ፊታዉራሪ ገበየሁ ማናቸው ? ያልተነገረው ታሪካቸው ምንድነው ?

 

ፊታዉራሪ ገበየሁ ማናቸው ? ያልተነገረው ታሪካቸው ምንድነው ?

Gihon Ethiopia 

14 March at 11:10 

 

ፊታዉራሪ ገበየሁ
ፊታዉራሪ ገበየሁ

ፊታዉራሪ ገበየሁ ገቦ (አባ ጎራዉ) በነሐሴ 12.1836 አ.ም በሸዋ ክፍለ ሃገር በተጉለትና ቡልጋ አዉራጃ አንጎለላ ልዩ ስሙ *አስታ ቆላ ጌጠር* በምትባል ስፍራ ተወለዱ። ክርስትናም የተነሱት በፅርሀ አርያም አንጎለላ ኪዳነ ምህረት ነዉ። ፊታዉራሪ ገበየሁ ዉልተታቸዉምም እድገታቸዉም ብሎም የእምዬ ምኒልክ የጦር ሚንስተር እስከመሆን የበቁት እዚሁ አንጎለላ ነዉ።እኚህን ጀግና ስናስታዉስ ኢትዮጵያዊነት ምን ያክል እረቂቅ መሆኑን እንረዳለን ፊታዉራሪ ስለሀገራቸዉ ደማቸዉን የገበሩ ጀግና የጦር አበጋዝ እንደነበሩ ታሪክ ይነግረናል። የንጉሰ ነገስቱ የመሀል ጦር አዛዥ ፊታውራሪ ገበየሁ ከጣልያኖች ጋር በተደረገው በሁሉም ጦርነት የተመሰከረላቸው ጀግና ነበሩ፡፡ የአምባላጌውን ምሽግ በመስበር በጣሊያን ላይ የመጀመሪያውን የድል ደውል ያሰሙት እና ዋናው የድሉ ባለቤት እሳቸው ነበሩ

በዚህም ምክንያት በወቅቱ የፈረንሳይ ጋዜጦች “የአምባላጌው የኢትዮጵያ ጀግና” በማለት እንዳወደሷቸው ተክለፃዲቅ መኩሪያ ፅፈዋል፡፡ የመቀሌውንም ጦርነት በደንብ ተካፍለው በጀግንነት ሲዋጉ እጃቸውን የቆሰሉ ሲሆን ፣ ከጦርነቱ በፊትም ራስ መኮንን ስለ እርቅ ጉዳይ በሚነጋገሩበት ጊዜ ገበየሁ እየተዋጉ ስላስቸገሩ እንደ አምባላጌው እንዳይዋጉ አስረዋቸው ሳለ በኋላ ግን ላይዋጉ አስምለው አስለቀቋቸው፡፡ በኋላም ጦርነቱ ሲጀመር የአምባላጌ የገፈቱ ድል ቀማሽ ፊታውራሪ ገበየሁ አባ ጎራ ነበር።

በእለቱ ታሞ ስለነበር ዱላ እየተመረኮዘ ነው ገደሉን የወጣው፤ ግና ይህ ሁኔታው ድልን ከመቀዳጀት አልከለከለውም። ስሙን ትንሹም ትልቁም ወዲያው አወቀው እና ገጣሚም እንዲህ ሲል አሞገሰው፦

የንጉሥ ፊታውራሪ ያ ጎራው ገበየሁ አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው

ለምሳም ሳይደርሱ ቁርሥ አደረጋቸው  

በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ የአድዋ ድል ጉልህ ድርሻ አለው፡፡ በጦርነቱ ላይ የተሳተፉ ጀግኖች ኢትዮጵያውያንም እንዲሁ፡፡ የአደዋ ጦርነት የተጀመረው በየካቲት 23 ቀን 1888ዓ.ም ከማለዳው ነበር፡፡ ውጊያው ከጠዋቱ 11፡30 ላይ በአራት ጄኔራሎች የሚመራው የጠላት ጦር በፊታውራሪ ገበየሁ ፣ በዋግሹም ጓንጉል ፣ በራስ ሚካኤል እና በራስ መንገሻ ጦር ላይ በሰነዘረው ጥቃት ተከፈተ፡፡

