ዐቢይ አሕመድ እንዴትና ለምን ተመረጡ? ድርሰቱ ሲተነተን 

ዐቢይ አሕመድ እንዴትና ለምን ተመረጡ? ድርሰቱ  ሲተነተን 

ሸንቁጥ አየለ

የድርሰቱ ሴራ ሲተነተን :- አቢይን በመምረጥ ህዉሃት ለሶስተኛ ጊዜ ጊዜአዊ ባለ ድል እንዴ ሆነች?

አምሳሉ ገብርኪዳን ዓርጋው

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ እንዴትና ለምን ተመረጡ???

ወያኔ/ኢሕአዴግ ትወናውን እንዴት ችለውበታል እባካችሁ! ሕዝቡን እኮ በጥፍሩ አቁመውት ሰነበቱ! ማን የቀረ አለ? በተለይ ደግሞ እነማን ገረሙኝ መሰላቹህ አቶ ኃይለማርያም መልቀቂያ የጠየቁት በገዛ ፈቃዳቸው ሳይሆን እንዲጠይቁ ተደርገው እንደሆነ የሚያውቁ ወይም የሚያምኑ ሰዎች ይሄንን የሰሞኑን የወያኔ/ኢሕአዴግን የሥራ አስፈጻሚውንና የምክር ቤቱን ሐሰተኛ ሽኩቻ እውነት አድርገው መቀበላቸው ወይም ማሰባቸው ነው በጣም የገረመኝ ነገር፡፡

አባዱላ ገመዳና በረከት ስምዖን ምን ብለው ምክንያት ሰጥተው ሥራ ለቀቅን በማለት ለአባዱላ ያሰቡት ነገር ሲከሽፍባቸው፣ በበረከት ያሰቡትን የፖለቲካ ትርፍ ካገኙ በኋላ ወር እንኳ ባልሞላ ጊዜ ቀደም ሲል ለመልቀቃቸው የሰጡትን ምክንያት በሚቃረን መልኩ እንደገና ደግሞ ምን ብለው እንደተመለሱ ላየ ሰው የእነኝህን ሰዎች ሥራ ሁሉ የሚያምን ቢኖር ቂል ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል???

ለዚህ ለጠቅላይ ሚንስትር (ዋና ሹም) ምርጫ አቶ ደመቀ ራሱን እንዲያገል ተደርጎ ዶ/ር ዐቢይ፣ ዶ/ር ደብረጽዮን፣ አቶ ሽፈራው ለፉክክር በቀረቡበት ምርጫ ተገኘ የተባለውን ብአዴን 45ቱም ድምፅ፣ ኦሕዴድ 45ቱም ድምፅ፣ ደኢሕዴን 18 ድምፅ ለዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፡፡ ሕወሓት 32 ድምፅ፣ ደኢሕዴን 27 ድምፅ ለአቶ ሽፈራው፡፡ ሕወሓት 2 ድምፅ ለደብረጽዮን 8 ድምፅ ተዐቅቦ 3 ድምፅ ያልተገኙ የሚለውን ውጤት ዓይታቹህት እንደሆነ በፍጹም በፍጹም ያ ሲወራ ሲናፈስ የነበረው ሽኩቻ እዚያ ውስጥ እንደነበረ የሚያሳይ አይደለም፡፡

ይሄንን እንዳንል ወይም ማስመሰሉን እንድናምን ለማድረግ ይመስላል ተፎካካሪ ሆኖ ቀርቦ ከተወዳደረና 2 ድምፅ አገኘ ከተባለ በኋላ ዶ/ር ደብረጽዮን አይ እኔ እጩ መሆኔን ተቃውሜ ነበረ፣ አትምረጡኝ ብየ ነበረ በማለት ለዛነው ከፍ ያለ ድምፅ ያላገኘሁት ዓይነት ንግግር እያናፈሰ ይገኛል፡፡ ካልፈለገ ራሱን ከፉክክሩ ያገላል እንጅ እየተወዳደሩ አትምረጡኝ ብሎ ነገር አለ እንዴ???

