ከሰሃራ በታች ሀገር አለኝ ማለት

ከሰሃራ በታች ሀገር አለኝ ማለት በዳግማዊ ጉዱ ካሣ

ከሰሃራ በታች ሀገር አለኝ ማለት

ዋ! ብሎ መቅረት ነው ትግሬ የገዛ’ለት፡፡

የሚል ባህላዊ የዘፈን ግጥም ትዝ አይላችሁም? ትዝ እንደሚላችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ትዝ ባይላችሁ ደግሞ የዱሮን ነገር የመርሳት ሁኔታ ላይ ናችሁ ማለት ነው፡፡ ለማንኛውም ሀገራችሁ በመጥፋት ሁኔታ ላይ መገኘቷን ለአፍታም እንዳትዘነጉ ያህል አሁን በቀድሞዋ ኢትዮጵያ የሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ከእንቅልፌ ነቅቼ – እኚህ ነቀዞች እንቅልፍም እኮ እኮ ከለከሉን እናንተዬ – አዎ፣ እምቢ ካለኝ እንቅልፍ ተስፈንጥሬ በመነሣት ብቻየን ተጎልቼ አንዳንድ ነገር ልነግራችሁ የምችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ይሄኔ አብዛኛው ምድረ አበሻ ተጋድሞ እንቅልፉን ይለሽልሻል፡፡ ወይ ወያኔ! ደርጎች የጃቸውን አይጡ፤ ለነዚህ እርጉሞች አሣልፈውን ሄዱ፡፡

ወያኔ በዕቅዱ መሠረት ሀገር የማጥፋቱን ሥራ በስኬት እያጠናቀቀ መሆኑን በጥቂት ወቅታዊ መረጃዎች እንመልከት፡-

ብዙ ዩኒቨርስዎች ትምህርት አቁመዋል፡፡ ለምሳሌ ከደብረ ብርሃን አካባቢ የሰማሁት የቅርብ ሰዓት ሰበር ዜና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ መምህራን የማስተማር ሥራቸውን እንዳልጀመሩ ታውቋል፡፡ ተማሪዎች ቢገኙም አስተማሪዎች ወደ ክፍል አይገቡም ወይም የመምህር ዕጥረት ሊኖር እንደሚችል ተገምቷል – ብዙ ቦታ ይህ (የብቁ) መምህራን ዕጥረት አለ ይባላል፡፡ ዋናው ነገር ግን ሁለተኛው ሴሚስተር ከተጀመረ አምስት ሣምንታት ቢያልፉም ከወለም ዘለም ውጪ የሚታይ ዕርባና ያለው ነገር የለም እየተባለ ነው፡፡

አንድ መምህር ባለ ሦስት ክሬዲት አወር ትምህርት እንዲያስተምር ሲመደብ ወደ ክፍል የሚገባው በሣምንት አንዴ ይሆንና ከዚያም ውስጥ ትምህርት በተጀመረ በሦስተኛው ሣምንት አካባቢ ለ10 ደቂቃ ያህል የኮርሱን ቢጋር (ኮርስ አውት ላይን) “አብራርቶ” ከክፍል ይወጣል፡፡ በቀጣዩ ሣምንት የጫት ምርቃና ተከታይ በሆነው ሃንጎቨር ምክንያት ይቀራል፡፡ በሌላው ቀጣይ ሣምንት ለሃያ ደቂቃ ያህል “ያስተምር”ና ሲጃራ ለመጠጣት እያዛጋ ከክፍል ወጥቶ ይሄዳል፡፡ እያለ እያለ ይልና … በሴምስተሩ ማገባደጃ ላይ የኮርሱ ምዕራፎች በቅጡ ሳይሸፈኑ ተማሪዎች ለፈተና እንዲዘጋጁ ይነገራቸዋል፡፡! ከዚያም ይፈተኑና “ይታረም”ና ውጤት ይለጠፍና ኤና ቢው በሎተሪ መልክ ለቀረበ ተማሪ፣ ሲና ዲው በጠበል መልክ ለተሣታፊው ይረጫል፡፡ … ከዚያም ምረቃ ደርሳል፡፡ ባልተማሩ መምህራን ያልተማሩ ምሩቃን ጋውን ይለብሱናም መነሳነሳቸውን ከአናት ወደግርጌ ያነሳሉ፡፡ ተመረቁ ይባላል፤ ሥራ ፈልገው የሚያገኙት በቀድሞዎቹ የስድስተኛና ስምንተኛ ክፍል ምሩቃን እንደገና እየሠለጠኑ ሥራውን ይለማመዳሉ – በሁሉም የሙያ ዘርፍ ነው ታዲያ፡፡

ይህ ዓይነቱ አሠራር በትግራይ ውስጥ ተግባራዊ ይሁን አይሁን አላውቅም፡፡ በሌሎች ግዛቶች ግን በአብዛኛው እንዲህ ያለ ወይም ወደዚህ በእጅጉ የቀረበ ሼክስፒራዊ ድራማ በብላሽ አለክፍያ እየታዬ ነው – ለነገሩ በነፃ አይደለም፤ ኢትዮጵያ በውድመቷ ስፖንሰር አድርጋ ከባድ ዋጋ እየከፈለችልን ነውች፡፡ በአንጻራዊ ሁኔታ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቢያንስ በ“አቴንዳንስ” ደረጃ ሳይሻሉ አይቀሩም፡፡ የጥራቱ ነገር ግን የሚነሣ አይደለም፡፡ ሀገርና ወገን የሚባል አስተሳሰብ ከሀገር በመሟጠጡ በእውነተኛ ብሔራዊ ስሜት ትውልድን የመቅረጽ ኃላፊነት የሚሰማው የትምህርት ሥርዓትና ተጓዳኝ አንቀሳቃሽ ኃይል የለም፡፡

አብዛኛው ሆድ አደር በመሆኑ፣ በዚያም ላይና በዋናነት የሙያ ሥነ ምግባርም ሆነ የሙያ ዕውቀትና ችሎታ ከሀገር ስለሸፈቱ ትውልድ በፓንጋ(በሜንጫ) እየተረፈረፈ ነው፡፡ የሚያስጨንቀው አቢይ ነገር በሰው አምሳል የሚንቀሳቀስ አጥፊ ሮቦት ሀገር ምድሩን ከወረረውና የጥፋት ተልእኮውን ከጽንፍ እስካጽናፍ ካዳረሰው በኋላ እንዴት አድርገን ኢትዮጵያን ከእንደገና መሥራት እንደምንችል ሲታሰብ ነው፡፡ ለሰው የማይቻለው ለፈጣሪ ይቻላልና እርሱው ይሁነን እንጂ አያያዛችን ሽል በእግር ዓይነት ነው፡፡ ወያኔዎች በኢትዮጵያ ማሕፀን አለደንቡ በእግራቸው የመጡ ገደቢስ ገፊዎች ናቸው፡፡ በእግሩ የመጣ ጽንስ አብዛኛውን ጊዜና ጥሩና ዘመናዊ አዋላጅ ከሌለ እናቱን ይገድላል፡፡ … ሰፊው በውጭ ሀገር ያለህ ምዕመን እንግዲህ የሀገርህን መሞት ተረዳ – ማለቴ አትርሳ!

ርሀቡ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የገጠሩ ርሀብ የታወቀ ነው፡፡ ፀሐዩ ንዳድ ሆንዋል፡፡ ቅጠልና ሣር ደርቋል፡፡ የሚላስ የሚቀመስ የጠፋባቸው አካባቢዎች ብዙ ናቸው፡፡ ወያኔ በተለይ ዐማራውን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት የተያያዘው ዘመቻ በዚህ የርሀብ አጋጣሚ ሊሣካለት የተቃረበ ይመስላል፡፡ ኢሰብኣውያኑ – ጭራቆቹ ወያኔዎች ይህን ዓይነቱን ዕድል እልል በቅምጤ የሚሉት ሰይጣናዊ ስጦታ ነው፡፡

ልትፈጀው ዘዴና ብልሃት ቀይሰህ በጥርስህም በጥፍርህም እያሳደድከው ባለኸው ሕዝብ ላይ እንዲህ የመሰለ አጋጣሚ ሲፈጠር ለዐረመኔዎቹ ወያኔዎች ፈልገው የማያገኙት ወርቃማ ዕድል ነው፡፡ ጥይት ይቆጥብላቸዋል፤ ሰይጣናዊ ዕውቀትንም ይቆጥብላቸዋል፤ ጉልበት ይቆጥብላቸዋል፤ ዓለም አቀፍ ትዝብትን ይቀንስላቸዋል፤ … ለዞረ ድምሩ ዋይታ ዝግጁ ይሁኑ እንጂ ዐማራን በመጨረስ ረገድ ወያኔዎች አሁን ብዙ የቀናቸው ይመስላል፡፡ ዐማራነቷን በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ያሟሟችውና ከኢትዮጵያዊነት የወረደ ዘውጋዊ ማንነት ያላዳበረችው ምድረ ዐማራም የሚዘንብባትን ወያኔያዊ ውርጅብኝ ሁሉ በ“አንተ ታውቃለህ” ዕድሜ ጠገብ ጸሎት ምርኩዝ በነፍስ ውጪ ነፍስ ግቢ ጣዕረ ሞት ትሰቃይ ይዛለች፡፡

በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ ርሀብ አለ፡፡ አስፋልትና መኪና፣ ሕንፃና ፋብሪካ የጥቂት ባለፀጋዎችን መንፈላሰስ ከማሳየት በዘለለ የብዙኃንን በርሀብ አለንጋ መገረፍ አያመለክትም፡፡

እናም በከተሞች በተለይም በአዲስ አበባ ትልቅ ርሀብ እየተከሰተ ነው፡፡ ጤፍ (ነጩ) 2500 ብር አካባቢ ነው – ጥቁሩ 2000 ገደማ – የሌሎች የምግብ ሸቀጦች ዋጋ አይነሣ፤ ብሩ ዜሮ ሊሆን ምንም አልቀረውም፤ ገቢና ወጪ ሰማይና ምድር ሆኑ፡፡ ብዙኃኑ በጥቂ-ትኋኑ ደማቸው በቀሰም እየተመጠጠ፣ መቅኒያቸው በስሪንጋ እየተነቀረ የቁም ሬሣ ሆነዋል፡፡ የባለስድስት መቶ ብር ደሞዝ ከሁለትና ሦስት ሕጻናት  ልጆቹና ከአንዲት የቤት እመቤቱ ጋር እንዴት እንደሚኖር አስቡት፡፡ ምን ዓይነት ድንጋይ ራስ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ፈጣሪ ለቅጣት እንደሰጠን ደግሞ አብራችሁ በዐይነ ኅሊናችሁ ቃኙት፡፡ እነሱ እንዴት እንደሚኖሩ እናውቃለን፤ የደመሞዛቸውን መጠን እናውቃለን፤ በንግድና በሙስና የሚዘርፉትን በሚሊዮንና ከዛም ባለፈ ያላቸውን ሀብትና ገንዘብ እናውቃለን፤ ደሞዛቸው ለይስሙላ እንጂ በርሱ እንደማይኖሩ እነሱ ብቻ ሣይሆኑ እኛም እናውቃለን፤ … የድንጋይነታቸው ብዛት እዚህ ላይ ነው፡፡

በዚህ የጦፈ የኑሮ ውድነት – በዚህ እናትና ልጅን በሚያባላ የሕይወት ምስቅልቅሎሽ – በዚህ ለትራንስፖርት ብቻ እንኳን የሚወጣው ከአንድ አነስተኛ ደሞዝ የሚበልጥ በሆነበት እሳት ዘመን የሠራተኛውን ኑሮ ለምን ማየት እንዳልቻሉ ይገርማል – በበኩሌ “ሚኒስትሮቻችን” ሰዎች ስለመሆናቸው እጠራጠራለሁ፤ “መሪዎቻችን” እንደኛው ከሰው ደምና ጅማት ስለመሠራታቸው እጠራጠራለሁ፤ “መንግሥታችን” የአጋንንት ስብስብ መሆኑን ለማይረዳ ወገን በርግጥም የነዚህ “ሰዎች” ተፈጥሮ በእጅጉ ሳያስደነግጠው አይቀርም፡፡ የሆኖ ሆኖ    አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ በርሀብ እያለቀ ነው – ከሙሰኞች በስተቀር ሌላው በርሀብ አንጀቱ እየታጠፈ ለልመናና ለአልባሌ ድርጊቶች እየተጋለጠ ነው፡፡ ወንዱ ለስርቆትና ለዝርፊያ፣ ሴቱ ለሽርሙጥናና መሰል የማኅበረሰብ ነቀርሣዎች እየተዳረጉ ነው – እንዴ፣ ኧረ ወንዶችም … ገብተውበታል እየተባለ ነው! ኢትዮጵያን ለማርከስ ቆርጦ የተነሣው የወደቀው መልአክ የሚሣነው ምን ነገር አለ? ወዲህም አለ ወዲያ የርሀቡ ጦርነት አዲስ አበባን እያመሳት ነው፡፡ ሥራና የገቢ ምንጭ ያለውም እየተራበ ነው እያልኩ ነው፡፡

አንድ መምህር እንዲህ ሆነ፡፡ በሚያስተምርበት ክፍል ልጆች “ፌይንት” እያደረጉ ይወድቃሉ፡፡ መምህሩ ይጨነቃል፡፡ አሰበ፡፡ “ርቧቸው ይሆን?” ብሎም ገመተ፡፡ ባለችው ውሱን ገቢ ዳቦና ሙዝ እየገዛ ሲያቀምሳቸው ደህና ይሆናሉ፡፡ እንዲህ እያደረገ ጥቂት ቀናትን ገፋ – (ባይገርማችሁ እርሱ ራሱም እኮ ርሀብተኛ ነው፤ በመምህር ደሞዝ የትኛው የተመጣጠነ ምግብ ይሟላል? በሊትር የ20 ብሩን ወተት በህልሙ ካልጠጣ፣ በኪሎ በትንሹ የ250 ብሩን ሥጋ በቅዠት ካላኘከ፣ ኪሎው 50 ብር የደረሰውን ብርቱካን በቅብዥር ካልበላ … በስተቀር እመኑኝ ይህ ሰው እንደኔ ርሀብተኛ ነው!)፡፡

