’ የሚል መልዕክት ያለዉ ሆኖ ይገኛል፡፡

በህገ መንግስቱ መነፅር ጉዳዩን ስንመረምረዉ ደግሞ የተፈናቃዮቹ ሰዎች የአማራ ብሄር ወይም የሌላ ብሄር መሆናቸዉ ትርጉም የለዉም፡፡

ዋናዉ ነጥብና ጥያቄ ይህ አሁን በደቡብ ክልል የተወሰደዉ እርምጃ የዜጎችን በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል የመኖር መብትን የሚነጥቅ ነዉይ? ይህ አስተሳሰብ እንደ እሴት ሆኖ በማህበረሰባችን ዉስጥ ከሰረፀ ዛሬ በእነዚህ ወገኖች የተጀመረ አካሄድ ወደ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ቤት ላለመንደርደሩ ማረጋገጫ አለ ወይ? ኢትዮጵያዊ በሁሉም ቦታ እንዳይኖር የመከልከል አካሄድ ህገመንግስቱን ከመጣሱም በላይ ለመጭዉ ትዉልደ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ጥልቅ ነቀርሳን ፈጣሪ እሴት አይደለም ወይ ?

ለምሆኑስ የክልሉ መስተዳድር ዜጎችን ከክልሉ የማባረር ስልጣን አለዉ ወይ ? በዚህና መሰል ጉዳዮች የፍርድ ቤቶች ሽሽትና ዝምታን መምረጥስ አግባብ ነዉይ? በኢትዮጵያ የህግ አስፈፃሚዉ፤ የህግ አዉጭዉና የህግ ተርጉዋሚዉ አካላት የስልጣን ክፍፍል፤ ሚዛን ጥበቃና የእርስ በእርስ ቁጥጥር በዚህና በመሰል ጉዳዮች ላይ በመንተራስ ሲመረመር ተጎትቶ የሚወጣዉ እዉነት ምንድን ነዉ? የሚሉት ጥቄዎች በልዩ ልዩ የህግ፤ የስነልቦና፤ የሶሽዎሎጂ ፤የኢኮኖሚክስ፤ የታሪክ፤ የፖለቲካ፤ የልማት ሳይንስ ወዘተ ምሁራን ትንታኔ እንዲቀርብባቸዉ ሀሳብ እያጫርኩ ለዛሬ ፅሁፌን እዚህ ላይ እገታለሁ፡፡

የጥበብና የፍቅር አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስ የተመሰገነ ይሁን

ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይባርክ !