ዐማራው ዐማራዊ ማንነቱን አረጋግጦ ጀግንነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን በደሙ እያስከበረ ነው!

ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት             ቅዳሜ ሐምሌ ፴ ቀን ፪ሺህ፰  ዓ.ም.             ቅፅ ፬ ፣ ቁጥር ፲፱

ዐማራው፣ ዐማራዊ ማንነቱን አረጋግጦ፤ ጀግንነቱንና ኢትዮጵያዊነቱን በደሙ እያስከበረ ነው!

ዐማራው የኢትዮጵያዊነት ዋልታና ማገር፣ ወራጅና ጭምጭም፣ ስሚንቶና አሸዋ መሆኑ ይታወቃል። ይህን ማንነቱን ጠንቅቀው የሚያውቁ፤ የአገርና የትውልድ ከኻዲዎች፣ ዐማራውን የሌሎች ነገድና ጎሣዎች ጠላት አድርገው በመሳል፣ ላለፉት ፳፭(ሃያ አምሥት) ዓመታት የዘረኛው የትግሬ ወያኔ አገዛዝ፣ የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል እንዲፈጸምበት አድርገዋል። በመሆኑም በቁጥር ከአምስት ሚሊዮን የማያንሱ ዐማሮችን በልዩ ልዩ መንገዶች ከምድረ-ገጽ እንዲጠፉ አድርገዋል። አንዳንድ አወቅን የሚሉ፣ የማንነት ቀውስ ውስጥ የገቡ ሰዎችም «ዐማራ የሚባል ነገድ የለም» እስከ ማለት የደረሱ መኖራቸውን፣ ዐማራው በትዕግሥትና በትዝብት ሲያያቸው እንደኖረ ይታወቃል። ወያኔም በትዕቢት ተወጥሮ፣ ዐማራን «ፈሪ፣ ሽንታም፣ ወራሪ፣ ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ»፣ ወዘተርፈ እያለ የዐማራን ዘር ከመግደልና ከማንገላታት አልፎ፣ መልካም ስምና ታሪኩን ጥላሸት ሊቀባ መሞከሩ በግልጽ ይታወቃል። ሆኖም፣ ሁሉም ነገር ገደብና ወሰን አለውና፣ የዐማራው ድምፅ ከፍ ብሎ እንዲሰማ በቆራጥነት የቆሙት ልጆቹ ባሰሙት ጩኸት፣ ይኸውና የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የዐማራው ሕዝብ ከሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ፋና ወጊነት የተቀጣጠለው ሕዝባዊ አመጽ ጎንደር ከተማን፣ አዘዞን እና ደንቢያን አካቶ፣ በዛሬው ዕለት ማለትም ሐምሌ 30 ቀን2008 ዓ.ም. ሕዝባዊ አመጹና እምቢተኝነቱ ወደ ገብርየ አገር፣ «ራስ ጋይንት» ተሸጋግሮ ውሏል። የራስ ጋይንት ሕዝብ የወያኔን የስለላና የአፈና መዋቅር በጣጥሶ፣ «ወልቃይት ጠገዴ ዐማራ ነው!»፣ «ደንበራችን ተከዜ ነው!»፣ «አላማጣ፣ ሰቆጣ የዐማራ ነው!»፣ « የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች፣ ኮሎኔል ደመቀ፣ አንዱዓለም አራጌ፣ እስክንድር ነጋ ይፈቱ! በኦሮሞ ወንድሞቻችን ላይ የተከፈተው ጥቃት ይቁም!» እያሉ፣ ዐማራዊ ማንነታቸውን አስረግጠው፣ ጀግንነታቸው በኢትዮጵያነት የተለወሰ ኅብር መሆኑን አሳይተዋል።

