በመስዋዕትነት የታጀበዉ ህዝባዊ ተጋድሎ ባክኖ እንዳይቀር የተቃዋሚዎች እዳ እና ግዴታ!

በመስዋዕትነት የታጀበዉ ህዝባዊ ተጋድሎ ባክኖ እንዳይቀር የተቃዋሚዎች እዳ እና ግዴታ!

ሸንቁጥ አየለ

የአሜሪካ መንግስትን በኢትዮጵያ በስፋት እየተካሄድ ያለዉ ህዝባዊ አመጽ ወያኔን ለመተካት አማራጭ ሀሳብን ወደ መቀበል እየገፋዉ እንደሆነ ልዩ ልዩ ጠቋሚዎች አሉ:: እንዴዉም ፕሬዝዳንቱ እራሳቸዉ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉትን ነዉ የሚሉ መርጃዎችም አሉ:: አሜሪካ ሀገራት ቀዉስ ዉስጥ ሲወድቁ የወደፊት ጥቅሟን በማስላት ተቃዋሚዎችን ወደ መንበረ ስልጣን የማምጣት ትልቅ ልምድ ያላት ሀገር ነች:: ወያኔን አንከብክባ የኢትዮጵያን መንበር እንዲቆጣጠር ያደረገችዉ ከእንግሊዝ መንግስት ጋር ባደረገችዉ የተባበረ ዉሳኔ ነዉ::

ሆኖም አሜሪካ ይሄ ተቃዋሚን ወደ መንበረ ስልጣን የማምጣት ሁኔታ የማይሳካላት ጊዜም አለ::ለምሳሌ የሶሪያ ህዝብ ምድር አንቀጥቅጥ አመጽ ሲያነሳ አሜሪካ የሶሪያን ተቃዋሚዎች ሰብስባ አሳድን ማስወገድ ፈልጋ ነበር::ስለሆነም ተቃዋሚዎችን ማስታጠቅ : አብረዉ እንዲሰሩ ማግባባት ላይ ተጠምዳ ለረዥም ጊዜ ቆይታ ነበር::ግን የአሜሪካ ህልም አልተሳካላም::
ምክንያቱም የሶሪያ ተቃዋሚዎች እርስ በርሳቸዉ አብረዉ ለመስራት ፈቃደኛ አልሆኑም::

የተለያዪ ተቃዋሚዎች ወደ ተለያዬ አላማ መፍሰስ አበዙ::አንዳንዱ አሸባሪዉን አይሲስን ሲቀላቀል: ሌላዉም የተገነጠለ ሀገር ሲያልም ቀሪዉም የጎሳ ድርጅቱን በማጠናከር የተሻለ የበላይነት ያለዉ ጎሳ ላይ አተኮረ:: አንዳንዱም የአሳድን መንግስት በመገልበጥ የሶሪያን መንግስት መቆጣጠር የመረጠ ቢኖርም ሌሎች ተቃዋሚዎችን ግን ማስተባበር አልቻለም::በዚህም እርስ በርስ መጠፋፋቱ ላይ አተኮሩ:: የአሜሪካም ህልም ሳይሳካ ቀረ:: በአናቱም አሜሪካንን መጋፋት እና ማበሳጨት የሚወዱት ፕሬዝዳንት ፑቲን አሳድን መርዳት ያዙ:: መደምደሚያዉ ታዲያ ምን ሆነ? መደምደሚያዉ የሶሪያ ህዝባዊ መስዋዕትነት ባክኖ ቀረ:: አሳድም ህዝቡን እየገደለ አሁንም መምራቱን ቀጠለ::

አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ በታላቅ ጀግንነት እና ወኔ የተሞላ ህዝባዊ ተጋድሎ እያደረገ ነዉ::የጎሳ ስርዓት የሚያራምደዉ የአንባገነኑ የወያኔ ስርዓት እንዲያከትም መላዋ ኢትዮጵያ ወያኔን ወጥራ ይዛለች:: የህዝቧ ልብ በወያኔ ላይ ሸፍቷል::ይሄ ልቡ ያመጸ ህዝብ ሞት አይፈራም::ወያኔ ግን አሁንም በጅምላ መጨረሱን ቀጥሏል::ወያኔ ህዝቡን በጅምላ በጨረሰ ቁጠር እና ህዝባዊዉ ተጋድሎ እየተፋፋመ በመጣ ቁጥር አለም አቀፉ ማህበረሰብ የወያኔ መወገድ ላይ ወደ ስምምነት እየደረሰ ነዉ::

በዚህ ሂደት ዉስጥ በመጨረሻዉ ሰዓት የህዝቡን ህዝባዊ ተጋድሎ ወደ ተደራጀ እና ሰርዓት ወዳለዉ መንግስታዊ መዋቅር ሊያመጡት የሚችሉት እንዲሁም የኢትዮጵያን ህዝብ ድምጽ በአለም አቀፍ ደረጃ ሊወክሉት የሚችሉት ተቃዋሚ ሀይሎች በተወሰን ደርጃ እንኳን ለመሰባሰብ አሁንም ዳተኝነት እና እርስ በርስ ላለመግባባታ የመወሰን አባዜ ዉስጥ እየዳከሩ ነዉ::በአንድ ብሄር ስም እንኳን የተለያዬ ድርጅት የመሰረቱ ሀይሎች ልዩነታቸዉን ወደ ጎን በማድረግ ወደ አንድ ግንባር መምጣት ባይችሉ እንኳን በኔትወርክ/መረብ/ትብብር ለመስራት ፈቃደኛ አልሆን ብለዋል::

ህዝባዊዉ ተጋድሎ ከፍተኛ መስዋዕትነት ተከፍሎበት ኢትዮጵያን ላንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማሸጋገር መቻል አለበት::ይሄ የሚሆነዉ ግን ይሄን የህዝብ ትግል መስመር የሚያሲዙ ሀይሎች ሲኖሩ ነዉ::እነዚህ ሀይሎች መነጋገር እና መግባባት ብሎም ቢያንስ በመረብ አብረዉ መስራት ሲችሉ ነዉ::አለዚያ ከሚከተሉት ሶስት ሁኔታዎች ዉስጥ አንዱ በኢትዮጵያ ሊከሰት ይችላል :-

1ኛ. የአሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባዉያን መንግስታት ደርግ ሲወድቅ እንዳደረጉት ብዙሃኑን ተቃዋሚ በማግለል ከአንድ እና ሁለት ተቃዋሚዎች ጋር ብቻ ተደራድረዉ ወያኔን በመገፍተር ሌላ አንባገነን ቡድን እና የነሱን ጥቅም አስጠባቂ ሀይል ኢትዮጵያ ላይ ሊተክሉባት ይቻላሉ::ይሄንንም የሚያደርጉት ተቃዋሚዎች እርስ በርስ ሊግባቡ ስለማይችሉ ትርምስ ከሚፈጠር አንድ ሀይል ጠቅልሎ ይያዘዉ በሚል ሰበብ ይሆናል::

2ኛ. አንዱ ወይም ሁለቱ የተቃውሚ ወገን ሁሉንም ተቃዋሚ በመደምሰስ ኢትዮጵያን በቁጥጥር ስር በማድረግ እርሱ የሚፈልገዉን ርዕዮተ አለም ህዝቡ ላይ በመጫን እንዲሁም ለዉጭ መንግስታት አልጋ ለኢትዮጵያ ህዝብ ግን ቀጋ በመሆን አገሪቱን ለሌላ የሰቆቃ ዙር ሊዳርጋት ይችላል::በተለይም አንድ የብሄር ድርጅት ሁሉንም ሀይሎች ደምስሶ ብቻዉን ስልጣኑን መቆጣጠር ከቻለ አግላይ መንግስት በኢትዮጵያ ዳግም ይፈጠራል::ይሄም ሀገሪቱን እንደገና ወደ ቀዉስ እና ብጥብጥ ይመራታል::

3ኛ. አገሪቱ እራሷ ልትፈርስ ትችላለች::ሀገሪቱ የምትፈርስ ከሆነ ደግሞ አሁን አንዳንድ ተቃዋሚዎች እንደሚያንሰላስሉት የከሌ ክልል ለእከሌ: የእከሌ ክልል ለዕከሌ የሚለዉ የማይጨበጥ ጽንሰ ሀሳብ ተግባራዊ የሚሆን ሳይሆን የበለጠ ጉልበት ያለዉ ወገን ነገሮችን እንዳሰኘዉ ሊያማስላቸዉ እና ብዙ ትርምስ ሊፈጠር ይችላል::በዚህ ትርምስ ዉስጥ መላዉ ኢትዮጵያ ወደ ማይበርድ የርስ በርስ ጦርነት ሊማገድ ይችላል::

እና ከተቃዋሚዎች ምን ይጠበቃል?

