የሕዝብና የቤት ቆጠራ አሁን ለምን?

የሕዝብ ቆጠራ ለሚዛናዊ የሀብት ሥርጭትና ክፍፍል ሚዛን ለጠበቀ የተፋጠነ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ዕድገቱን በታቀደና በተቀናጄ መንገድ ለመምራት እጅግ አስፈላጊ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም:: የሕዝብ ቆጠራው ለተፈላጊው ግልጋሎት የሚውለው ግን ቆጠራውን የሚመራውና የሚቆጣጠረው መንግሥታዊ ተቁዋም በምላተ ሕዝቡ ታማኒና ቅቡል ሲሆን; ፖለቲካው ከአካባቢያዊነት ከዘር; ከሃይማኖት እና ከጎሣ የፀዳ ሆኖ ውጤቱን ሁሉም አምኖ ሲቀበለው እንደሆነ ይታመናል:: እንደ አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ነገድና ጎሣዎች በሆኑ አገሮች ; በተለይም ለበርካታ ዓመታት ከአንድነትና አብሮነት በተቃራኒው ልዩነት ሆን ተብሎ በተራገበባት; የነገድ የፖለቲካ ድርጅቶች እንደ አሸን በፈሉባት ኢትዮጵያ; የሕዝብ ቆጠራው በትክክል ይካሄዳል ; ውጤቱንም አብዛኛው ሕዝብ ይቀበለዋል ለማለት ያስቸግራል:: በአሁኑ ጊዜ ቆጠራውን አስቸጋሪና ኢታማኒ የሚያደርገውም ለዘመናት በፀረ ኢትዮጵያና በፀረ ዐማራነት የተደራጁ የነገድ ድርጅቶች የፈለጉትን ለመሆን በመራጩ ሕዝብ ላይ የሚነዙት ፕሮፓጋንዳና የሚያሰራጩት መልዕክት የቆጠራው ውጤት እነርሱን ጠቅም ወደሆነ አቅጣጫ ሊመሩት የመቻላቸው ሁኔታ በግልጽ የሚታይ ስለሆነ ነው:: ዛሬ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የዘር ድርጅቶች ከመንግሥት አቻ የሚያደርጋቸው የመገናኛ ብዙኃን የገነቡ ከመሆኑም በላይ : ከማናቸው በላይ በብርሃን ፍጥነት በእያንዳንዱ መራጭ እጅ የሚገባው የማኅበራ ሚዲያ በቆጠራው ውጤት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል ነው የሚባል አይደለም:: የአገራችን ፖለቲካ የተቃኘው አንዱን ደፍቆ የራስን የበላይነት በማንገሥና ሌሎችን በማግለል ላይ ያነጣጠረ ከመሆኑም በላይ ; አጠቃላይ ቅኝቱ

የመሬትና የሌሎች የተፈጥሮ ኃብቶችን ሽሚያና ነጠቃ ላይ ያተኮረ ስለሆነ ; የሕዝብ ቆጠራው ለታለመለት መልካም ተግባር ከመዋል ይልቅ ለብጥብጥና መሰል ተፈላጊ ላልሆኑ ድጊቶች እንዳያጋልጠን ብርቱ ጥንቃቄ ሊወሰድበት ይገባል:: ለዚህ አባባላችን መነሻ የሆነንም ባለፉት 27 ዓመታት በዐማራው ነገድ ላይ የተፈጸመው የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል ; መፈናቀል ; መሳደድና መዋረድ ዓለም የመሠከረለት በመሆኑ ነው:: ይህም ብቻ አይደለም :: በሶማሊና በኦሮሞ ነገዶች መካከል የታየው መፈናቀልና መሳደድ በወላይታና በሲዳማ ; በቀቤና እና በጉራጌ ነገዶች መካከል የተፈጸመው አሰቃቂ ዕልቂት ; በጠለምት ;ራያ ;ወልቃይት ;ጠገዴ ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ የዘርና የማነት ጥቃት ሥጋቻችን መሬት የያዘ መሆኑ ማሳያችን ነው::