ስለ ጾምና ጸሎት (ከየፍቅር ጉዞ ማርያምን ይዞ ፌስቡክ የተገኘ)

ስለ ጾምና ጸሎት (ከየፍቅር ጉዞ ማርያምን ይዞ ፌስቡክ የተገኘ)

 

✔ ፆም (ጦም ) ማለት ሰውነትን ከመብል ከመጠጥና ከክፉ ስራ ከሐሜት ከመጥፎ ንግግርና ከኃጥያት ሁሉ መከልከል ማለት ነው ።

✔ የፆም ጊዜ ራስን የማዋረድ የኃዘን የጸሎት የንስሐና የኑዛዜ ጊዜ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል ።

✔ በአምላካችን ፊት ራሳችንን እናዋርድ ዘንድ ፥ ከእርሱም የቀናውን መንገድ ለእኛና ለልጆቻችን ለንብረታችንም ሁሉ እንለምን ዘንድ በዚያ በአኅዋ ወንዝ አጠገብ ፆም አወጅሁ ። 《ዕዝ 8 ፡ 21》

✔ ይህንም ቃል በሰማሁ ጊዜ ተቀምጬ አለቀስሁ ፥ አያሌ ቀንም አዝና ነበር በሰማይም አምላክ ፊት እፆምና እጸልይ ነበር ። 《ነህ 1 ፡ 4》

✔ ማቅ ለብሼ በአመድም ላይ ሆኜ ስፆም እጸልይና እለምን ዘንድ ፊቴን ወደ ጌታ ወደ አምላኬ አቀናለሁ ። 《ዳን 9 ፡ 3》

 የሚፆሙ ሰዎች በሁለት ይመደባሉ 

↪ 1. የፆም ጊዜያቸው እስኪፈጸም ድረስ ያለምንም እህል ውሃ በባዶ ሆድ የሚጦሙ ሲሆን

↪ 2. ከስጋ ከቅቤ ከእንቁላልና ለስጋ ሀይል ሰጪ ያልሆኑ ምግቦችን እንዲሁም ከሚያሰክር መጠጥ በመከልከል እስከ ተወሰነ ሰዓት በባዶ ሆድ ቆይተው ሰዓታቸው ሲደርስ የሚመገቡ ናቸው ።

 ያለ ምንም እህል ውሃ የሚፆሙ 

✔ ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ ሰብስብ ፥ ለእኔም ፁሙ ሶስት ቀን ሌሊትንና ቀኑን አትብሉም ፥ አትጠጡም እኔና ደንገጥሮቼ ደግሞ እንዲሁ እንፆማልን ። 《አስ 4 ፡ 16》

✔ የነነዌ ሰዎች እግዚአብሔርን አመኑ ለፆም አዋጅ ነገሩ ፥ ከታላቁም ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ ማቅ ለበሱ ። 《ዮናስ 3 ፡1 – 10》

➡ ❤ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ አለም የመጣውና በስጋ የተገለጠው ለሁለት ዐበይት ነገሮች ነው

↪ ♥1ኛ. ራሱን መስዋእት አድርጎ እኛን ለማዳን ሲሆን

↪ ♥2ኛ. ለእኛ ለክርስቲያኖች ማድረግ የሚገባንን ነገር ሊያሳየንና አርአያ ሊሆነን ነው ።

➡ ❤ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ አርባ ቀንና አርባ ሌሊትም ከፆመ በኋላ ተራበ ። 《ማቴ 4 ፡ 1 – 5》

ከሀይል ሰጪ ምግብ የሚፆሙ

✔ በዚያም ወታት እኔ ዳንኤል ሶስት ሳምንት ሙሉ ሳዝን ነበርሁ ። ማለፊያ እንጀራም አልበላሁም ፥ ስጋና ጠጅም በአፌ አልገባም ፥ ሶስቱም ሳምንት እስኪፈጸም ድረስ ዘይት አልተቀባሁም ። 《ዳን 10 ፡ 2 – 3》

✔ ጉልበቶቼ በፆም ደከሙ ስጋዬም ቅቤ በማጣት ከሳ ። 《መዝ 108/109 ፡ 24》

✔ ሌላው ጸሎትና ፆም አጋንንትን ማሸነፊያ እንዲሆን ጌታችን በ 《ማቴ 17 ፡ 21》ተናግሯል ።

ሰባቱ 7 አጽዋማት

↪ 1ኛ. ዐብይ ፆም 《 አርባ ፆም 》 ↩

✔ ይህ ፆም በ《ማቴ 4 ፡ 1》 እና በ《ሉቃ 4 ፡ 1》 እንደተጻፈው ጌታ ራሱ የፆመው አርባ ፆም የሚባለው ነው ። አርባ ፆም የተባለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ምንም ሳይቀምስ ለአርባ ቀንና አርባ ሌሊት ስለፆመው እና ዲያሽሎስን ድል እንዳረገው እኛም የሱን አርአያ በመከተል ነው የምንፆመው ።

↪ 2ኛ. ፆመ ሐዋርያት ↩

✔ ከአብይ ፆም ቀጥሎ ሁለተኛው ፆም ፆመ ሐዋሪያት 《 የሰኔ ፆም 》 ይባላል ። ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ ብኋላ ለስብከተ ወንጌል ከመሰማራታቸው በፊት የፆሙት ፆም ነው ።በዚህም የወንጌል ስራቸው ሰምሮላቸዋል ።

