ህዝባዊዉ ጽንስ እስኪወለድ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋዉ ስራህን ዝም ብለህ ከዉን

ህዝባዊዉ ጽንስ እስኪወለድ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋዉ ስራህን ዝም ብለህ ከዉን
ሸንቁጥ አየለ
=====================

 

ህዝባዊዉ ጽንስ እስኪወለድ ጋዜጠኛ ሙሉቀን ተስፋዉ ስራህን ዝም ብለህ ከዉን
ሙሉቀን ተስፋዉ

 ሙሉቀን ተስፋዉ የህዝብ ልጅ ነዉ:: ጎበዝ ወጣት ነዉ:: ወደፊት ደግሞ እየበሰለ ሲመጣ በርካታ ስራን ለኢትዮጵያ ህዝብ የመስራት አቅም አለዉ:: አሁን ባለዉ የወጣትነት ዘመኑ ሶስት መጽሃፍን ማበርከት የቻለ እና ብዙ ግፎችን ያጋለጠ ትንታግ ጋዜጠኛ ነዉ:: በተለይም የተደበቀዉን የአማራ ህዝብ የዘር ማጥፋት ስራ ቁልጭ አድርጎ በመረጃ እና በድፍረት ተንትኖ በመጽሀፍ አዘጋጅቶ ለህዝብ ያቀረብ የቁርጥ ቀን ልጅ ነዉ::

ኢትዮጵያ ዉስጥ ጋዜጠኛ በነበረበት ወቅት ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ አንገብጋቢ ጉዳዮች ትኩረት ሰጥቶ የሚዘግብ ብቻ ሳይሆን እቦታዉ ድረስ እየሄደ: ልዩ ልዩ ፖለቲከኞችን እየጋበዘ እና እያከራከረ በትጋት ያለወገንተኝነት ሲሰራ የነበረ ደፋር ጋዜጠኛ ነዉ:: ቀለም ቀንድ ላይ በሀላፊነት በሚሰራበትም ጊዜ በግሉ መንግስታዊ ድርጅት ዉስጥ ይሰራ ነበርር:: ሆኖም ከዚህ ዋና ስራዉ በተጨማሪ ግን የቀለም ቀንድ ጋዜጣ አንድም ደሞዝ ሳይከፍለዉ ጋዜጣዉን በታላቅ ሀላፊነት ሲያገለግል የነበረዉ ለህዝብ ካለዉ ፍቅር እንጅ ጥቅም ፈልጎ አይደለም::

በሂደትም ጠቅልሎ ወደ ጋዘጠኝነት ከገባ ብኋላ ማንም ጋዜጠኛ ደፍሮ ሊያከናዉነዉ የማይችለዉን ስራ በታልቅ ወኔ ሰርቷል:: ይሄን ጋዜጠኛ ወያኔ ብዙ ቢያንገላታዉም በመጨረሻ እንደ ሌሎች ጋዜጠኞች ወደ ግዞት ሳይወረዉረዉ እግዚአብሄር አድኖት ወደ ዉጭ አገር መዉጣት ችሏል:: ሆኖም ሙሉቀን አሁንም ህዝባዊ ስራዉን ቀጥሏል::

እናም ሙሉቀን ሊበረታታ እና ሊመሰገን ይገባዋል :: ሃያ አምስት አመታት ሙሉ አንድ መጽሃፍ እንኳን ሳይጻፍበት የከረመዉን የአማራ ህዝብ ላይ የተከናወነዉን የዘር ማጥፋት ስራ እጅግ በታላቅ ድፍረት በቁርጠኝነት እና በትጋት ማጋለጥ የቻለ አንድም ጋዜጠኛ ወይም አክቲቪስት ወይም ፖለቲከኛ እስካሁን አላዬንም::

ይሄን ወጣት የሚጠሉት ሶስት ሀይሎች ናቸዉ:: የኢትዮጵያን ህዝብ መበደል የሚዘግብ በተለይም አማራዉ በደሉን የሚዘግብለት ጋዜጠኛ እና ድምጽ ሊሆነዉ የሚችል ታዋቂ ሰዉ ወጣለት ብለዉ ስጋት የያዛቸዉ የጸረ አማራ ስነ ልቦና የታጠቁ ሰዎች ግንባር ቀደሞቹ የሙሉቀን ተስፋዉ ስም አጠልሺዎች ናቸዉ:: የወያኔ ቡችሎችም ህዝብ ማወናበድ ስራቸዉ ስለሆነ መልካሙን ሰዉ ሀሰተኛ ሀሰተኛዉን መልካም እያደረጉ ያቀርባሉ:: ሌሎች ደግሞ በተወናበደ መረጃ ሙሉቀን ላይ የግል ጥላቻ ያላቸዉ ሀይሎች በሀሰት ሙሉቀንን ይከሳሉ:: ያብጠለጥላሉ:: ወይም ሙሉቀን የሰራዉን ታላላቅ ስራ ከማዬት የተሳሳተዉን ጥቃቅን ነገር እየመዘዙ የሙሉቀንን ሰብዕና ለመግደል ይተጋሉ::

