አቶ ማሙሸት አማረ የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው

አቶ ማሙሸት አማረ የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው

በጌታቸው ሺፈራው

 

አቶ ማሙሸት አማረ የሽብር ክስ ተመሰረተባቸው
ማሙሸት ዓማረ ጽኑው ኢትዮጵያዊ!

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዝደንት አቶ ማሙሸት አማረ ዛሬ ሀምሌ 25/2009 ዓ.ም የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁን ቁጥር 652/ 2001 አንቀፅ 4 ስር የተደነገገውን ተላልፈዋል በሚል በማሴር፣ መዘጋጀትና ማቀድ የሽብር ክስ ተመሰርቶባቸዋል፡፡

አቶ ማሙሸት አማረ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ተነስቶ የነበረውን ህዝባዊ እምብይተኝነት በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል እንዲስፋፋ አባላትን በመመልመል፣ ሀገር ውስጥና ውጭ ሀገር ከሚገኙ ግለሰቦች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ በጎጃምና ጎንደር የነበረውን እንቅስቃሴ በማቀናጀት በመምራት ተንቀሳቅሰዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለግንቦት ሰባት አባላትን መልምሎ ወደ ኤርትራ በመላክ፣ መንግስትን በትጥቅ ትግል ለመጣል በሰሜን ሸዋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በመመስረት፣ አባላትን በማሰልጠንና በማስታጠቅ ተንቀሳቅሰዋል የሚል ዝርዝር ክስ ቀርቧል፡፡

አቶ ማሙሸት አማረ ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም መንግስት አይ ኤስን ለማውገዝ በጠራው ሰልፍ ላይ ሰልፈኛው በኢህአዴግ ላይ ተቃውሞ ማሰማቱን ተከትሎ በተቃውሞው ተሳትፈሃል ተብለው ለእስር ተዳርገው የነበር ሲሆን ሰልፉ በተደረገበት ቀንና ሰዓት ከምርጫ ቦርድ ጋር በነበራቸው ክርክር ሰልፉ ላይ አለመገኘታቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከምርጫ ቦርድ በማቅረባቸው በነፃ እንዲለቀቁ በፍርድ ቤት ቢወስንም፣ ከፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ውጭ ለተጨማሪ ቀናት ታስረው ከቆዩ በኋላ ሌላ ክስ ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወል፡፡

አቃቤ ህግ ሚያዝያ 14 ሰልፍ ላይ እንደተገኙ ላቀረበው ክስ በዚሁ ቀንና ሰዓት ከምርጫ ቦርድ ጋር ክርክር ላይ እንደነበሩ ማስረጃ በመቅረቡ ሚያዝያ 13 ህዝብን አነሳስተው ለሚያዝያ 14 በመንግስት ላይ ተቃውሞ እንዲያሰማ አድርገዋል በሚል ሌላ ክስ ተመስርቶባቸው እና አራት ግለሰቦች መስክረውባቸው በድጋሜ በፍርድ ቤት በነፃ ተለቀዋል፡፡ አቶ ማሙሸት ባለፉት 26 አመታት ከ10 ጊዜ በላይ ለእስር እንደተዳረጉ ተገልጾአል፡፡ አቶ ማሙሸት የክስ መቃወሚያ ለማቅረብ ለነሃሴ 1/2009 ዓ.ም ተቀጥረዋል፡፡