ሲናፈሱ ከነበሩ ወሬዎች አኳያ የምርጫውን ውጤት መተንተኑ ብቻውን አውሎ ያሳድራል፡፡ ትወና እንደሆነ በላያችን ላይ ሲሠራብን የሰነበተው የሚጠቁሟቹህን አንድ ሁለት ነገር ብቻ ላንሣ፦

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማጽደቅ በተጠራው “የሕዝብ ተወካዮች” ስብሰባ አስቀድሞ አንድነት፣ ጥምረት፣ ወዳጅነት መሥርተው ወያኔን አንበርክከውታል ምንትስ ቅብርጥስ ሲባልላቸው የነበሩት ኦሕዴድና ብአዴን ከዚያ ቅጽበት በፊት ይሄ መሠረቱት የተባለው ፀረ ሕወሓት ጥምረት መፍረሱን የሚጠቁም አንዳች ነገር ሳናይ አዋጁን ውድቅ በማድረጉ ወሳኝ ጉዳይ ላይ ተለያይተው ዓየንና አላቸው የተባለው ጥምረት መፍረሱን ኦሕዴድ በብአዴን መከዳቱን እንድናስብ የሚያደርግ ተግባር ተፈጽሞ ዓየን፡፡

በተለይ በድምፅ አሰጣጡ ሒደት ላይ ተያይዘው የወጡ ያየናቸው ስሜት (emotion) ገላጭ ፎቶዎች (ምስለ አካሎች) የኦሕዴድ አባላት አዋጁን በመቃወም የሰጡት ድምፅ የእውነት የሚያስመስሉ ነበሩ፡፡ እነኝህ ፎቶዎች ናቸው እኔንም ሸውደውኝ “ኦሕዴድ በይፋ በሕወሓት ላይ ፊቱን አዙሮ ለሕዝቡ ቆሟል!” የሚባለውን ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳምን አድርጎኝ የነበረው፡፡ እነሱ ለካ ደምበኛ የፊልም (የምትርኢት) ቀረፃ ላይ ነበሩ፡፡

በእርግጥ የዶ/ር ዐቢይ በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማጽደቅ በተጠራው ስብሰባ ላይ አለመገኘት ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ሆን ተብሎ የተደረገ እንደነበረ በጣም ግልጽ ነበረ፡፡ ምክንያቱም እሱ እዚያ ተገኝቶ የሚሰጠው የድጋፍ ወይም የተቃውሞ ድምፅ ብዙ ነገሮችን ግልጽ ያደርግ ስለነበረና ይሄ እንዲሆን ስላልተፈለገ ነበረ እንዳይገኝ የተደረገው፡፡

አዋጁን በመቃወም ድምፅ ቢሰጥ “ለኦሮሞ ሕዝብ የሚያስተላልፈው መልእክት ያልተፈለገ ይሆንና ዐመፁን ሊያባብስብን ይችላል!” ብለው ሰጉ፡፡ አዋጁን ደግፎ ድምፅ ቢሰጥ ደግሞ የሕዝብ ጠላት ተደርጎ ሊቆጠርና ነገር ሊበላሽ ሆነ፡፡ ስለዚህ ባይገኝ ይሻላል ተብሎ እንዳይገኝ ተደረገ፡፡ የድምፅ አሰጣጡም ባያቹህት መልኩ የኦሮሞ ሕዝብ ተወካዮቹ ናቸው በሚባሉት ተስፋ እንዳይቆርጥ ይልቁንም ተቆርቋሪዎቹ አለኝታዎቹ እንደሆኑ ሊያስብ በሚችልበት መልኩ የታየው ውጤት እንዲመዘገብ ተደረገና በዚያ መልኩ ተቋጨ፡፡