መሉቀን ተስፋዉ የሰራዉን አንድ መቶኛ እንኳን ስራ ያልሰሩ ተቃዋሚ ነን ባይ ከሳሾቹን ሳይ አፍርላቸዋለሁ:: ግን የእያንዳንዱን ድብቅ እና ግልጽ አላማ በደንብ በመከታተል ለህዝብ ማጋለጥ ይገባል:: ወያኔን ለማስወገድ በዚህ ወይም በዚያ መልክ የሚሰሩ ህዝባዊ ጀግኖችን የምታጠቁ እቡያን የማታዉቁት ስዉር ህዝባዊ ጣት እንዳይወጋችሁ ጥንቃቄ አድርጉ::

ይሄ ልጅ ማንንም ሲያንቋሽሽ ወይም በማንም ላይ ድንጋይ ሲወረዉር አልታዬም:: እርግጥ ነዉ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ስለ አማራ ህዝብ መገፋት መገደል መሰደድ እና ዘር መጥፋት ተግቶ እየጮህ እና እየዘገበ ያለ ጋዜጠኛ ነዉ:: ሙሉቀን በርታ:: ሁሉም ነገር በሂደት ግልጽ መሆኑ አይቀርም:: ወሽ ከሆነ ይጠፋል: ሽል ከሆነ ይጋፍል ነዉና ህዝባዊዉ ጽንስ እስኪወለድ ስራህን ጠንክረህ ስራ::

ኢትዮጵያ እጅግ ዉስብስብ ሀገር ነዉ:: ጠላቶቹም ዉስብስብ: ፖለቲካዉም ዉስብስብ: ህዝቡ ጠላትና ወዳጁን ለመለዬት በብዙ ሀሰተኛ ቡድኖች በየቀኑ ይወናበዳል:: በፖለቲካ መድረኩ ላይ ከነሱ በቀር ሌላ ሰዉ ጭፈራ እንዲያቀርብ የማይፈልጉ እኩያንን እና እቡያን ብዙ ናቸዉ:: ስለሚታረደዉ እና ስለሚገፋዉ ህዝብ ግድ የላቸዉም:: በያዙት ጋዜጠኝነት ወይም በተቆጣጠሩት ሚዲያ ስለሚታረደዉ ህዝብ እና የዘር ማጥፋት ስለሚደረግበት ህዝብ መዘገብ አይፈልጉም:: በተቃዋሚ ፖለቲከኝነት ተሰልፈዉ ለህዝብ ነጻት እና ፍትህ እንታገላለን ቢሉም ሆዳቸዉ ዉስጥ ግን ጥቁር ጥላቻ እና ሙት የጸረ ህዝብ ተልዕኮ አለ:: እናም ህዝባዊ የመሰላቸዉን ሁሉ አንቀዉ ለመግደል ይተጋሉ::

የፍትህ ታጋይ ነን ይላሉ:: ግን ሀሰተኛ ናቸዉ:: ፍትህ ምን እንደሆነ አያዉቁም:: እዉነትን በመደበቅ ፍትህ ያደረጉ ይመስላቸዋል:: ህዝብ ሲታረድ እና ሲገፋ ስለታረደዉ ህዝብ እና ስለተገፋዉ ህዝብ ከመዘገብ እና ከመጮህ ይልቅ ቅራንቅንቦ ምክንያት እየደረደሩ እዉነቱ እንዳይወጣ ይተጋሉ:: እዉነትን በእግራቸዉ ይረግጣሉ:: ግን ህዝባዊ ነን ይላሉ::

ወያኔ አማራ ህዝብ ላይ ሀያ ስድስት አመታት የዘር ማጥፋት ስራዉን አንዴ በሰሜን አንዴ በደቡብ አንዴ በምስራቅ አንዴም በምዕራብ እያደረገ የአማራን ህዝብ ከሁሉ ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ጋር እያቃረነ አሁንም ቀጥሏል:: ይሄን የሚያከናዉነዉ ወያኔ እና ወያኔ ብቻ ነዉ:: የአማራ ህዝብ ጠላት ወያኔ እና ወያኔ ብቻ ነዉ:: የአማራ ህዝብ ሁሉንም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የሚወድ ብቻ ሳይሆን ከሁሉም ኢትዮጵያዊ ማህበረሰብ ጋር የተዋሃደም ነዉ:: የኢትዮጵያ ህዝብም ሁሉ ሰዉ ወዳድ እና ደግ ህዝብ እንጅ የማንም ጥላቻ የለዉም:: የህዝባችን አንድ እና አንድ ጠላት ወያኔ እና ወያኔ ብቻ ነዉ::

ሆኖም ተቃዋሚ ነን : ጋዜጠኛ ነን : አክቲቪስት ነን የሚሉት ወያኔ በአማራ ህዝብ ላይ የሚያከናዉንበት የዘር ማጥፋት ስራ አይዘገብ እያሉ በሚታረደዉ ህዝብ ላይ ሌላ እርድ ያከናዉናሉ:: እናም አሁን የሙሉቀን ወንጀል ስለ አማራ ህዝብ መዘገቡ ብቻ ነዉ:: የሙሉቀን ወንጀል እዉነትን ማጋለጡ ብቻ ነዉ::

ሙሉቀን አይዞህ በርታ ! ወሽ ከሆነ ይጠፋል: ሽል ከሆነ ይጋፍል ነዉና ህዝባዊዉ ጽንስ እስኪወለድ ስራህን ጠንክረህ ስራ::