የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ህብረት ናላዉን ያዞረዉ ወያኔ በትግራይ ተወላጆችም ስልጣኑን ልቀቅ የሚል ጥያቄ ቀረበለት

ሸንቁጥ አየለ

– የወያኔ ሚኒስቴሮች አማራ እና ኦሮሞ አንድ በመሆን የጋራ ትግል እያከናወነ ስለሆነ 25 አመታት የጎነጎኑትን የጥላቻ መንፈስ ሁሉ እንደናደባቸዉ ሲያስተዉሉ ” አማራ እና ኦሮሞ በምንም ታምር አንድ ሊሆን የሚችል ህዝብ አይደለም” እያሉ በይፋ መናገር ጀምረዋል::

-እብድና ዘመናይ የልቡን ይናገራል ብሎ የህዝብ ተረት የጽሁፉ ማጣቀሻ አድርጎ የጻፈን ወጣት የሀሳብ አቀንቃኝ በቴሌቪዥን የዶክመንተሪ ፊልም ድራማቸዉ የሚፈርጁት ወያኔዎች አሁን መፈረጅ የማይችሉት ህዝብ ተነስቶባቸዋል:: ቢፈርጁትም ሆነ ቢወነጅሉት የማይቆም የህዝብ ማዕበላማ ቁጣ ገጥሟቸዉ ተጨንቀዋል:: የሆድ ቁርጥት ብቻ አይደለም::የራስ ምታትም ነዉ የገጠማቸዉ::

-ሰሞኑን በጎርረቤት ሀገራት በስደት ላይ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን የደረሰኝ መልዕክት ደግሞ የሚያስለቅስ የወያኔ ደባ መገለጫ ቢሆንም ከዚያ በላይ ግን የወያኔን መራራ ምጥ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነዉ::በጥገኝነት እና በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን መሃከል መተማመን እና ወንድማማችነት እንዳይፈጠር ” ሀገር ቤት አማራ እና ኦሮሞ በጋራ ወያኔን እየታገሉት ነዉ የሚባለዉ ሀሰት ነዉ:: እንዳታምነዉ እርሱ አማራ ነዉ:: እንዳታምነዉ እሱ እስላም ነዉ:: እንዳታምነዉ እርሱ ኦሮሞ ነዉ:: እንዳታምነዉ እርሱ ክርስቲያን ነዉ:: እንዳታም ነዉ እንዳታምኚያት” የሚል ሰፊ ማህበረሰብን የመበታተን ስራ እየሰሩ ነዉ:: በስደት ላይ የሚገኝ ዜጋ እንኳን ተረዳትቶ መራራዉን የስደት ኑሮዉን እንዳያሸንፈዉ የወያኔዎች የክፋት መንፈስ አሁንም ልዩነት እና ጥላቻን ይሰብካል::

– ወያኔ ለመሆኑ አማራ እና ኦሮሞ ለምን አንድ ሆኑ ይላል? የጋራ ራዕይ ያላቸዉ ህዝቦች ስለሆኑ ነዋ:: የጋራ ዲሞክራሲ እና ፍትህ ስለተጠሙ ነዋ:: የሚስማሙበት እና የሚያስተዳድሩት የበለጸገች ኢትዮጵያን ስለፈለጉ ነዋ::ወያኔ እንደሚለዉ አማራ እና ኦሮሞ ከአንድነታቸዉ ልዩነታቸዉ የሰፋ ህዝቦች ሳይሆኑ ከልዩነታቸዉ አንድነታቸዉ የበዛ ህዝቦች ስለሆኑ ነዋ:: አማራ ከጎንደር እና ከጎጃም ምን አለ? የኦሮሞ ወንደሞቼ መከራ እና መጨፍጨፍ : መታረድ እና መገፋት ይብቃ አለ:: ኦሮሞስ ከሸዋ ምን አለ? አማራ ወንድሜ ነዉ::አማራ የኛ ነዉ አለ::

– ወያኔ እንዲህ አይነት የፍቅር ሀሳብ በኢትዮጵያ ምድር ይቀነቀናል ብላ አልማም አስባም አታቅም ነበር:: በርሷ ቤት ሁሉንም የጥላቻ መንገዶች ዘርግታ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ እርስ በእርሱ ሲጨፋጨፍ እርሷ ዉስኪዋን እየጠጣች ጭፈራ ቤት ስታደራ ልትኖር ነበር ቀመሯ::