ፊታውራሪ ገበየሁ በዚህ ጦርነት ፊት ለፊት የገጠሙት በእንዳ ኪዳነ ምህረት በኩል የመጣውን እና በጄኔራል አልበርቶኒ የሚመራውን የጠላት ጦር ነበር፡፡ በጦርነቱ ፊታውራሪ ገበየሁ ከሰራዊቶቻቸው በመለየት ጎራዴያቸውን መዘው በዋናው የትግል አውድማ ፣ በተፋፋመ እና በቀለጠው ውጊያ ላይ ተወርውረው ገቡ፡፡ ዘለው እንደገቡም ከጀግናው ጓደኛቸው ከቀኝ አዝማች ታፈሰ ጋር እየፎከሩ የጠላትን አንገት በጎራዴ ሲቆርጡ እና ሲገነድሱ ቆይተው ከርቀት በተተኮሰ ጥይት ተመተው ወደቁ፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ስለ ፊታውራሪ ገበየሁ አዲስ አበባ ድረስ ተማርኮ መጥቶ የነበረው የኢጣልያ መኰንን ፣ጆቫኒ ቴዶኒ የጻፈው ማስታወሻ እንዲህ ይላል….. “በቢያን ኪኒና በማዘቶ ለሚመሩት መድፎች እየተመቱ አበሾች ወደ ኋላ ሲያፈገፍጉ አይቶ “ፈሪ እንዴት ትሸሻላችሁ? እኔ እንዴት እንደምሞት ለንጉሱ ሄዳችሁ ንገሩ” በማለት ፈረሱን በአለንጋ አስነስቶ በግልቢያ በሚዘንበው የመድፍ ጥይት መካከል ገባ፡፡

 እንዲያውም በተክለ ፃዲቅ መኩሪያ መፀሃፍ ላይ እንደተከተበው ፦ “ጦርነቱም አጅግ በበረታ ጊዜ የኢትዮጵያ ጦረኞች ወደ ሇላ እንደማፈግፈግ ሲል ቀይ የክብር ልብስ የለበሰዉ ፊታዉራሪ ገበየሁ “ወደ ሸዋ በህይወት የተመለሰ አሟሟቴን ይናገር” ብሎ ዘሎ ወደ ተፋፋመዉ ዉጊያ ገባ በዚያም እየተዋጋ ሳለ ተመትቶ ወደቀ የጣልያንም ወተደሮች አብረዉ ወድቀዉ ሬሳዉን አከበሩት ድሉም ለኢትዮጵያ ሆነ።” እሱን ሲያይ ሁሉም እየሮጠ ተከታትሎ ገብቶ ከመድፈኞቹ ጋር ተጨፋጭፎና ገድሎ መድፈኞችን ማረከ፡፡ የገበየሁ ሬሳ ከወደቀበት ቦታ የእኛዎቹ ጀግኖች አብረው በመውደቅ የእርሱን ሬሳ አከበሩት” በማለት ገልጾታል፡፡

ፊታውራሪ ገበየሁ ገና ወደ አድዋ ሲዘምቱ ተናዘውም ነበር “ስሸሽ ከኋላዬ ከተመታሁ አሞራ ይብላኝ፣ እኔ እንደ አባቶቼ አይደለሁምና ወግ አይገባኝም፤ ከፊት ለፊት ስፋለም ከወደቅሁ ግን እሬሳዬን /አፅሜን/ ትውልድ ቦታዬ ውሰዱልኝ” አሉ፡፡ እንደተባለውም ሆነ በፅኑ ሲፋለሙ ስለ ሀገራቸው ነፃነት አደዋ ላይ ወደቁ፡፡ በሕይወት እያሉ:-“የአድዋ ሥላሴን ጠላት አረከሰው ገበየሁ በሞቴ ግባና ቀድሰው” የተባለላቸው ገበየሁ(በአካባቢው አጠራር ጎራው ገበየሁ)፤ አድዋ ሥላሴ ተቀብረው ከቆዩ በኋላ አፅማቸው ወደ አምባላጌ ጊዮርጊስ ተወሰደ፡፡ በቃል ኪዳናቸው መሠረት ከሰባት ዓመት በኋላም አፅሙ በትውልድ አካባቢያቸው በአንጎለላ ኪዳነ ምህረት ቤተ ክርስቲያን አረፈ፡፡

ከአድዋ ድል በኋላ በጃንሜዳ የጦር አበጋዞች በፈረስ ሲያልፉ የፊታውራሪ ገበየሁ ፈረስ ብቻውን ከፊት ሲያልፍ ያዩት አፄ ምኒልክ ተንሰቅስቀው እንዳለቀሱም ይነገራል፡፡ ፊታዉራሪ ገበየሁ ነፍሱን ሰጥቶ ሀገሩን በታላቅ ተጋድሎ ያከበራት ጀግና ነዉ።ይህ ጀግና የሰራዉን ገድል ያክል አልተዘመረለትም በስሙም የተሰየመ ቤተ መዘክር እንኳን የለም የታሪክ ተወቃሽ እንዳንሆን ያስከበሩንን ጀግኖቻችንን እናክብር። የገበየሁ እንጉርጉሮ የሚለውን መነባንብ ለማድመጥ ይሄንን ሊንክ ይጫኑና ያድምጡ https://youtu.be/Qt5Q-rBh0Rg

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር