የኢትዮጵያ ምርጫ:- ወገኔ ሆይ! ኢትዮጵያ እንድትረጋጋና እንድታድግ ከፈለግህ ከአግላይና ጸረ ህዝብ አስተሳሰብ ራቅ!

የኢትዮጵያ የምርጫ አስፈጻሚ መስሪያ ቤት (National Election Board of Ethiopia) በሃገራችን ስድስተኛው ምርጫ ሰኔ ፩፬ ቀን ፳፳፫ እንደሚደርግ አሳዉቆአል። ለሃገራችን ኢትዮጵያ ደህንነት አንድነት ሰላምና እድገት ሳንሰለች የምንታገል ወገኖችና መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ይህንን የምርጫ ሂደትና ስርአት በከፍተኛ ትኩረት በመከታተል ላይ እንገኛለን። በሰላም በዲሞክራሲና በብሄር ብሄረሰብ ስም በኢትዮጵያዉያን በተለይ አማራውንና ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን በማግለል ከፍተኛ ደባና በደል ተፈጽሞአል። አሁንም ያንን በመሰለ ጸረ ህዝብ ጸረ አንድነታና ጸረ ዲሞክራሲ አስተሳሰባቸው ቆሽሸው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ላይ ጭቦ ለመስራት ያሰፈሰፉ የዉጭና የዉስጥ አፍራሾች መኖራቸውን በሚናገሩትና በሚጽፉት ሃሳብ ላይ ለመረዳት ይቻላል።

በአንድ በኩል “ኢትዮጵያ የሁላችን ነች:: ዲሞክራሲም የህዝብ ድምጽ ነው” እያልን በሌላ በኩል ሰፊዉን አማራና የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን አግልሎ ሃገራችንን ኢትዮጵያን በሰላም እናስተዳድራለን ማለት አርቆ አለማሰብ ብቻ ሳይሆን ሃላፊነት የጎድለው አስጠያቂ አሰራር ጭምር ነው። እዚህ ላይ ለአብነት ያህል አማራዉንና የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን አነሳሁ እንጂ በሌሎች ነገዶችም ሆነ እምነቶች ላይ ይሄ አስነዋሪ ድርጊት እንዳይፈጸም ፍትህ አዋቂዎች መሆን አለብን። መራጭ ወገኔ ሆይ! ሃገርህ እንድትረጋጋና እንድታድግ ልጆችህ በሰላም አድገው እንዲኖሩ ከፈለግህ ከአግላይና ጸረ ህዝብ አስተሳሰብ ራቅ። ኢትዮጵያ የህግ የበላይነት ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ሃገር እንዳትሆን ከ፲፻፱፻፱፩ አመተ ምህረት ጀምሮ ወያኔ የዘረጋቸው ጸረ አንድነትና ጸረ ሰላም ከፋፋይ ህጎች ደንቦችና ምልክቶች በሙሉ ከስራቸው ተነቅለው መጣል አለባቸው። በዚህ አጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ መጨነቅ ያለባቸው እንዴት ምርጫዉን ማሸነፍ እንዳለባቸው ሳይሆን እዴት ምርጫው ከሴራ ፖለቲካ የጸዳ መሆን እንዳለብትና ህዝብ ተቀይሞ ችግር እንዳይፈጠር ነው። ይህንን ካደረጉ ለአጭር ጊዜ ሳይሆን ለትዉልድ የሚተርፍ ታሪክ በመስራት ቆመውም ሆነ አልፈው ሲወደሱ ይኖራሉ።

ወያኔን እና ኦነግን እየከሰሱና እየወነጀሉ እነሱ የጻፉት በታኝና አግላይ መተዳደሪያ ደንብና ጸረ አንድነት ባለጌ የወያኔ ሰንደቅ አላማን ሰቅሎ ስለ ኢትዮጵያ ህዝብ እድገ ህብረት ፍትህ አንድነትና እኩልነት መለፈፍ ህዝቡን ከስርአቱ ከማራቅና ሌላ መቅሰፍት ከመቀስቀስ ዉጭ ምንም ፋይዳ አያመጣም። መሪ የሃገር ምስል/ተወካይ ስለሆነ እያንዳንዱ መራጭ ከመምረጡ በፊት የሚመርጠው ሰው በእዉቀትና በግብረገብ የታነጸ ብቻ ሳይሆን ግርማ ሞገስ ያለው ወይም ያላት መሆን አለባቸው። እዉቀትና ግርማ ሞገስ ያለው ኢትዮጵያን የሚመጥን መሪ ቢናገር ይደመጣል ዝምም ቢል ይከባራል። የወያኔ የኦነግና ሌሎች ኢትዮጵያ አደጋ ላይ እንድትወድቅ የሚፈልጉ ሃይሎች አማራና ኢትዮጵያን በሚመለከት ያላቸው አፍራሽ መንገድ አንድ ስለሆነ ወገን ሳትታለል ለመላው ኢትዮጵያና ህዝባችን ታማኝ የሆነ መሪ ከመንበሩ ላይ ለማስቅመጥ የሚቻልህን ሁሉ አድርግ። ያ ካልሆነ ስራችን ሁሉ ታጥቦ ጭቃ ነው!!

ድል ለተበዳዩና ሃገር ወዳዱ የኢትዮጵያ ህዝብ!
ሽንፈት የኢትዮጵያን መፍረስ ለሚመኙ ከሃዲዎች!