እጅግ አሳዛኝ መርዶ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ:- ንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ ወልደኢየሱስ ማረፋቸው ታወቀ

እጅግ አሳዛኝ መርዶ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ:- ንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ ወልደኢየሱስ ማረፋቸው ታወቀ

   የእዉቀት ድረገጽ ሊቁ አባታችን ንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ ወልደኢየሱስ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየታቸው ጥልቅ ሃዘን ተሰምቶናል። አባታችን ንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ “ኢትዮጵያ የዓለሙ መፋረጃ ” በሚለው መጽሃፋቸው የኢትዮጵያዊነትን ስፋትና ጥልቀት ጽፈዋል።

ሲናገሩና ሲያስተምሩ የሰማ ሰው የዚህ ዓለም ሚስጥራት ሁሉ እንደተገለጸላቸው ለማወቅ ጊዜ አይፍጅበትም። በእርጋታና በቅንነት ሲናገሩ ተሰምተው አይጠገቡም ነበር። ከመንፈሳዊ እዉቀትና ከሃገር ወዳድነትም አልፈው ስለ ሰው ልጅ እኩልነት ‘ኢትዮጵያ የዓለሙ መፋረጃ” በሚለው መጽሃፋቸው ዉስጥ አብራርተው ጽፈዋል። በነበራቸው እዉቀትና ከፍተኛ የመጻፍ ችሎታ ብዙ ጠቃሚ መጻህፍትን ለትዉልድ አበርክተዉ አልፈዋል። ኢትዮጵያ ታላቁን መንፈሳዊ ልጅዋን አጥታለች።

በህይወት ዘመናቸው በመትጋት ከትዉልድ ወደ ትዉልድ የሚተላለፍ እዉቀትን መጽሃፍትንም ሆነ ዘመናዊዉን ድረ ገጽ በመጠቀም የኢትዮጵያን ህዝብ አእምሮ በመመገብ እጅግ ብዙ ስራዎችን አከናዉነዋል።

ከእዉቀት ለቤተሰቦቻቸው ለቅርብ ዘመዶቻቸዉና ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ብርታትንና መጽናናትን ይስጥልን በማለት የተሰማንን መሪር ሃዘን እንገልጻለን። የአባታችንን የንቡረ እድ ኤርሚያስ ከበደ ወልደኢየሱስን ነፍሳቸዉን በገነት ያኑርልን። አሜን።