-ከሰዉ ሀሳብ የእግዚአብሄር ሀሳብ ይበልጣል ሆነና ነገሩ የህዝቡን መንፈስ እግዚአብሄር በአንድ ገመድ ገመደዉ:: ህዝብ ሳይመክር አንድ ልብ ሆኖ ተገኘ::ፖለቲከኞች ሳይመክሩት እና ሳይነግሩት ከህዝቡ ልብ ዉስጥ ኢትዮጵያዊነት እንደ ጥልቅ የዉቃያኖስ ሿሿቴ ሲንሿሿ ተደመጠ:: በወልቃይት ህዝብ ላይ በሚደርሰዉ የዘር ማጥፋት በደል: መገፋት እና መከራ የተጠራዉ ሰላማዊ ሰልፍ የመላዉ ኢትዮጵያ ህዝብ መከራ እና መገፋት ማንጸባረቂያ መድረክ ከመሆን ዘሎ የኢትዮጵያዉያን የወንድማማችነት መስበኪያ መድረክ ሆኖ ቁጭ አለ::

-ህዝቡ ከፖለቲከኞች ሁሉ ቀድሞ ፖለቲከኞች ሲሰሙት ጆሯቸዉን ጭዉ የሚያደርግ: ተቃዋሚዎች እራሳቸዉ በሀፍረት እስኪንቀጠቀጡ ድረስ የኢትዮጵያዊነትን ሀያል የፍቅር መንፈስ ጥልቀት እንዳልተረዱት እስኪደመሙ ድረስ የጎንደር አማራን እልህ እግዚአብሄር እንደ ዉቅያኖስ ምንጭ ድንገት በሀይል እና በእልህ እንዲፈልቅ አደረገዉ:: እናም ማንም ያልጠበቀዉን የተራቀቀ የኢትዮጵያዊነት መልዕክት ማንም ሳይጽፍለት አንግቦ : አረንጓዴ ቢጫ ባንዲራዉን ከተቀበረበት በማዉጣት ለብሶና ታጥቆ አደባባይ ወጣ::የምሞተዉ ስለ አማራ ወገኖቼ; ስለ ኦሮሞ ወንድሞቼ ነዉ ብሎ : ፍትህ ለኢትዮጵያ ሁሉ ይሁን ብሎ ሲናገር ወያኔን ተርበተበተ:: ሌላዉ ቀርቶ ልባቸዉ በኢትዮጵያዊነት ላይ በጥላቻ የቀዬመ ተቃዋሚዎችን እንኳን ድንገት የመንፈስ ለዉጥ እና ነዉጥ ዉስጥ ገቡ ::

-ከሸዋ መልሱ ፈጣን ነበር:;የሸዋ ኦሮሞ እንደ ጎንደር አማራ ኢትዮጵያ በአባቶቹ ደም ተቦክታ የተሰራች መሆኗን ያዉቃል እና ፈጣን መልስ ለጎንደር አማራ ወንድሞቹ ጥሪ አጸፋዉን አስተጋባ::እንዲህ አለ :- ” አማራ የማነዉ? አማራ የኛ የኦሮሞዎቹ ነዉ:: አማራ ምናችን ነዉ? አማራ የኛ የኦሮሞዎች ወንድም ነዉ! የአማራን ህዝብ መግፋት እና መግደል ይቁም”::

– እናም ወያኔ ያኔ ብርክ ያዘዉ:: ሚኒስቴሮች: የተንኮን እና የጥላቻ አማካሪዎች ምላሳቸዉን መሳል ጀመሩ:: የጥላቻ ጽንሰ ሀሳብ ማዉጠንጠን ጀመሩ::ሳያዉቁትም አዉቅዉትም የጥላቻ መሃንዲስ መሆናቸዉን ለኢትዮጵያ ህዝብ እራሳቸዉ እየመሰከሩ “አማራ እና ኦሮሞ ምን አንድ የሚያደርገዉ የጋራ አጀንዳ አለዉ?ምንስ አንድ ያደርገዋል? እንዴትስ አንድ ሆኖ በኛ ላይ ለተቃዉሞ ይነሳል? በፍጹም አንድ መሆን የለባቸዉም” ብለዉ ሳያፍሩ ተናገሩ:: ጉድ እኮ ነዉ:;አንድ ሀገር እመራለሁ የሚል ሀይል ለምን ህዝብ አንድ ሆኖ ብሎ እንዲህ ሲብከነከን ምናልባት በአለም ታሪክ የመጀምሪያዉ ሰይጣናዊ ተምሳሌት ሳይሆኑ አይቀሩም::

