እንጻፍ ካልንማ!

እንጻፍ ካልንማ!

ከቤተ አማራዋ የውብዳር አክሊሉ

እስኪ ስለ ሸዋ ጨለፍ አርገን ለመፃፍ እንሞክር::  እንፃፍ ካልንማ ስለ ጥንቷ የሸዋ ከተማ ስለ ተራራማነቷ እና የተፈጥሮ መከላከያነቷ እንፅፋለን ስለ አስተዳደር ዝናዋ ስለ ኢትዬጵያ ዜጎች መሸሸጊያነቷ እና መጠለያነቷ እንፅፋለን ስለ አባዳኛው ሀገር አንጎለላ ስለ አቡኑ ከተማ እና የሣህለ ሥላሤ የትውልድ ስፍራ ሰላድንጋይ አፄ ዘረዓይቆብ ስለመሠረቷት እድሜ ጠገቧ ጥንታዊት ከተማ የቀድሞዋ ደብረ ዔባ ያሁኗ ደብረብርሀን እንፅፋለን ብርሀን ከሰማይ ስለወረደበት የደብረብርሀን ሥላሤ ግቢ እንፅፋለን በግንብ ስለተከበበችው ፫ በሮች ስላሏት የስምጥ ሸለቆ ከተማ የአብዱል ረሱል የእስልምና መቃብር ስፍራ ስላለባት አልዩአምባ እንፅፋለን የአፋር አርጎባ እና አማራ ህዝብ ባንድ ገበያ ውሎ ሰላም ግባ ተባብሎ ተመራርቆ ስለሚለያይባት ቆላማዋ አልዩ አምባ እንፃፍ ካልንማ ስለ ስለ አንኮበር መሬ ምንጃር ሸንኮራ መንዝ ይፋት እና ቡልጋ እንፅፋለን ።

ዓማራ ኢትዮጵያና አንድነትእንፃፍ ካልንማ ስለ እምነት ቦታዎቻችን እንፅፋለን ስለ ዋሻ ገብረኤል አቡነ ተክለሀይማኖት ስለ ደብረሊባኖስ ገዳም ስለ ምስካብ ቅዱሳን መድሀኒያለም ዋሻ እንፅፋለን ከአንድ ወጥ አለት ፈልፍሎ ዳግማዊ ላልይበላን ስለሠራው መጋቢ ተክለፃዲቅ ሸዋረጋ እንፅፋለን የቅዱሳን አፅም ማረፊያ ስለሆነው የአርባሃራ መድሀኒያለም ዋሻ እንፅፋለን ። እንፃፍ ካልንማ ስለ አራት ማዕዘኑ እድሜ ጠገቡ የጎዜ መስኪድ እንፅፋለን እንፃፍ ካልንማ ስለ ሸዋ የተፈጥሮ ሀብቶች እንፅፋለን ስለ ብርቅዬ አእዋፍን በውስጡ ስለያዘው ወፋሻ ደን ስለ ሰንሠለታማ ተራሮች ስለ ዠማ ወንዝ እንፅፋለን ገድሎ ሜዳ ላይ በክብር ጉብ ስላሉት የሙሽራ ድንጋዬች እንፅፋለን ከመንዝ ደጋማ ተራሮች እስከ ይፋት ቆላማ ሜዳዎች ያሉትን እንፅፋለን ከቀወት ኮረብታ እስከ ሚዳና መርሐቤቴ ዕልፍ አእላፍ ትዕይንቶችን እንፅፋለን እንፃፍ ካልንማ ስለ ሸዋ ጥበብ እንፅፋለን ስለ ኮከብ ቆጣሪዎቹ ዘመዶቼ እንፅፋለን ዩዲት ጉዲት ለ 40 አመት ግራኝ አህመድ ለ 15 አመት ሲገዙ ሸዋን ማለፍ አቅቷቸው ገትሮ ስላቆማቸእ አለም ስላልፈታው የሸዋ ጥበብ እንፅፋለን::

ከሸዋ ወጥተንም ወደ አገር ግንድ ጎንደር ሄደን ስለ ቤተልሔም እንፅፋለን ድጓ እና ፃመ ድጓ ሲንቆረቆር የሰማንውን እንፅፋለን ከፃፍንማ ስለ እነ ዋሸራ ደብረ ኤልያስ እና ዲማ ጊዬርጊስ ደብረወርቅ ላይ ቅኔ እና ጥበብ የሚዥጎደጎደውን እንፅፋለን ወደ ወሎ ተሻግረን ስለ ዋድላደላንታ ሊቃውንት የሚፈልቁበትን ጥበብ ስለሚታይበት እንፅፋለን ። እንፃፍ ካልንማ ስለ ታላቁ ደራሲ ዳኛቻው ወርቁ አገር ደብረሲና ስለ ታላቁ እና ዘመን የማይረሳው መሲህ ፕ/ር ዓስራት እንፅፋለን::  የሚኒሊክ መስኮት አጠገብ ተ�ቀምጠው የበግ ፀጉር እየጎነጎኑ ኮፍያ ሰርተው የሚሸጡት እና አካባቢውን ለእንግዳ ስለሚያስጎበኙት እረኞች ጣርማበር ላይ ቆሎ እና ጦስኝ ሸጠው ስለሚያድሩት ቆነጃጅት እንፅፋለን:: አናንተዬ የጦስኙ ሽታ አልናፈቃችሁም ??

ታላቁ የዠማ ወንዝ መሃል ለመሃል ተጉለትና መርሃቤቴ ማዶ ለማዶ
ታላቁ የዠማ ወንዝ መሃል ለመሃል ተጉለትና መርሃቤቴ ማዶ ለማዶ

እንፃፍ ካልንማ ስለ ደብተራው እና ገበሬው አባቴ አዝመራው ስለማይነጥፍበት አጎቴ እንፅፋለን ከፊቷ ፈገግታ ስለ ማይጠፋው እናቴ እንዝርት ከእጇ ስለማይለየው አክስቴ ደግነት እና ቅንነትን ስለተላበሱት ጎረቤቶቼ ስለ እንግዳ ተቀባይነታቸው እንፅፋለን በአዝመራ ወቅት ወገቧን አስራ ማጭዷን ይዛ ከወንድሜ ጎን ስለምትሠለፈው እህቴ እንፅፋለን የበግ ለምድ ከትከሻው ዋሽንት ከእጁ ስለማይለየው የበጎች እረኛው ወንድሜ እንፅፋለን ከብቶቻችንን አብልተን እና ውሀ አጠጥተን ከመስኩ ላይ አስተኝተን እኛም ከረጅሙ ዛፍ ጥላ ስር ቁጭ ብለን ከምቀኝነት አስመሳይነት እና ክፋት በፀዳ እውነተኛውን የፍቅር አቦጊዳ ስላስተማረኝ አብሮአደግ ጓደኛዬ እንፅፋለን።

አያችሁ እነዚህን ሲነኩ ውስጥ እግራን የገረፉኝ ያክል ይሰማኛል እንደ ጣት ቁስል ይጠዘጥ�ዘኛል እንቅልፍ ይነሳኛል አያችሁ ሲነኩብኝ ያመኛል !!! እጃችን እስኪዝል እስኪጣመም ብንፅፍ ታሪኩ ዓባይን በጭልፋ ነውና ንቅንቅ የለም ። “ጠሀፊዎች እንድትፅፉ ትጋበዛላችሁ የግድ ቦለቲካ ተንታኝ መሆን አይጠበቅባችሁም”