ያኔ በወሳኝ ጉዳይ ላይ ኦሕዴድን ከድቶ አዋረደው የተባለው ብአዴን ዛሬ ደግሞ በወሳኝ ጉዳይ ላይ ሕወሓትን በመቃረን በሙሉ ድምፅ የኦሕዴድ ወነኛ አጋር ሆኖላቹህ ብቅ አለ፡፡ ይሄንን ነገር ተምኑታላቹህ??? እውነት ይመስላቹሀል ወይስ ትወና??? እሽ ሌላው ሁሉ ይቅርና ግን ቢያንስ እንኳ ትግሬ የብአዴን አባላትና ለሕወሓት ፍጹም በሆነ ታማኝነት አገልጋይነታቸው የሚታወቁት የብአዴን አባላት ሕወሓትን ተቃርነው ከኦሕዴድ ጋር በመሰለፍ የብአዴን ድምፅ ሙሉ ለሙሉ ለዶ/ር ዐቢይ እንዲሆን ያደርጉ ነበረ ወይ??? ፈጽሞ የማይሆን የማይመስል ነገር ነው፡፡

ሌላው ደግሞ አቶ ደመቀ መኮንን ከምርጫው ራሱን ማግለሉ ነው፡፡ ይሄም የተደረገበት ምክንያት እንዲመረጥ የተፈለገው ዶ/ር ዐቢይ ስለሆነና አቶ ደመቀ ተፎካካሪ ሆኖ በቀረበበት ሁኔታ ለአቶ ዐቢይ የሚሰጡ ድምፆች ያልተፈለገ ትርጉም የሚሰጣቸው ሆኖ በመገኘቱ ነው አቶ ደመቀ እራሱን እንዲያገል የተደረገው፡፡

ለምሳሌ ሕወሓት ምንም እንኳ አቶ ደመቀ ፍጹም የሕወሓት ታማኝ ናቸው ከሚባሉት የብአዴን አባላት አንዱ ቢሆኑም ሕወሓት ድምፁን ለአቶ ደመቀ ስለማይሰጥ ይህ ጉዳይ ወያኔን በአማራ ሕዝብና በታችኛው የብአዴን አባላት ዘንድ ወያኔን ትዝብት ላይ እንደሚጥለው ስለታወቀ ነው አቶ ደመቀ እራሱን እንዲያገል የተደረገው፡፡ እንጅ አቶ ደመቀ እራሱን ለማግለሉ ብአዴን ወይም ደግሞ እራሱ አቶ ደመቀ አንድም የሰጠው አሳማኝ ምክንያት የለም፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን ምክትል ጠ/ሚ እንደመሆናቸው በሕጉ መሠረት አቶ ኃይለማርያም ወደ ጠቅላይ ሚንስትርነቱ በመጡበት አግባብ አቶ ደመቀ ተረክበው ቀሪ የአቶ ኃይለማርያምን የሥልጣን ዘመን ማጠናቀቅ ሲኖርባቸው ለምን ይሄ ቀርቶ አዲስ ጠ/ሚ እንዲመረጥ እንደተደረገ ምንም የተሰጠ መግለጫም የለም፡፡

በእነኝህ ምክንያቶች ሽኩቻና ዱላ ቀረሽ ውዝግብ የተሞላ ነው የተባለው የጠ/ሚ ምርጫ ትወና እንጅ እንደተባለው ኦሕዴድና ብአዴን በሕወሓት ላይ ያበሩበት ያደሙበትና ያሸነፉበት ምርጫ አይደለም፡፡

“ማን ማንን አወዳድረን ምን ዓይነት ቁጥር ብናወጣ ሊታመንልንና ኦሕዴድና ብአዴንም በሕወሓት ላይ እንዳመፁ፣ እንደተነሡ፣ እንዳበሩ በማስመሰል የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ ኦሕዴድንና ብአዴንን አለኝታ እንደሆኑት እንዲያምን፣ በነሱ ላይ ተስፋ እንዲጥል በማድረግ ፖለቲካዊ ጥቅማችንን ሊያስጠብቅልን ይችላል?” እያሉ ነው በር ዘግተው ሲዶሉቱብን የሰነበቱት፡፡

እነኝህ ሁለት ስብሰባዎቹ ሽኩቻና ውጥረት የነበረባቸውና ኦሕዴድና ብአዴንን ጀግኖች ለማስመሰልም ትናንት 20,7,2010ዓ.ም. የኢሕአዴግ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ለብዙኃን መገናኛ በሰጡት መግለጫ እንደገለፁት ከሁለት ወራት በፊት የኢሕአዴግ የሥራ አስፈጻሚ የ17ቱ ቀን ግምገማ ላይ “ነበረብን!” ነገር ግን በመግለጫ ሳይቀር “ፈተነዋል!” ያሉት ችግር ማለትም የእርስ በርስ መጠራጠር፣ መርሕ አልባ ግንኙነትና ጉድኝት፣ ሕዝበኝነትና ከኢሕአዴግ የርዕዮተዓለም መስመር የማፈንገጥ ሁኔታዎች አሁንም ጎልቶ እንደታየ ገልጸዋል፡፡

