ማሙሸት አማረ፥ የሩብ ክፍለ ዘመን አሸብራቂ ታጋይ!

ማሙሸት አማረ፥ የሩብ ክፍለ ዘመን አሸብራቂ ታጋይ!
ሸንቁጥ አየለ

 

ማሙሸት አማረ፥ የሩብ ክፍለ ዘመን አሸብራቂ ታጋይ!
ህጋዊዉ የመኢአድ ፕሬዝዳንት አቶ ማሙሸት ዓማረ

ግንባሩን አላጠፈም:: በመከራ ዉስጥ በመራመዱ አልተከፋም:: ከግማሽ እድሜዉ በላይ በትግል ዉስጥ በማሳለፉ ቅሬታ የለዉም:: ከአስራ ሶስት አመታት በላይ በስር ቤት በማሳለፉም በምሬት ሲናገር ተደምጦ አያዉቅም:: ኢትዮጵያን ይወዳታል እንጅ ኢትዮጵያ እንድትወደዉ አንድም ቀን ጠብቆ አያዉቅም:: ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ ሲናገር ታላቅ እና ከፍ ያለ አክብሮት አለዉ::ሲናገር ጠንቃቃ ነዉ:: አንደበቱ ልዝብ ነዉ:: ስሜትን በመግታት ልምድ ዉስጥ ያለፈ ታላቅ ባለ አዕምሮ ሰዉ ነዉ::

በኢትዮጵያዊነት ሲከሱት አልተበሳጨም:: በብሄሩ አሳበዉ ሲያሳድዱት አንድም ቀን አልተሸማቀቀም:: በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አቀንቃኝነት ሲኮንኑትም አንድ ጊዜም ቅር አልተሰኘም:: የሆነዉን ነገር ሁሉ ይወደዋል:: ኢትዮጵያ ያላትንም ሁሉ ይወዳል:: ኢትዮጵያ ዉስጥ በወያኔ ዘመን ለመፈረጅ ሰዉ መሆን በቂ እንደሆነ በደንብ ገብቶታል:: ሰዉ ከዚህ ወይ ከዚያ ብሄር ቢሆን ወያኔን እስከተቃወመ ድረስ በብሄሩ ይፈረጃል:: ኦርቶዶክስ ወይም ሙስሊም ቢሆንም ወያኔን እስከተቃወመ ድረስ በወያኔ ይፈረጃል:: ኢትዮጵያዊነት እምነቱ ከፍ ያለም ቢሆን በኢትዮጵያዊነት እምነቱ ይከሰሳል:: እናም ማሙሸት አማረ ስትጠይቀዉ የሚመልሰዉ መልስ ያስደምማል:: “ወያኔ የሚሰራዉ ስራዉን ነዉ:: መፈረጅ እና የማጥላሊያ ቅጣይ ማዉጣትን እንደ ግብ የሚወስደዉ ታጋዮችን ለማሸማቀቅ መሆኑ መታወቅ አለበት:: እናም ትግል ዉስጥ የሚገባ ሁሉ ይሄን አዉቆ ከተነሳ መፈረጅን በታላቅ ደስታ መቀበል አለበት” ብሎ ይመልሳል:: በመሆኑም ዝም ብሎ በአርምሞ ይታገላል::

የሚታግልበትን ድርጅት ስም ነጥቀዉ ለሌላ ሲሰጡት ትግል ቆመ አላለም:: ባንዳዎች ዙሪያዉን ሲከቡት ወደኋላ አላፈገፈገም:: ደጋፊዎቹ እንደ ቦና ጉም ትን ብለዉ ሲሸሹት ከኢትዮጵያዊነት ትግሉ ሸብረክ አላለም:: ሌላዉ ቀርቶ በጣም ይታመንባቸዉ የነበሩት የትግል አጋሮቹ የከሰሱት ጊዜ እንኳን ትግል እርሜ አላለም:: የኢትዮጵያ ፖለቲካ በሸፍጥ የተሞላ መሆኑን ጠንቅቆ ያዉቃል:: እናም ሁሉንም ነገር ፈገግ ብሎ ያሳልፈዋል:: “ኢትዮጵያዊነት መከራ እና ፈተና ዉስጥ ያለፈ ታላቅ መንፈስ ነዉ !” ይልሃል ማሙሸት አማረ:: “በእኛ ዘመን የተለዬ ነገር አልገጠመንም:: የቀደሙ አባቶቻችንን የገጠማቸዉ መከራ እና ፈተና እንጅ የገጠመን” ብሎ ያምናል ማሙሸት አማረ::

በዉይይት ወቅት በተመስጦ ያደምጣል:: መናገር ከጀመረ የመረጃ ዝናብ ያዘንባል:: ንግግሩ በቁም ነገር የተሞላ ነዉ:: ሀሰት እና ሃሰተኛ ይጸዬፋል:: ወዳኋላ ወይም ወደፊት በማለት አይዋዥቅም :: ወደፊት ብቻ በትግል መስመሩ ላይ ይራመዳል:: ዉስብስብ በሆነዉ እና በባንድነት ስነልቦና በተሞላዉ የኢትዮጵያ የተቃዉሞ ወንዝ ዉስጥ ገብቶ መዋኘት ከባድ እንደሆነ ያዉቃል:: በተለይም ባንዶችን ፊት ለፊት መናገር እና መግጠም ብዙ ዋጋ ያስከፍላል:: ባንዶቹ እጅግ ብዙ ከመሆናቸዉ የተነሳ ንጹሃኑን ጠልፈዉ እየጣሉ ከጠላትም ከወገንም በሁለት ቢላዎ እየበሉ እሞቀበት ገብተዉ እየጨፈሩ ከፓርቲ ፓርቲ እያማረጡ ከባንዳዉ ወያኔ ጋር እየተርመጠመጡ የቀደመ የኢትዮጵያዉያንን መሰረት ሁሉ እያንኳሰሱ ዛሬ ያመኑበትን ነገ እየረገሙ ይመላለሳሉ:: ማሙሸት አማረ ግን እንዲህ አይነት ነገር ከቶም አይነካካዉም:: ጽይፉ ነዉ:: መጸዬፍ ብቻ አይደለም ፊት ለፊት ይገጥመዋል::

ራበኝ አይልም:: ለግሌ አይልም:: ይሄ ቀረብኝ አይልም:: እንደሌሎች ልታወቅ ልታወቅ አይልም:: ሀሰት ፈብርኮ አደባባይ ላይ ወጥቶ አይጨፍርም:: እቤት ዉስጥም እጓዳም አደባባይም ላይ ያዉ አንድ አቋም አለዉ አንዲት ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በወያኔ ስርዓት ስለማትመጣ ወያኔን መታገል አለብን ብሎ በፍጹም ያምናል:: በአደባባይም ይናገራል:: ትግሉንም በትህትና ለሃያ ስድት አመታታ ቀጥ ብሎ አራምዶታል:: አሁንም በመከራ ወህኒ ዉስጥ ስለኢትዮጵያ ይማቅቃል:: ማሙሸት አማረ:: እሱ ስለ ኢትዮጵያ ሲል በፍቅር እና በደስታ ይሄን ያህል አመታት ይማቅ እንጅ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ስለዚህ ሰዉ በቂ እዉቀት የለዉም:: ምናልባትም ስለዚህ ሰዉ ህዝቡ እንዳያዉቅ ያሸመቁ ብዙ ታጋይ መሳዮች እንዳሉም እዉነትን የሚያነፈንፈዉ ብልህ ወገን በቂ መረጃ ላይኖረዉ ይችላል::

አንድ ቀን እንዲህ ሆነ:: ስዬ አብርሃ የሚባል ገዳይ የወያኔ ምሰሶ ከመለስ ዜናዊ ጋር ተጣላ ተባለ:: እናም ወዲህ እና ወዲያ እንደ ወጭት ዉሃ የሚዋልለዉ የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ተሰብስቦ ስዬ አብርሃን ጭንቅላታችን ላይ እናስቀምጠዉና ይምራን:: ወያኔን ስዬ ይጥለናል የሚል ዉይይት ተጀመረ:: ስለሆነም መኢአድንም በአንድ አድርጎ ስዬ ይምራልን የሚል ልኩስኩስ ሀሳብ መጣ:: ማሙሸት ጥያቄ ጠዬቀ:: “ስዬ ከመለስ በምን ይሻላል? ደግሞስ ስዬ ይምራን ስትሉ ምን አይነት ስርዓት እንዲያመጣላችሁ ፈልጋችሁ ነዉ?” አንዳንዱ እየተነሳ ዘባረቀ:: “ስዬን የወያኔ ሰራዊት ስለሚያዉቀዉ ወያኔን ለመጣል ምርጡ አማራጭ ስዬ ነዉ” የሚል ማብራሪያ ሰጠ::አንዳንዱም “ስዬ ቆራጡ” እያለ ፈነጨ::

ማሙሸት ይሄን ሁሉ አዳምጦ አንድ መልስ መለሰ:: “ስዬን ለጊዜዉ እንደፈለጋችሁ በአንቀልባ አዝላችሁት ዙሩ:: አሁን መጽሀፍ እየጻፈ ነዉ:: መጽሀፉ ሲወጣ ምን እንደሚል ታዩታላችሁ:: ወያኔ የሚባለዉ ፓርቲ ምርጡ ፓርቲ ነዉ:: ጥፋተኛዉ መለስ ብቻ ነዉ ብሎ ይሰብክሃል:: በስዬ አይን ወያኔ ማለት የሰማያት ጻድቃን ስብስብ ሲሆን የስዬ ጸቡም ከመለስ ጋር ብቻ ነዉ:: እናም ስዬ ማለት መለስ ማለት ነዉ:: መለስን አንስተህ ስዬን ለማስቀመጥ ምን ትግል ያስፈልጋል? ይሄ ፈጽሞ ከንቱ ትግል ነዉ:: እኛ ስዬ ከሚባል ሰዉ ጋር አንሰራም” ሆኖም በቦታዉ የነበሩ ጋዜጠኛ ተብዬዎች እና ፖለቲከኞች ወጥተዉ ማሙሸት ላይ በትችት ወረዱበት::

ይሄን ያስተዋለ አንዱ የማሙሸት ጓደኛም ” አንዳንዴ ምን አለበት ዝም ብትል:: ይሄ ሁሉ ትችት ባንተ ላይ የሚዘንበዉ ብልጠት ስለሚጎልህ ነዉ” ሲል መከረዉ:: ማሙሸት ፈገግ አለ:: “አጼ ምኒልክን የሚወቅስ ሀገር እኔን አንድ ተራ ማሙሸት አማረን ለምን ወቀሰኝ ብዬ እንድከፋ ጠብቀህ ከሆነ አይከፋኝም:: ሆንም ባንዳ አዝዬ ትግል እያልኩ እንድዞር አትጠብቅ:: እሞቀበት መደለቅ የፈለገ መብቱ ነዉ:: እኔ ግን እዉነቱን በመናገር መሳሳታቸዉን ከመናገር ከታቀብኩ ህዝቤን እያታለልኩ ነዉ ማለት ነዉ:: ስዬ ማለት ያዉ እንደነ መለስ ሀገር ያፈረሰ ወንጀለኛ ነዉ::”

ማሙሸት አማረ አሁንም የመኢአድ ህጋዊ ፕሬዝዳንት ነዉ:: ብዙሃኑ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች እና ጸሃፊዎች ከዉጭ ሀገር እስከ ሀገር ቤት ህሊናቸዉን ወደ ዉስጥ መመርመር የማይችሉ ግልብ ናቸዉ:: ወያኔ ህጋዊዉን መሪ ሲያስረዉ “የቀድሞዉ” የመኢአድ መሪ ይሉታል:: ተደጋግሞ ቢነገራቸዉም አይሰሙም:: የወያኔን የስር ዉሳኔ ተቀብለዉ እንደ ገደል ማሚቶ ይጮሃሉ:: የቀድሞዉ የሚባለዉ ህዝብ ከሻረዉ ብቻ ነዉ:: በህጋዊነት ፓርቲው: አመራሪ አባሉ እና ደጋፊዉ ህዝብ የመረጠዉን ህጋዊ መሪ ወያኔ “ህጋዊ አይደለህም” ወንጀለኛ ነህ ስላለዉ ህጋዊነቱን አያጣም:: ስለዚህ አንድ መሪ ስለታሰረ ብቻ እየሮጡ “የቀድሞዉ” ማለት የወያኔን ዉሳኔ ማጽደቅ ነዉ ተብለዉ ቢነገሩም አይሰሙም:: እናም የቀድሞዉ የመኢአድ ፕሬዝዳንት ብለዉ ይጠሩታል::

እናም በርካታ ሚዲያዎች የአንባገነን እና የዘረኛ ቡድንን ዉሳኔ እንደ ዉሳኔ እየተቀበሉ በርካታ ታጋዮችን ከትግል ማማ ላይ እያወረዱ ይፈጠፍጧቸዋል:: እንዲህ አይነት የገደል ማሚቶ ሚዲያ በተሰበሰበበት ማህበረሰብ ዉስጥ እዉነት እንደ እሳት ዉስጥ ቅቤ ዝም ብሎ ሳይታይ ይቀልጣል:: ማህበረሰቡ ሆያሆዬ ወዳድ እና እዉነትን ከመመርመር የዘገዬ ስለሆነ ስር ያለዉ እና ስር የሌለዉን አጥርቶ አያስተዉልም:: አጥርቶ የሚያስተዉልበት ሚዲያም የለዉም::