የዐማራዊነት ጀግንነትን እንኳን ወዳጅ ጠላቶች፣ ማለትም፦ ደርሽቦች፣ ግብፆች፣ ጣሊያኖችና እንግሊዞች የመሰከሩት ገሐድ ዕውነት ለመሆኑ ለአፍታ መጠራጠር አይቻልም። ይህ ጀግንነትና ኅብረ-ብሔራዊነት የዐማራው ማንነት መገለጫው በመሆኑ፣ ሌሎቹ አግልለውትና የሞት ፍርድ ፈርደውብት እያለ እንኳን፣ ይህንም እያወቀ፣ በእነርሱ ላይ ቂምም ሆነ ጥላቻ በልቡ አልቋጠረም። ጎንደር፣ ጋይንት፣ ደብረታቦር፣ ባሕርዳር፣ አዘዞ እና ቆላድባ በተካሄዱ የሕዝባዊ እምቢተኝነት የተቃውሞ ሰልፎች፣ «በኦሮሞ ወንድሞቻችን ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋት እንቃወማለን!»፣ «በቀለ ገርባ ይፈታ!» የሚሉ መፈክሮችን ከራሱ ኅልውና በፊት አስቀድሞ አስተጋብቷል። ይህ የዐማራው የማንነቱ መለያ፣ የሆደ ሠፊነቱ መገለጫ፣ የትዕግሥቱ ስፋት መታወቂያ በመሆኑ፣ ሕዝባችን ላሳየው ጀግንነት፣ ቆራጥነት፣ ከሁሉም በላይ ዐማራዊ ማንነቱን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ለንቅጦ፣ ለአገራችን ዳግም ትንሣኤ የለኮሰው የለውጥ ችቦ እኛ  በውጭ በስደት የምንኖረውን ልጆቹን አኩርቶናል።

ጎንደር፣ የኢትዮጵያ አንድነት ሲቋጠርበት እና ሲፈታበት የኖረ ታሪካዊ ምድር ነው። ዘመነ መሣፍንት የተጀመረው የትግሬው ራስ ሥዑል ሚካኤል በጎነጎነው ሤራ አማካኝነት በአገራችን በተከለው የእርስ በእርስ ጦርነት ከዚሁ ጎንደር ላይ ነው። ይህ ሤራ አገራችንን ለ70 ዓመታት ያህል ማዕከላዊ አመራር አሳጥቶ፣ ሕዝባችን እርስ በርሱ እንዳጫረሰ ይታወቃል። ይህ የብላ ተባላና፣ የፍዳ ዘመን የተቋጨውና የኢትዮጵያ አንድነት የተቋጠረው፣ ከዚሁ ጎንደር ውስጥ ከቋራ በበቀሉት፣ በአባ ታጠቅ ካሣ (ዳግማዊ ዐፄ ቴዎድሮስ) በተመራው ፀረ-ዘመነ መሣፍንት እንቅስቃሴ ነው።

ከ1520 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1535 ዓ.ም. ድረስ በክርስትና ሃይማኖትና በፍትሐ ነገሥት ላይ የተመሠረቱን ዕሴቶችን አጥፍቶ አረባዊ ማንነት ለማለበስ የተነሳው ግራኝ አሕመድ፣ ለ15 ዓመታት ያህል አገሪቱና  ሕዝቡን ለማጥፋት ያደረገው ጥረት፣ የተገታው ጎንደር ላይ፣ ዘንተራ፣ ደጎማ ሥር በተደረገ ጦርነት ላይ ነው። ይህ በጎንደር ምድር በግራኝ ላይ የተገኘው ድል ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት ማንሰራራትና መቀጠል ዋስትና ሆኖ ማገልገሉ ግልጽ ነው።

ልክ እንደዛሬው የትግሬ-ወያኔ ኢትዮያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት እንደሚያደርገው ሙከራ፣ ከ1928 ዓ.ም. እስከ 1936 ዓ.ም. የጣሊያን ፋሽስት ኢትዮጵያውያንን በነገድ ከፋፍሎ ለመግዛት ሞክሮ ነበር። ሆኖም የፋሽስት ጣሊያኖች ቅዠት ለመጨረሻ ጊዜ ላይመለስ ያከተመው፣ ጀግኖቹ የጎንደር አርበኞች፣ ጎንደር ላይ መሽጎ በነበረው የጄኔራል ናዚ ጦር ላይ፣ በሣንቃ በር፣ በቁልቋል በር፣ በሊማሊሞ፣ እና በጭልጋ ሰራባ ላይ በተጎናጸፉት ድል ነው። ይህም የኢትዮጵያን ነፃ አገርነት እንዲረጋገጥ ወሣኝ ሚና የተጫወተ እንደሆነ ይታወቃል።