1ኛ. በኢትዮጵያዊነት ተደራጅተና የሚሉት እራሳቸዉን ቢያንስ በመረብ ቢያሰባስቡ::ከሆነላቸዉም ወደ ትብብር እና ግንባር ከፍ ቢሉ::
2ኛ. በአማራነት ተደራጅተናል የሚሉትም እራሳቸዉን ቢያንስ በመረብ ቢያሰባስቡ::ከሆነላቸዉም ወደ ትብብር እና ግንባር ከፍ ቢሉ::
3ኛ. በኦሮሞነት ተደራጅተናል የሚሉትም እራሳቸዉን ቢያንስ በመረብ ቢያሰባስቡ::ከሆነላቸዉም ወደ ትብብር እና ግንባር ከፍ ቢሉ::
4ኛ. ወያኔ በዘራዉ የተንኮል ጥላቻ ምክንያት እና ለ25 አመታታ በተከሰቱ በርካታ ክፉ ሁኔታዎች የተነሳ የኦሮሞ እና የአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰፊ ልዩነት እንዳላቸዉ ይታወቃል:: ቢሆንም የዛሬዉን ልዩነት እንዲሁም የትናንቱን የተረት ተረት ጥላቻ በማለዘብ በነገ የህዝባቸዉ እንዲሁም የኢትዮጵያ መጻኢ ሁኔታ ላይ በማተኮረ በተወሰነ ደረጃ የመግባባት እና አብሮ በዉይይት የመስራት መንፈስ ቢጀምሩ::

5ኛ. በኢትዮጵያዊነት የተደራጁ የፖለቲካ ድርጅቶች የብሄር ድርጅቶችን የማግለል አሰራርን በመተዉ ከብሄር ድርጅቶች ጋር ቢያንስ በመረብ የሚሰሩበትን ከተቻለም ወደ ትብብር የሚሄዱበትን ቀመር ቢከተሉ
6ኛ. ሁሉንም ኢትዮጵያ ዉስጥ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶችን (ማንንም የማያገል) የሚያሳትፍ ቢያንስ አንድ እና ሁለት አለም አቀፍ መድረኮችን በማዘጋጀት ሀገራዊ አጀንዳዎችን በጋራ መቅረጽ የሚያስችል ስምምነት ቢደረግ::ለምሳሌ የወደፊት ኢትዮጵያ ህገ መንግስት ምን ሊመስል እንደሚገባው የጋራ ምክክር ቢደረግ

እስካሁን ልዩ ልዩ የማስተባበር እና የማቀናጀት ጥረቶች እንደተደረጉ የሚካድ አይደለም::ትብብሮቹ ግን ዋና መገለጫቸዉ እና መለያቸዉ የሚከተሉት እዉነታዎች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሆነዉ ይገኛሉ:-

1ኛ. አንዱን ወገን አግልሎ ለሌላዉ ወገን ደግሞ ከሚገባዉ በላይ የገዘፈ ቦታ የሰጠ
2ኛ. በመዋዋጥ ስልት ላይ የሚያጠነጥኑ አካሄዶችን እንደ ዋና የትብብር እና የቅንጅት መስፈርት ያስቀመጠ የሶሻሊስቶች እና የኮሚኒስቶችን አጥፊ ስልት የተካነ መሆኑ
3ኛ. ከመከባበር ይልቅ በመናናቅ አባዜ የታሸ መሆኑ
4ኛ. አንዳንዴም አንዱን ብሄር በማግለል ሌላዉን ብሄር ደግሞ እንክ እንክ በማለት የተንሸዋረረ ስልትን መከተል
5ኛ. ገና በሌለ ስልጣን ላይ የመጣላት እና የመመቀኛኘት መንፈስ የበዛበት ሁኔታ የረበበት መሆኑ
6ኛ. ሀገር ሁለተኛ አጀናዳ ግለሰቦች ግን አንደኛ አጀንዳ የመሆን ዝንባሌ መስፈን

እንግዲህ አሜሪካኖቹ አሁን 50 እና 60 ተቃውሚዎችን በመሰብሰብ ሁሉ ኢትዮጵያዉያን ተቃዋሚዎችን ያሳተፈ ሀይል በመፍጠር ወያኔን ይተኩታል ብሎ ማሰብ ቀልድ መሆኑን ማወቅ ይገባል::ወይም እንደ ሶሪያ አይነት ሁኔታ አይፈጠርም ብሎ ማሰብ አይቻልም::በግብጽም ያ ሁሉ የህዝብ ተጋድሎ ከተከናወነ ብኋላ ሰራዊቱ ሁሉንም ሀይል ቀጥቅጦ በማጥፋት ሰፊዉ የግብጾች ህዝባዊ መስዋዕትነት ያለዋጋ ባክኖ የቀረዉን እዉነት ማንሰላሰል ተገቢ ነዉ::