✔ ስለዚህ አልጫ የነበረውን ዓለም በወንጌል ለማፋጠን ሐዋርያት ከፆም ከጸሎት ጋር የቱን ያህል እንደተጋደሉና መንፈስ ቅዱስም በሐዋርያት አድሮ የሰራውን ድንቅ ስራ ለማሰብ ነው ።

↪ 3ኛ. ፆመ ፍልሰታ ↩

✔ ይህ ፆም ከነሐሴ 1 ቀን እስከ ነሐሴ 15 ቀን የሚፆም ነው ። ይህ ፆም የእመቤታችን መታሰቢያ ነው ። ይህም እመቤታችን ከሞት ተነስታ በክብር ወደ ገነት ስታርግ ሐዋርያው ቶማስ ከተልዕኮ ሲመለስ ተገናኝተው የከፈኗን ጨርቅ ለበረከት ሰጥታዋለች ።

✔ ሐዋርያት ይሄንን ዜና ከቶማስ በስሙ ጊዜ እነሱም የቶማስ ያየውን ያዩ ዘንድ አምላካችንን ከ ነሐሴ 1 – 15 ቀን በፆም ለምነውት ክርስቶስም ለጥያቄያቸው መልስ ሰጥቷቸዋል ።

✔ ስለዚህ ይህን ድንቅ ነገር ለማሰብና ይህን ፆም ምክንያት በማድረግ የተሰወረው መንፈሳዊ ሚስጥር ሁሉ በቸርነቱ ለቤተክርስቲያን የተገለጠ እንዲሆን በማለት ምእመናን በየዓመቱ ፆመ ፍልሰታን ይፆማሉ ።

↪ 4ኛ. ፆመ ነብያት《የገና ፆም》 ↩

✔ ይህ ፆም ከህዳር 15 እስከ ታህሳስ 28 ያለው ጊዜ ሲሆን በዓሉ  ♥ ልደት  ♥ በዘመነ ዮሐንስ ታህሳስ 28 ቀን ይውላል ። ጌታችን ኢየሰስ ክርስቶስ በስጋ ከመገለጡና ሰው ከመሆኑ በፊት ነቢያት የጌታን መምጣት በናፍቆት በፆም እና በጸሎት ሲጠባበቁ ነበር ።

✔ ስለዚህ የነቢያትን የፆም ድካም ለማሰብና አሁንም የአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ደግሞ የሚመጣ ክርስቶስን በናፍቆት ሲጠባበቁ እንደ ነቢያት መንፈሰ ኃይልን ለመልበስ በእምነት ለመጽናት በእምነት ለመጽናት ኃጢያትን ለመዋጋት ሲባል ይህን ፆም ክርስቲያኖች ይፆሙታል ።

↪ 5ኛ. ገሃድ 

✔ ገሃድ ማለት ግልጥ የሆነ ለውጥ ማለት ነው ። ገሃድ የጥምቀት ብቻ ነው ። ይኸውም ጥምቀት ረቡዕና ዓርብ ቀን በሚውልበት ጊዜ በኋላው የሚገኙ ማክሰኞና ሐሙስ የፍስክ ቀንነታቸው ወደ ፆምነት ተለውጦ ይፆማል ። ሆኖም ጥምቀት በሌላም ቀን ቢውል የዋዜማው ቀን ይፆማል ።

↪ 6ኛ. ነነዌ ፆም 

✔ የዚህ ፆም ጊዜ ሶስት ( 3 ) ቀን ብቻ ነቅ ። ቀኖቹም በየዓመቱ ሰኞ ማክሰኞ ረቡዕ ናቸው ። የነነዌ ፆም በመባጃ ሐሙስ( አቆጣጠር ) ከፍ እና ዝቅ ስለሚል አንድ ጊዜ በጥር አንድ ጊዜ በየካቲት ይሆናል ።

✔ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ይህን ፆም የወሰኑት ልትጠፋ የነበረች ነነዌን በፆም ምክንያት እግዚአብሔር ይቅር ስላላት ይህን አምላካዊ ይቅርታውን ለዘለዓለም ለማሰብና ዛሬም በዚህ ዓለም ከነነዌ የከፋ ርኩሰትንና ኃጢያትን ስላለ የነነዌ ሕዝብ ይቅር ያልክ አምላክ ዛሬን ይቅር በለን ለማለት ነው ።

↪ 7ኛ. የረቡዕ ዓርብ ፆም ↩

✔ ሰባተኛውና የመጨረሻው ፆን ረቡዕ እና ዓርብ ነው ። አይሁድ ክርስቶስን በእንጨት ሰቅሎ ለመግደል የተፈራረሙበት ዕለት ረቡዕ ስለሆነ እና ዓርብ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ይህ ነው የማይባል መከራ የተቀበለበት የተሰቀለበትና የሞተበት እኛን ያዳነበት ቀን ስለሆነ ነው ።

ለመንፈሳዊነት ቅድሚያ እንስጥና የእግዚአብሔርን ብድራት እንጠብቅ፡ እግዚአብሔር ጾማችንን ጾመ ድህነት ጾመ ስርየት ሰይጣንን ድል መንሻ ፣የኃጥያት መደምሰሻ ፣ መንግስተ ሰማያትን መውረሻ ያድርግልን