የሚገርመው ነገር ግን ይወሩ የነበሩት ሽኩቻዎች እውነት እንደሆኑና እንዳልሆኑ እንዲያረጋግጡ አቶ ሽፈራው በጋዜጠኞች (ዘጋቢዎች) ሲጠየቁ ሲወራ የነበረው ሁሉ ሐሰትና ጭራሽም እሳቸው ከሚያውቁት የኢሕአዴግ ስብሰባ ሁሉ ይሄኛው ፍጹፍ ሰላማዊውና ዲሞክራሲያዊው (መስፍነ ሕዝባዊው) እንደሆነ በመናገር ከላይ ሽኩቻና ውዝግብ የነበረ ለማስመሰል የእርስበርስ መጠራጠር፣ መርሕ አልባ ግንኙነትና ጉድኝት ከመስመር ማፈንገጥ… ጎልቶ ታይቷል ሲሉ የተናገሩትን የራሳቸውን ቃል እዚያው ላይ መልሰው ተቃርነውታል፡፡

ለመሆኑ ዶ/ር ዐቢይ እንዲመረጥ የተፈለገው ለምንድን ነው?፦

እንደምታውቁት ሕዝባዊው ዐመፅ ያየለባቸው አካባቢዎች የኦሮሞና የአማራ አካበቢዎች ናቸው፡፡ ወያኔ “ቀደም ሲል ጀምሮ በተሠራው ጠንካራ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ዶ/ር ዐቢይ ወይም የለማ ቡድን በኦሮሞም ሆነ በአማራ ሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን፣ ተቀባይነትና ታማኝነትን እንዲያገኙ አድርጌያለሁ!” ብሎ ስለሚያስብ በመጭ ጊዜያት ዶ/ር ዐቢይ ከጓዶቻቸው ጋር በሚሠሩት የፕሮፓጋንዳ (የልፈፋ) ሥራ ሕዝቡን በማጃጃል “በዋናነት የኦሮሞና የአማራ ሕዝብ እየተሳተፉበት ያሉበትን ሕዝባዊ ዐመፅ ለማረጋጋት ብሎም ለማክሰም ያስችለኛል!” ብሎ በጽኑ ስለሚያምንና በዚህ መንገድ ሕዝባዊ ትግሉን ለማክሸፍ ብሎም አዳፍኖ ለማስቀረት አስቦ ነው ወያኔ ዶ/ር ዐቢይን እንዲመረጥ ያደረገው፡፡

በዚህም መሠረት እንግዲህ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወገባቸውን አስረው ስሜትን በሚያሰክር መልኩ ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን፣ ወንድማማችነት እንደጉድ ሲሰብኩት የምታዩ ይሆናል፡፡ ከስር ከስር ደግሞ ካድሬነታቸው (ወስዋሽነታቸው) በግልጽ በማይታወቁና ገለልተኛ መስለው በሚታዩ ካድሬዎች (ወስዋሾች) እና አድርባይ ሆዳሞች በየመሥሪያቤቱ፣ በየ ብዙኃን መገናኛው፣ በየ የትምህርት ተቋማቱ፣ በየ የእምነት ተቋማቱ፣ በየ የግል ሥራው ወዘተረፈ. የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ስሜት ቀስቃሽ ስብከቶች በየቦታው እንዲራገቡ እየተደረገ ሕዝቡን በእነኝህ ባዶና አስመሳይ ስብከቶች የሚያምፅበት ምንም ምክንያት እንደሌለው እንዲሰማው በማድረግ ሕዝባዊውን ትግል ለማዳፈን በሰፊው ጥረቱና ዘመቻው ሲጧጧፍ የምታዩ ይሆናል፡፡