አንድ ቀን ታዲያላችሁ ልጆቹ ሲዝለፈለፉበት በኪሱ ዱዲም ስላልነበረው አምርሮ አለቀሰና ዕድሉን ተራገመ – ክፍል ውስጥ፡፡ ያቺን ክፍለ ጊዜ ሳይጨርሳት የማስተማር ሥራውን ወዲያዉኑ በመተው ግቢውን ለቅቆ ወጣ፡፡ “አእምሮየ እንዲህ እየተሰቃዬ የምበላው እንጀራ በአፍንጫየ ይውጣ!” ብሎ የትሚናውን ሄደ፡፡ … በብዙ ትምህርት ቤት ያለው እውነታ ይሄው ነው – በብዙ ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም በወላጆችና መምህራን ተዘርግቶ ድሆች ልጆች ምሣ ይመገባሉ፡፡ እንደአጠቃላይ እውነታ ግን አብዛኛው ተማሪና ምግብ ተለያይተዋል፡፡ ወላጅነትና ልጅን በወግ በማዕረግ አሳድጎ መዳርና መኳል  ዐይንና ናጫ ሆነዋል፡፡ ዛሬ ያለው በዕድል ማደግ ነው፡፡

ወያኔዎች የትምህርትን ዋጋ ከዜሮ በታች ስላዋሉት ለመማር የሚተጋው ዜጋ ቁጥር እጅግ ጥቂት ነው – መስረቅና መዝረፍ፣ መቅጠፍና ማጭበርበር፣ በዘር ተቧደኖና በሃይማኖት ተደራጅቶ ሕዝብን መንጨት፣ በፎርጅድ ዲግሪ መምበሽበሽና በዚያም ያለተቆጣጣሪ በተለይ ባለቤት የሌለውን የመንግሥትን ሥራ መያዝ … እንደጽድቅ … እንደግምቢ ባህል እንዲታይ በመደረጉ ትውልድ ካላንዳች ቦምብና ጥይት … ካላንዳች መትረየስና ባዙቃ … ካለምንም የኒኩሌር መሣሪያ በወያኔያዊ ትውልድን የማምከን ትልቅ “ጥበብ” የሀገር ወረደ መቃብር እየተፈጸመ ነው – ልብ አድርጉ! የምነግራችሁ በስማ በለው ያገኘሁትን ሸፋፋ መረጃ ሳይሆን ራሴም በውስጡ ያለሁበትን እውነተኛ ሀገራዊ ዘግናኝ ክስተት ነው፤ ይህ ሥዕል አጠቃላዩ እውነተኛ የሀገር ምስል  ሲሆን እዚህና እዚያ ሊታዩ የሚችሉና የምገልጥላችሁን እውነት ሊያስተሃቅሩ የሚሞክሩ ተቃራኒ እውነቶች ቢኖሩ ከንፍሮ ጥሬ የማግኘት ያህል እንጂ ዋናውን ሀገራዊ ምስል አይለውጡም፡፡ እንጂ በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ወይም በናዝሬት የሴቶች ትምህርት ቤት ከሚማሩ ልጆች መካከል ተስፋ የሚጣልባቸው ዜጎች አናገኝም ማለት አይደለም – እንዲያም ሆኖ ግን ከሞላ ጎደል የሁሉም ዜጋ ምኞትና ፍላጎት በተቻለው አቅም ሀገሪቱን በባሌ ወይም በቦሌ ለቅቆ መውጣት ስለሆነ እዚህ ላይ የምለው ነገር ሀገሪቷን ስለመጥቀሙ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ሁሉም ሰው በመንፈስ ሸፍቷል፤ ሰውነቱ ሀገር ውስጥ ቢገኝም ልቡ አውሮፓና አሜሪካ ነው፡፡ ደርግና ወያኔ ምሥጋን ይንሳቸውና ኢትዮጵያ የወላድ መካን ሆናለች፡፡

ነቃ ነቃ ያለው ዜጋ አንጋጦ ተስፋ የሚያደርገው የተስፋይቱን ምድር አሜሪካንን ነው፤ ኢትዮጵያን ከነመፈጠሯም ረስቷል፡፡ በወያኔና ወያኔን ከነሙሉ ትጥቁና የጥፋት ጓዙ ጃዝ ብለው ባሠማሩት ወገኖች ዘንድ የሚፈለገው ደግሞ ይሄው ነው፡፡ ኢትዮጵያን የማጥፋት ህልም አንግበው የተነሡ ታሪካዊ ጠላቶቿ በአሁኑ ወቅት ጽዋቸውን እያጋጩ እንደሆነ በምናቤ ይታዩኛል፡፡ ለማንኛውም ርሀብ ጊዜ አይሰጥምና ርሀቡን ብቻ ሣይሆን የርሀቡን መንስኤ ወያኔን በማጥፋት የጋራና የእኩል ሀገር እንድትኖረን እንጣር፡፡ የጸሎት ኃይል ከሁሉም ጦር ይበልጣልና ወደፈጣሪ ተመልሰን የተገፈፍነውን ፀጋ እንድንላበስ እንለምነው፡፡ በሰው ብቻ አንመካ፡፡ ሰው ደካማ ነው፡፡ ሰው ሟች ነው፡፡

ሰው ወዳቂና ሲለውም ውዳቂ ሆኖ የሚገኝ ዕቡይ ነው፡፡ ሰው ባስቀመጡት የማይገኝ ተንሸራታች ፍጡር ነው፡፡ ሰው ተለዋጭና ተለዋዋጭ  ነው፡፡ በጥቅም ይለወጣል፤ በአስተሳሰብና አመለካከት ይለወጣል፤ በዘርና በሃይማኖት ይሳባል፤ እናም ይለወጣል፤ ሰው ጤናማ አእምሮውን በተለያዩ አደጋዎችና አስገዳጅ ሁኔታዎች ሊነጠቅ ይችላል፡፡ ስለዚህ የምናምን ሰዎች ፈጣሪን የሙጥኝ ብለን እንጠይቀው፡፡ ለነሱ የሰጠውን ዲያብሎሣዊ አፍራሽ ኃይል ቀምቶ ለኛ መለኮታዊውን ግምቢ ኃይል ሊያጎናጽፈን ይችላል፡፡ ለቅጣት የታዘዙብን ዓመታት ሊያጥሩልን የሚችሉት በዐመፃ ተግባራችን በመቀጠል ሣይሆን ከነውር ተግባራችን በመመለስና በመፀፀት ለፈጣሪ ትዕዛዛት – ለጤናማ ኅሊና መርኆዎችም ጭምር – በመገዛት ነው፡፡  ሃይማኖት ባይኖረን እንኳን ክፉንና ደግን መለየትና ከሕጻናት የበለጠ ማሰብ የሚያስችለን ጭንቅላት ተፈጥሮ አድላናለችና ያን በመጠቀም ቀና ቀናውን እናስብ፤ እንመኝም፡፡

ኦሮምያ የሚባል ሀገር የለም – “ይሄኔ ነው መሸሽ!” የምትሉ አንባዎች እንደምትኖሩ ከቅርብ ጊዜው ውሽልሽል ታሪካችን በመነሣት መገመት አይከብደኝም – ግን እውነቱን መናገር ስላለብኝ ነው፡፡ ውሸት ከአሁን በኋላ በተለይ አይጠቅመንም፡፡ እያለባበሱ ማረስም አረሙ ሲወጣ መንቀሉ ዕዳ ነው፤ ሰውን በቃላት ማስደሰት ወይም ማሳዘን እንደሚቻል ግልጽ ነው፡፡ እውነትን በመሸፈን የሚገኝ ደስታ ግን ጊዜያዊና የጉሽ ጠላ ስካር የሚሉት ዓይነት ነው፤ በዚህ ውስጥ ብዙ ዳከርንበት – የተገኘ እውናዊ ለውጥ ግን የለም – ድፍን ግማሽ ምዕተ ዓመት ሆነን ሌባና ፖሊስ ስንጫወት፡፡ ለኔ ቁልጭ ብሎ እንደሚታየኝ ከአሁን ወዲያ ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ የሚገነባው በመለማመጥና በይሉኝታ እንደማይሆን ስድስተኛው ሕዋሴ ይነግረኛል፡፡ ለማንኛውም የፈለግኸውን ስም ልትሰጠኝ ትችላለህ፡፡ አማሪያም ሆነ ትግሪያ የሚባል ሀገርም የለም፡፡ ይህን እውነት ማንም ወገን ሊረዳ ይገባዋል፡፡