ከወያኔ ጋር ተጣላን ስላሉ ብቻ (መጣላት አለመጣላታቸዉ በወል አይታወቅም) ወያኔን ያገለገሉ ህዝብን ሲገሉ እና ሲያስገድሉ የነበሩ እጃቸዉ በደም የተጨማለቀ ሰዎችን ብሎም ሀገሪቱን ሲያፈርሱ የነበሩ ብልጣብልጦችን እንደ ምርጥ ታጋይ ሰማዬ ሰማያት ለማዉጣት የሚጣደፈዉ የተቃዋሚ ተብዬዎች ሚዲያ ጽኑአን ታጋዮችን እና የሰበአዊ መብት ተከራካራካሪዎችን እንዲሁም ጋዜጠኞችን በወያኔ ዉሳኔ እስር ቤት ሲገቡ ወንጀለኛ ያደርጋቸዉ እና “የቀድሞ” ጋዜጠኛ: “የቀድሞ” መሪ : “የቀድሞ” ምንትስ እያለ ይጠራቸዋል:: በዚህም የሀቅ ልጆች እና የሀቅ ታጋዮች ወያኔ እንደሚፈልገዉ ከህዝቡ ልብ እየተፋቁ ወደ ቀድሞነት እየተለወጡ ወደ ስርቻ ይወረወራሉ:: የሚያስባቸዉ እና የሚያስታዉሳቸዉ የለም::

የኢትዮጵያ ሰዉ አንዳንዴ ያስቃል:: ቆራጥ ታጋይ እና የታመነ መሪ ይፈልጋል:: ግን ቆራጦቹን እና የታመኑትን ወያኔ ወደ እስር ቤት ሲጥላቸዉ እንደ ተጣለ እቃ ይረሳቸዋል:: ምርጦቹ ጋዜጠኞች: ምርጦቹ ታጋዮች እና ምርጦቹ መሪዎች ሲታሰሩ በቃ “የቀድሞ” ይባሉ እና እንደ ተጣለ እቃ ወደ ስርቻ ተወርዉረዉ ይረሳሉ:: ሃሃሃሃ…ከዚያ ይልቅ የወያኔ አገልጋይ የነበሩትን እና የህዝብ አራጆቹን ብልጣብልጦች ልክ እንደ ጀግና እያስጨፈረ ድል እንዲያመጡለት ይጠብቃል:: ድል? እም…ቀልድ::

መርህ የሚባለዉ ነገር ገደል ገብቷል:: እዉነት እሳት ዉስጥ እንደገባ ቅቤ የትም ትቀልጣለች:: በዚህ አይነቱ ዉስብስብ የተቃዉሞ ፖለቲካ ዉስጥ ምርጦቹ ሳይታዩ ይቀልጣሉ:: የሆነ ሆኖ ማሙሸት አማረ በዚህ ሁሉ ሲከፋ አይሰማም:: ቅሬታም ፈጽሞ የለዉም:: የእርሱ አላማ አንድ ነዉ:: ኢትዮጵያን መዉደድ ለሚወደዉም ነገር በደስታ እና በታላቅ ወኔ መስዋዕት መሆን:: እየሆነም ያለዉ ይሄዉ ነዉ::

አሁን ማሙሸት አማረ በወያኔ ወንጀለኛ ትእዛዝ እስር ቤት ነዉ:: በመላ ሀገሪቱ በተለይም በአማራ ክልል እና በኦሮሚያ የተቀሰቀሰዉን አመጽ የመራዉ እና ያስተባበረዉ ማሙሸት አማረ ነዉ ብሎ ወያኔ ከሶታል::ወያኔ ምንም አይነት ክስ በማሙሸት አማረ ላይ ቢያቀርብም ቅሉ ግን ማሙሸት አማረ አሁንም ህጋዊዉ የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መሪ ነዉ:: የሩብ ክፍለ ዘመን አሸብራቂ ታጋይ የሆነዉ ማሙሸት አማረ በትህትና እና በቆራጥነት ስለ ታላቂቱ ኢትዮጵያ ሀገሩ የከፈለዉ መስዋዕትነት ሁሉ በታመኑ ኢትዮጵያዉያን ልብ ዉስጥ ከፍ ያለ ቦታ አለዉ::

ማሙሸት አማረ በእስር ቤት ዉስጥ ብትሆንም መልካም አዲስ አመት ይሁንልህ !