ጎን ለጎንም ኦሕዴድ ከቅጥረኛውና የአማራን ሕዝብ ጥቅም ለአንድ ደቂቃ እንኳ አስከብሮና ለማስከበርም ፈልጎና አስቦ ከማያውቀው ብአዴን ጋር በመሆን አገዛዙ የአማራ ክልል እያለ በሚጠራው የሀገሪቱ ክፍል በወንድማማችነት ሽፋን ኢፍትሐዊ የኦሮሞ ጥቅም እንዲከበር የሚያደርጉ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት በክልሉ የትምህርት ሥርዓት እንዲካተትና ለተማሪው እንዲሰጥ ይደረጋል፣ የኦሮሞ የባሕል ማዕከል በባሕር ዳር ከተማ ይገነባል ወዘተረፈ. በሌሎች ሀገር አቀፍ ጉዳዮች ላይም በወያኔ መልካም ፈቃድ የሚመጡ አንዳንድ ጥገናዊ ለውጦች የሚደረጉ ይሆናል፡፡

ከዚህ የተለየ ነገር የሚጠብቅ ሰው ካለ ሲበዛ የዋህ እንደሆነ ልነግረው እወዳለሉ፡፡ እንኳንና ከእናቱ እቅፍ ተቀብለው “ማንጁስ!” እያሉ ጡት አጥብተው አስተምረው ያሳደጉት ዐቢይ የደርግ መኮንን የነበረው አባዱላም እንኳ ለሕዝብ ሲያስብ ሕዝብን ሲያስቀድም ዓይተን አናውቅም፡፡ ከአምላክ በላይ ወያኔን ሲያመልክ ነው የታየው፡፡ ዐብይም ማስመሰሉን የተካነ መሆኑ ከአባዱላ ካልለየው በስተቀር ከአባዱላና ቢጤዎቹ ፈጽሞ የተለያየ አይደለም፡፡ ማንጁስ ዐቢይ የኋላ ታሪኩ ይሄንን እንዲያደርግ የሚፈቅድለት ዓይነት ሰው አይደለም፡፡ እናም በዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ተስፋ ያደረግሽ የዋህ ካለሽ እያንዳንድሽ ተስፋ ቁረጭ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ምናልባት ምናልባት የሚሆነው አይታወቅምና ዶ/ር ዐቢይና ቡድኑ ድንገት ተለውጠው የሚባለው ሽኩቻና መርሕ አልባ በመባል የተተቸው የኦሕዴድ ብአዴን ወዳጅነት፣ ጉድኝትና ጥምረት እውነት የሚሆን ከሆነ ደግሞ እንግዲህ ምን ይፈጠራል መሰላቹህ ሁለት መንግሥት የሚኖረን ይሆናል ማለት ነው፡፡

ይሄም ምን ማለት መሰላቹህ፦ ትዕዛዙ ተፈጸሚ የማይሆንለት ጉልበት አልባ ሕጋዊ ስም ያለው የዐቢይና የካቢኔው (የሸንጎው) መንግሥት አንዱ መንግሥት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ከሕግ በላይ በመሆን የፈለገውን ነገር የማድረግ የመፈጸም ጉልበት ያለው፣ ያዘዘውን መፈጸምና ማስፈጸም የሚችለው ደኅንነቱን፣ መከላከያውንና ኢኮኖሚውን (ምጣኔ ሀብቱን) የተቆጣጠረው የሕወሓት ቡድን ደግሞ ሌላኛው መንግሥት ነው፡፡

ይህ ሁኔታ በሚፈጥረው ክፍተት ሥርዓት አልበኝነት በሀገሪቱ የሚሰፍን ይሆናል፣ ዝርፊያ ይጧጧፋል፣ ተጠያቂነት የሚባል ነገር የሚጠፋ ይሆናል ወዘተረፈ፡፡ በመሆኑም በሁሉም መንገዶች የኢትዮጵያ ሕዝብ ተጠቃሚ የማይሆን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ብቸኛው፣ አዋጭውና አስተማማኙ መንገድ ወያኔ/ኢሕአዴግን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገላገል ብቻና ብቻ ነው፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
amsalugkidan@gmail.com