ጠላት በቀደደልን ቦይ እየፈሰስን የሀገራችንን ቁስል አናነፍርቅ፡፡ እርግጥ ነው ሁሉም በጊዜው መስተካከሉ የማይቀር እንደሆነ መጠቆሙ የዐዋጅን በጆሮ እንደመንገር ነው፡፡ ዛሬ በዘረኝነት አበሾ አዳሜ ሰክሮ ቢወላገድ ነገ ጧት እውነት ቦታዋን ስትይዝ በስካራችን ጡዘት ባደረግነው ጠያፍ ተግባር እንጸጸታለን፡፡ ስለዚህ ከትዕቢትም በሉት ከዕብሪት መቆጠብና ወደኅሊና መመለስ ተገቢ ነው – ብዙም ሳይረፍድ፡፡ “ፍቅር ያዘኝ ብለሽ አትበይ ደምበር ገተር፤ እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አር’ጎን ነበር” የሚሏትን ባህላዊ ግጥም ማስታወስ ይገባል፡፡ አንዳንድ ሰው ይገርመኛል – ቀፎ ነው፡፡

የራሱ የሚለው የሌለው የገደል ማሚቶ ነው፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን ኢትዮጵያን ለማጥፋት ያሤሩና ለጊዜው የተሣካላቸው የሚመስሉት ታሪካዊ ጠላቶቻችን በቤተ ሙከራቸው እየፈበረኩ በሚያከፋፍሉን ሀገር አፍራሽ ዘይቤ መጠለፍ አልነበረብንም፤ በየትም ሀገር እንደሚታየው ሁሉ በመካከላችን በደልና ጥፋትም እንኳን ቢኖር እርስ በርስ መተራረም እንጂ የጋራ ጎጆን ነቅንቆ እስከማፍረስ ወደሚደርስ የጠላት ተንኮል ልባችንንና መላ ትኩረታችንን መስጠት አይገባንም ነበር – “ይሁን ግዴለም”ን በዘለለ ሰቅጣጭ ሁኔታ አንዴ ተሳስተናል፤ ከአሁን በኋላ ግን መሳሳት አይኖርብንም፡፡

ነገር ግን አያርመን ብሎ – ለመብል መጠጥም ይሁን ለልዩ ዓላማ ስኬት ብለን በስህተታችን ብንቀጥል የእስከዛሬው ሞኛሞኝ ታሪክ አይደለም የሚበቀለን – እኛ ታላላቆች በፈጠርነው እሳት ክፉኛ የተለበለበውና መቆሚያ መቀመጫ ያሳጠነው ቀጣይ ትውልድ ድራሻችንን ከማጥፋት አይመለስም፡፡ ባሏን የጎዳች መስሏት የገዛ ሰውነቷን በጋሬጣ እንደቧጨረችው ገልቱ ሴት ሆነን በተለይ ላለፉት 25 ዓመታት ራሳችንን በጦርና በጎራዴ ስንመትር ቆየን፡፡ አሁን አይበቃንም ታዲያ? ምን እስክንሆን ነው የምንጠብቀው? በዚህች አንቀጽ አነሳሴ ኦሮሚያ የሚባል ሀገር የለም የሚል ነበር፡፡ ይህ ስያሜ መቼና በማን እንደተፈጠረ ፣ ለምን ዓላማ እንደተፈጠረ … ብዙ ስለሚያናግር አንገባበትም፡፡ ለምን ወደዚህ ርዕሰ ጉዳይ እንደገባሁ የሚጠቁም አንድ ትዝብት ግን ላስቀምጥ፡-

በቅርብ ጊዜ ነቀምት ላይ አንድ ሠርግ ላይ ተገኘሁ – በተዛዋሪ፡፡ አስገራሚ ሠርግ ነው፡፡ በዚያ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች በታደሙበት ሠርግ ላይ አንድም የዐማርኛም ሆነ የትግርኛ ወይም የሌላ ብሔር/ብሔረሰብ ሙዚቃ እንዲዘፈን አልተደረገም ማለትም አልተፈቀደም፡፡ አለመዘፈኑ የምርጫ ጉዳይ ስለሆነ ምንም አይደለም ሊባል ይችላል፡፡ መጥፎነቱ ግን መልእክቱ ነው፡፡ አንጀት በጣሽ መልእክት ነው የተላለፈው በዚያ ሠርግ – የማዕቀቡም ዋና ዓላማ ይሄው ነው፡፡ ሕዝብን ከሕዝብ ማቆራረጥ ነው ዓላማው፡፡ ያን ያደረገው አንድ ወይ ሁለት ሰዎች ቢሆኑ ነው፡፡ እነዚያ ሰዎች ጥረታቸው የኦሮሚያን ኑባሬ ማግነንና ሌሎችን ማስረሳት ወይም ማስጠላት ነው፡፡ በዚያ ሠርግ ላይ “ሙሽራየ” ወይም “አምሯል ሸገኑ” ቢዘፈን “ኦሮሚያ” አትዋረድም ወይም አይዋረድም – በምን ፆታ እንደሚጠቀሙ አላውቅም – የጀርመን ተፅዕኖ ካለባቸው ወንድ መሆን አለበት(በነገራችን ላይ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ኦሮሞ ያልሆነ ሰው ይኖር ይሆን? ዐይናችሁን ጨፍኑና እስኪ ለጥቂት ጊዜ አስቡ፡፡