በሌላ በኩል ወያኔ ለ17 ዓመት በትጥቅ ትግል የቆየው ትግራይና ጎንደር ክፍለ-ሀገሮች ውስጥ መሆኑ ይታወቃል። በ17 ዓመቱ ግብግብ ጎንደር አያሌ ጀግኖቹን አጥቷል። የደርግ አገዛዝ በሕዝቡ አመኔታ ሲያጣ፣ ወያኔ ዲሞክራት መስሎ በአስተጋባው ፕሮፓጋንዳው፣ «ከደርግ የከፋ አይመጣም» በሚል የሞኝና አርቆ ካለመሳብ በመጣ ችግር፤ ወያኔ ባገኘው ድጋፍ ተበራቶ፣ ጎንደር ከተማን እንደያዘ፤ ማዕከላዊ መንግሥቱ በሥልጣን ላይ ለመቆየት የቻለው ሁለት ወራት አይሞላም። የጎንደር በወያኔ እጅ መውደቅ፣ ለኢትዮጵያ መበታተን ፈር ቀደደ። ስለዚህ ሰሞኑን፣ ጎንደር ላይ የተጀመረው ሕዝባዊ አመጽ፣ ያለፉት ታሪኮቻችን ፈለግ ተከታይ በመሆኑ፣ የአገራችን የአንድነት ትንሣኤ ብሥራት እንደሆነ በልበ ሙሉነት ታሪክን ነቃሽ በማድረግ መመስከር ይቻላል። በመሆኑም ዛሬም ዘረኛውን የትግሬ-ወያኔ ቡድን ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ አሽንቀንጥሮ ለመጣል፣ ጎንደር ላይ የተለኮሰው የለውጥ እሣት፣ ወያኔን ለብልቦ፣ የአገራችን አንድነትና የሕዝባችን ዕውነተኛ በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሠረተ ነፃነትና ዕኩልነት እንደሚያጎናጽፈን ጥርጥር የለንም።

ጥሪ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፦ በትግሬ-ወያኔ አገዛዝ በግፍ የተገደሉ ወገኖቻችን ደም ደመ-ከልብ ሆኖ የማይቀረው የሕይዎት መስዋዕትነት ከፍለው ያቀጣጠሉትን የነፃነት ትግል ወደፊት ስንገፋ ብቻ ነው። የትግሉም የመጀመሪያ ግብ እያንዳንዷ የኢትዮጵያ ግዛት ከግፈኛው የትግሬ-ወያኔ አገዛዝ ነፃ እስክትወጣ ድረስ መሆን ይኖርበታል። በትግሉ ወቅት ለወደቁ ኢትዮጵያዊ ሰማዕታት፣ በስማቸው መንገዶች፣ ትምሕርት ቤቶች፣ እና የመታሰቢያ ሐውልቶች ልናቆምላቸው ይገባል።

በዚህ አጋጣሚ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት፣ ላለፉት አራት ዓመታት፣ የዐማራው ድምፅ እንዲሰማ ያደረገው ጥረት፣ ሰሚ ጆሮ እና አዳማጭ ኅሊና ያገኘ መሆኑን፣ ከጎንደር ሕዝባዊ አመጽ ለማረጋገጥ በመቻላችን፣ ልፋታችን የበለል አለመቅረቱን እንድንገነዘብ አድርጎናል። ይህም የተያያዝነውን የዐማራን ኅልውና እና ማንነት የማስጠበቅ ትግላችን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እያረጋገጥን፣  እስካሁን በቀጥታ የትግሉ አካል ያልሆኑ አካባቢዎች ትግሉን በፍጥነት እንዲቀላቀሉ ጥሪያችን እናቀርባለን።

ዐማራን ከፈጽሞ ጥፋት እንታደጋለን!

ዐማራነታችን የማንነት መገለጫ መታወቂያችን፣ ኢትዮጵያዊነት ኃይማኖት ማተባችን ነው!

ፈለገ-አሥራት የትውልዳችን ቃል ኪዳን ነው!

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