-የሆኖ ሆኖ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ህብረት ናላዉን ያዞረዉ ወያኔ ሌላ እንደ ሀተት በሽታ ቁጭ ብድግ የሚያደርግ የህዝብ ቁጣም ተከትሎ መጥቶለታል:: ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል የትግራይ ተወላጆችም ስልጣኑን ልቀቅ የሚል ጥያቄ በማንሳት እና የስም ዝርዝራቸዉን ይፋ

በማድረግ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄ መቀበላቸዉን እና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን መሰለፋቸዉን እየገለጹ ነዉ:: ሰሞኑን በኢሜይል በስፋት እየተሰራጨ ያለዉ መልዕክት እንደሚያስረዳዉ ወያኔ በፍጥነት ሰላማዊ የሽግግር መንግስት የሚቋቋምበትን ሁኔታ በማመቻቸት እርሱ ስልጣኑን ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያስረክብ እንዲሁም በኢትዮጵያ ብሄረሰቦች መሃከል አላስፈላጊ የደም መፋሰስ እንዳይፈጠር ሁሉም ወገን ነገሮችን በርጋት እንዲይዛቸዉ የሚያሳስብ መልዕክት አስተላልፈዋል::እሰይ ኢትዮጵያዉያን አሁን ቀስ በቀስ እየተግባቡ ነዉ ማለት ነዉ::

-እንግዲህ ወያኔ ብቻዉን ቀረ ማለት ነዉ::የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ ጥያቄዉን በአንድ መስመር ላይ እያሰለፈ ነዉ::ወያኔ ስልጣኑን መልቀቅ አለበት::ሀገሪቱ ካሁን ብኋላ ለዲሞክራሲ በሯን ወለል አድርጋ መክፈት አለባት:: የኢትዮጵያ ህዝብ የስልጣን ባለቤት መሆን አለበት:: የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ይፈልጋል? ምንስ ይመኛል ? ምንስ ራዕይ አለዉ? ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ; ለሁሉም የምትመች እና ሁሉም የሚስማማባት ሀገር ተፈጥራ ማዬት ነዉ::

-ይሄ ነገር እንዳይፈጠር የሚፈልግ ወያኔ ብቻ ሆኖ ቀረ ማለት ነዉ:: ቢሆንም አሁንም ለወያኔ ቀኑ ገና አልጨለመበትም::ነገሮች ፈጽሞ ከቁጥጥሩ ዉጭ ሳይሆኑ በቅንነት የምዕራባዉያን አጋሮቹን: እያንዳንዱ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ: የታጠቀ የፖለቲካ ድርጅት: የሲቪክ ማህበራት እና ሌሎችንም የሚያገባቸዉን ሁሉ በማካተት የተሳካለት የሽግግር መንግስት እንዲመሰረት እና በፍትነትም ህዝብ የሚመርጠዉ መንግስት እንዲመሰርት ለማገዝ የሚያስችለዉ አቅም አሁንም አለዉ:: ቀኑ ሳይጨልም ይሄን ነገር ብቻ ወያኔ ቢፈጽም የኢትዮጵያ ህዝብ ታላቅ ባለዉለታ ይሆናል:: ህዝቡም 25 አመታታ ሙሉ የሰራዉን ሀጢያት ሁሉ ይቅር ሊለዉ ይችላል:: ደግሞም የኢትዮጵያ ህዝብ የይቅርታ መንፈስ ያለዉ ህዝብ ነዉ እና ይቅርታ ያደርግለታል::

-ህዝብ ሆደ ሰፊ ነዉ::ሀገርም ህያዉ ነዉ::ትዉልድ እንደ ዥረት ፍሰት አይቋረጥም::መንግስታት ያልፋሉ::ስልጣን: ዝና እና ሀብት ይጠፋሉ::መልካም ስራ እና ህዝባዊነት ግን በሆደ ሰፊዉ ህዝብ መሃከል: በህያዉ ሀገር ዉስጥ: እንደ ዥረት በሚፈሰዉ ትዉልድ ዉስጥ እንደ ቀንዲል ሻማ ሲያበራ ይኖራል:: ወያኔ ሆይ በመጨረሻዉ ሰዓት እንኳን ታሪክ የመስራት እንድል አለህ እና እንደገና እራስህን ለመመርመር እስከ መጨረሻዉ አትዘግይ:: ብትዘገይም ቀንህ አሁንም ተጠቅልሎ ወደ መቃብር አልገባም እና ኢትዮጵያም ብዙ ሳትደማ አንተም ተጠቅልለህ ወደ መቀመቅ ሳትወርድ የማስተዋል መንፈስን እግዚአብሄር ይላክልህ::

https://www.facebook.com/S.Ayele.Eth/posts/1103660763016308