በመላዉ አረብ አገራት ተቃዋሚዎች ተሰባስበዉ የህዝባቸዉን አመጽ እና ተቃዉሞ ከመምራት ይልቅ እርስ በርስ በመጓትት ላይ በማተኮራቸዉ የአረብ ስፕሪንግ አመጽ እየተባለ የሚጠራዉ ህዝባዊ አመጽ በብዛት ባክኖ ቀርቷል:: አሁን ይሄን ጽሁፍ የሚያነብ አንዳንድ ተቃውሚ በልቡ ችግር የለም እኛ ወያኔን ጥለን መንግስቱን እንቆጣጠረዋለን ብሎ ሊመጻደቅ ይችላል::የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ይሄን አይነት ልበ ጠጣርነት እና ስልጣንን ለብቻ የመመኘት ሀሳብን ፈጽሞ የማይፈልገዉ እዉነት ነዉ::እናም አንድ ተቃውሚም አሸንፎ ወይም ከአሜሪካኖቹ ጋር ተደራድሮ ስልጣኑን ቢቆጣጠረዉ የህዝቡ የተጋድሎ መስዋዕትነት ባክኖ እንደቀረ እሙን ነዉ::

ይሄን ሁሉ እዉነታ በማገናዘብ ተቃዋሚዎች ያላስታራቂ: ያለ አደራዳሪ: ያለ ሽማግሌ አንዱ ወደ ሌላዉ በመቅረብ በመረብ የመስራት እርምጃ ማሳዬት አለባቸዉ::በፈጣን ሂደትም ወደ ትብብር በማደግ የምዕራባዉያን መንግስታትን ድጋፍ ለማግኘት በአብሮነት በመስራት እና ኢትዮጵያ እዉነተኛ የዲሞክራሲ ሽግግር ታደርግ ዘንድ ማስቻል አለባቸዉ::በተያያዥነትም የተገንጣይነት ሀሳብ የሚያራምዱ የተቃዋሚ ሀይሎች ሀሳባቸዉን ሲያስተካክሉ ብቻ የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ድጋፍ እንደሚያገኙ መርሳት የለባቸዉም::

አሜሪካኖቹም ሆኑ ሌሎች ምዕራባዉያን ኢትዮጵያ ወደ ብዙ ትናንሽ ሀገር ተከፋፍላ የማያዉቁት ብዙ ችግር እና የአሸባሪ መፈልፈያ መንግስታት እንዲፈጠሩ እንደማይፈልጉ መረዳት ከአንድ ፖለቲከኛ ነኝ ከሚል ወገን ይጠበቃል::ስለዚህም ልዩነትን ማቻቻያ ስልቶችን በተሻለ መንገድ በመቀመር በኢትዮጵያ ጥላ ስር የሚወክሉትን ማህበረሰብ በተሻለ ፍላጎቱን እንዴት ማንጸባረቅ እንደሚቻል እንዲሁም በትብብር በመስራት የተሻለ ሀገራዊ ፖለቲካ ማስፈን ላይ ማተኮር ተገቢ ነዉ::

በአጠቃላይ ብዙ ህዝባዊ ተጋድሎ እየተካሄደበት : ብዙ መስዋዕትነት እየተከፈለበት ያለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የወደፊት ተስፋ ባክኖ እንዳይቀር የተቃዋሚዉ ጎራ አደራ እና እዳ እንዳለበት ማወቅ አለበት::ይሄንን ህዝባዊ ተጋድሎ እና መስዋዕትነት ማስጠበቅ እና ማስቀጠል ብሎም ለፍሬ ለማድረስ ከተቃዋሚዉ ጎራ ብዙ እንደሚጠበቅ እንያንዳንዱ ተቃዋሚ በደንብ ሊገነዘበዉ የሚገባ እዉነት ነዉ::የዚህ ግንዛቤ መገልጫዉም ከላይ እንደተተረከዉ እያንዳንዱ የፖለቲካ ቡድን እና ድርጅት የፖለቲካ ህሳቤዉን ወደ ከፍታ ማማ ላይ በማሳደግ ተግባራዊ ማድረግ ሲችል ነዉ::

ተመሳሳይ ሀተታዎች