እናሳ የቱ ነው ኦሮሚያ የቱስ ነው “ኢምፓየሩ”? “ሲነጋ ለማፈር!” አሉ እመት ብርጣሉ!)፡፡ የሆኖ ሆኖ ያ የጉሽ ጠላ ጰራቅሊጦሳዊ የዘፈን ዕቀባ ስሜታዊ እንጂ ምክንያታዊ እንዳልነበር አንዳንዶች አጉርምርመዋል፤ በዚህ መልክ የትም አይደረስም፤ ሰውን በፍቅር ልታቀርበው እንጂ በጥላቻ ልታርቀው አይገባም፡፡ የዘመናት የታሪክ ሽመና የተሣሠረን ሕዝብ በዘመን አመጣሽ ወያኔያዊ ሽብልቅ መሰነጣጠቅ እንደማይቻል እፍኝ የማይሞሉ ነውጠኞችን ሣይሆን  የብዙኃኑን መስተጋብራዊ ሕይወት በመመልከት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በተረፈ ዝርዝሩን በነገይቷ ከወያኔና መሰል ጎጠኞች ነፃ የሆነች ኢትዮጵያ በግልጽ የምናየው ይሆናል፡፡ (በነገራን ላይ አዲሲቱ “የጎረቤት ሀገር” ኤርትራ ላይ –  አሥመራ ውስጥ ከአሥር ዘፈኖች ሁለትና ሦስቱ ዐማርኛ መሆኑን በኢሳት አንድ ዝግጅት ተረድተናል፡፡ ስለዐማርኛ የተቆረቆርኩ እንዳይመስላችሁ – ስለኢትዮጵያ እንጂ፡፡ ዐማርኛ ደግሞ የዐማሮች ቋንቋ ሣይሆን የኢትዮጵያውያን ነው፡፡ ዐማርኛን መናቅ ኢትዮጵያን መናቅ ነው – ዐማሮችማ ከታወጀባቸው ዘርን የማጽዳት ወያኔያዊ ዐዋጅ ገና መቼ ተላቀቁና ስለቋንቋ ጉዳይ ይነጋገራሉ? “ጽድቁ ቀርቶብኝ…” እንዲሉ ነው፡፡)

ለነገሩ ምን ብዙ አስለፈለፈኝ? እንዲያው ተናደድ ቢለኝ እንጂ ሁን ያለው ከመሆን አይዘልም፡፡ ሁሉም ግን ሆኖ ያልፋል እንጂ እንደሆነ አይቀርም፡፡ መሆንና አለመሆን የሞትና የሕይወት ያህል ቁርኝት ያላቸው ጓደኛሞች ናቸው፡፡ ይህ ጉድፋምና ዕድፋም ዘመን ወደታሪክ ጥቁር መዝገብ ሊገባ የቀረው ጊዜ በጣም ኢምንት መሆኑ ያስታውቃል – እጅግ ምናልባት ከአምስት ዓመት በታች! የጨለማው ዘመን ሲያልፍ ወርቃማው ዘመን ይብታል፡፡ ካልሞትን ያኔም እንገናኛለን፡፡

ልብ አድርጉ! “የናቁሽ ሁሉ እግርሽ ሥር ተደፍተው ይሰግዱልሻል” የተባለው በሥውር ለኢትዮጵያም ነው፡፡ አሁን መናገር አልፈልግም፡፡ ግን ኢትዮጵያን የሚሠሩ ጀግኖች ታዘዋል፡፡ በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ይበሠራል፡፡ ልዑል እግዚአብሔር እንደተደበቀ የቀረበት የመከራ ዘመን በየትም ሀገር አልታየም፤ ችግሩ የርሱ የጊዜ ቀመርና የኛ የምድራውያን ሰዎች የጊዜ ቀመር በእጅጉ መለያየቱ ነው፡፡ በሌላም በኩል ችግሩ የኛ ወደርሱ ከልብ አለመቅረብ ነው፡፡ ሰውነታችን ቤተክርስቲያን ደጅ ተነጥፎ ያረፍዳል – አብዛኞቻችን ግን እንዴት እንደ፣ጸለይ እንኳን አናውቅም፡፡

በደለን የምንለውንና የምንጠላውን ሰው “ልቡን አራራልኝ” እንደማለት “በወር ውስጥ ደፍተህ ተዝካሩን አብላኝ!” እንላለን፡፡ ጌታ ስንቱን ደፍቶ ይጨርሰው? ለቁልቢ ገብርኤል በስለት ቅማልና ዐይጥ ይዘን እየሄድን ከፈጣ ጋር እንዴት ዕርቅ ልንፈጥር እንችላለን? እረኞቻችንስ በዚህ በመከራ ዘመን የት አሉ? ዋናው እረኛ የዲያብሎስ አሽከር የሆነበት ምክንያት ከዘላለማዊው የእግዚአብሔር መንፈስ ይልቅ አላፊና ጠፊው የሥጋ ፈቃዱ የዘረኝነት ሰይጣናዊ ልማዱ በልጦበት አይደለምን? ያሣፍራል፡፡ ለዚህም ነው ቫቲካንን ጨምሮ ብዙዎቹን የሃይማኖት ተቋማት የጥልቁ ባሕር ገዢ በእጅ አዙር እንደተቆጣጠራቸው የሚነገረው፡፡ በዚህ ሁኔታ ፈጣሪ ፊቱን ባይመልስልን እንዴት ልንፈርድበት እንችላለን ታዲያ? በቆሻሻ ቱቦ ውስጥ ንጹሕ ውኃ ሊያልፍ አይገባም፤ በቆሸሸ ልብ ውስጥ ፈጣሪ ማደሪያ ቤት አያዘጋጅም፡፡ ስለዚህ ጥፋቱ በዋናነት ከኛው ነው፡፡ “ቤታቸውን ክፍት ትተው ሰው ሌባ ይላሉ” ይላሉ ወጣቶች በአዲስ ተረታቸው፡፡ እውነት ነው፡፡

ለማንኛውም ያልታመመ ጤነኛ፣ ያልሞተ በሽተኛ፣ ያልደኸዬ ከበርቴ፣ ያላረጀ ጎረምሣ፣ ያልመለጠ ጎፈሬ፣ ያልሸበተ ኮበሌ፣ ያልጎበጠ ሸበላ፣ ያልከሰመ ወዘና… በየአካባቢያችሁ ፈልጉና ካገኛችሁ በርግጥም ኢትዮጵያም እንዲህ እንደሆነች ትቀራለች ብዬ ልመናችሁ፡፡ የነገ ሰው ለመሆን ከወረት ንፋስ፣ ከዘመን አንከሊስ ራሳችንን እንጠብቅ፡፡ የስሜት ፈረስ የትም እንደማያደርስ እንገንዘብ፡፡ ከሁሉም ከሁሉም “አገባሻለሁ ያለሽ ላያገባሽ፤ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ” የምትለዋን ነባር ምሣሌያዊ ብሂል አንርሣ፡፡ ከሁሉም በበለጠ “ሟች ይዞ ይሞታል” እንዲሉ ወያኔ ወደግባተ መሬቱ ሲጠጋ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ መዘንጋት አይገባንም፡፡ 

የነጋበት ጅብም ያገኘውን እየጠረገ ይሞታል እንጂ እንዲሁ እጅ አይሰጥም፡፡ ወያኔም መሞቱ ለማይቀረው ብዙ ጥፋት እንደሚያስከትል የታወቀ ነው፤ እልኽና ቁጪት ውስጥ ሲገቡ መናገር የሚከብድና የማያስፈልግም ወንጀል እንደሚሠሩ መገንዘብ አለብን፤ ላለመሞት የሚንፈራገጥ አንድ ነገር ያልታሰበ ጥፋት እንዳያስከትል መጠንቀቅ ብልህነት ነው፤ “ዐይቡን ሳያዩት አጓቱን ጨለጡት” ይባላልና በተለይ ያን ደግና ሩህሩህ የትግራይ ሰፊ ሕዝብ ከወያኔዎች አፍራሽ ተልእኮ በመነጠል እነዚህ ጉዶች ብቻ ለተገቢው የታሪክ ፍርድ እንዲጋለጡ ከጀግኖች ኢትዮጵያውያን ብዙ የአስተዋይነት ሥራ ይጠበቃል፡፡ ደም ደምን እንደምትጠራ የታወቀ ነው፡፡ ፍቅር ግን ሁሉንም ታሸንፋለች፡፡ እናም በሁሉም ረገድ ጥንቃቄና ብልሃት የተሞላበት ትግል ማካሄድ ተገቢ ነው፡፡ … ሌሊት ነው የጻፍኩት – አሁን ገና ከማለዳው  12፡05 ሆነ፡፡ አይዞነ – ይህን ነገር የጻፍኩት በምንም ተፅዕኖ ሥር ሆኜ አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን ከጎኔ እንደነበር በፍጹም ልቤ አምናለሁ – ከእምነት ውጪ የሚጨበጥ ማስረጃ ላቀርብላችሁ ባለመቻሌ ደግሞ አዝናለሁ፡፡ ደከመኝ…

አባይ ወዲያ ማዶ ዘመድ አለኝ ማለት፤

ዋ! ብሎ መቅረት ነው አባይ የሞላ’ለት፡