ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንከርስት፤ እንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ ጀግና

 

 

          ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንከርስት፤ እንግሊዛዊቷ የኢትዮጵያ ጀግና

 

                                                ኪዳኔ ዓለማየሁ

                                                ነሐሴ 10 ቀን 2001 ዓ/ም

  1. መግቢያ

ይህ አጭር ጽሑፍ (1) የሚያተኩረው፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፤ ወለተ ክርስቶስ ተብላ በተሰየመችው፤ የዓለም ስሟ ሲልቪያ ፓንከርስት በሆነው፤ ኢትዮጵያ በፋሺሽቶች በተወረረቺበት ጊዜ፤ ከዚያም በሁዋላ ሌሎች ቅኝ ገዢዎች ሊቀራመቷት በቋመጡበት ዘመን በሚያስደንቅ ጀግንነት 20 ዓመት ሙሉ በታገለችው፤ በተከበረች፤ ወይዘሮ የሕይወት ታሪክ ላይ ነው። የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማም፤ ሲልቪያ ፓንከርስት በዜግነት እንግሊዛዊት ብትሆንም በተጨባጭ ተግባሯ ግን የኢትዮጵያ ጀግና የነበረች ስለ መሆኑ ግንዛቤ እንዲዳብር ለማድረግና እስካሁን ተዘንግቶ የቆየው ልዩ መታሰቢያ እንዲቆምላት ለማሳሰብ ነው።

ሲልቪያ ፓንከርስት፤ እ.ኤ.አ በ1882 እንግሊዝ ሐገር ተወልዳ፤ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው፤ እ.ኤ.አ መስከረም 27 ቀን 1960 አዲስ አበባ ነበር። አስከሬኗ የተቀበረውም፤ ወለተ ክርስቶስ ተሰኝታ፤ እንደ ታላላቅ አርበኞች፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፤ ልዑል አልጋ ወራሽ አስፋ ወሰንና ሌሎች ክቡራን በተገኙበት በቅድስት ሥላሴ ቤተክርስቲያን ነበር። የ50ኛው ዓመት መታሰቢያዋ መስከረም 17 ቀን 2003 ዓ/ም ይከበራል ማለት ነው።

ከዚህ በታች በዝርዝር እንደሚቀርበው፤ ለኢትዮጵያ ነጻነት፤ ፋሺሽቶችና በጊዜው የነበረው የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን ለመቆራረስ የነበራችውን ዓላማ በመቃወም ጭምር፤ በሙሉ ቆራጥነት ባከናወነችው ከፍ ያለ ተጋድሎና ላስገኘችው አመርቂ ውጤት የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታዋ መሆኑ እንዲታወቅ ለማድረግ ነው። በተጨማሪም፤ ሲልቪያ ፓንከርስት ካከናወነቻቸው ከፍተኛ ተግባሮች ውስጥ፤ ልእልት ጸሐይ ሆስፒታልን ለማሠራት ያስፈለገው ገንዘብ እንዲዋጣ ማድረጓ፤ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት እንዲከበርና ፓርላማውም እንዲሻሻል ያደረገቺው ጥረት ሁሉ ይጠቀሳል። ይህን ለመሰለ ከፍ ያለ ጥረትና ተጋድሎ ተገቢውን ዋጋ የሚከፍል የኢትዮጵያ ሕዝብ ትውልድ ስላለ ለወይዘሮ ሲልቪያ ፓንከርስት መታሰቢያ በማቆም የጸረ-ፋሺሽትና ጸረ-ቅኝ አገዛዝ አቅዋሟና ለኢትዮጵያ ያበረከተችው መስዋእትነትና አርአያነት ታውቆና ተከብሮ እንዲኖር ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ያስፈልጋል። ሌላው የዚህ ጽሑፍ ትልቁ ዓላማ፤ በሲልቪያ ፓንከርስት ስም የሚሰየም፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍተኛ ጥቅም የሚያስገኝ የመታሰቢያ አገልግሎት ለማቁዋቁዋም ነው።

 Ethiopians and the rest of the world:
ወይዘሮ ሲልቪያ ፓንከርስ
  1. ሲልቪያና ኢትዮጵያ እንዴት ተገናኙ

ሲልቪያ፤ እድሜዋ 20 ዓመት ሲሆን፤ የሞዜይክ (mosaic) ስነ ጥበብ ለማጥናት እ.ኤ.አ በ1902 ቬኒስ ከተማ፤ ኢጣልያ፤ ሔዳ ስለ ነበር፤ ስለ ሐገሩ ያደረባት ልዩ ዝንባሌ ከዚያን ጊዜ ጀመረ። በወጣትነት እድሜዋ የነበራት ትኩረትና ስትታገልለት የነበረው ዓላማዋ የእንግሊዝ ሴቶች የመምረጥ መብት እንዲኖራቸው ለማድረግ ቢሆንም እ.ኤ.አ በ1919 ለጉብኝት ቦሎኛ ከተማ፤ ኢጣልያ፤ በነበረቺበት ጊዜ የሙሶሊኒ ወንበዴዎች (“ስኩዋድሪስቲ”) ተራውን ሕዝብ ሲደበድቡ ተመልክታ የትግልዋ ትኩረት ፋሺሽቶችን በመቃወም ላይ አነጣጠረ። (2) የጸረ-ፋሺሽት አቅዋሟ ተጠናክሮ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ያተኮረው ግን ኢጣልያ እ.ኤ.አ ታሕሣሥ 5 ቀን 1934 ወልወል፤ ኢትዮጵያ ላይ በፈጸመቺው ወረራ ምክንያት ነበር።

(1) ስለ ሲልቪያ ፓንከርስት ብዙ ተጽፉዋል። ለዚህ ጽሑፍ ዝግጅት መሠረት የሆነው ዋናው መጽሐፍ፤ በሪቻርድ ፓንከርስት የተጻፈው፤ “Sylvia Pankhurst, Counsel for Ethiopia”, (2003) የተሰኘው መጽሐፍ ነው።

(2) እንዲሁም፤ እንግሊዝ ሐገር በስደት ይኖር ከነበረው ኢጣልያዊ፤ ከሲልቪዮ ኮሪዮ ጋር ተፋቅራ ሪቻርድ ፓንከርስት ተወለደ።

የሙሶሊኒ ዓላማ፤ ኢትዮጵያን በሙሉ ለመውረር መሆኑን በመገንዘብ፤ ሲልቪያ ፓንከርስት፤ በጊዜው የነበረው የመንግሥቶች ማሕበር (League of Nations) ገብቶ በነበረው ቃልኪዳን መሠረት፤ ኢትዮጵያን ከኢጣልያ ወረራ እንዲያድን ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎች በመጻፍ እንዲሁም ሕዝባዊ ስብሰባዎች በማኪያሔድ ከፍ ያለ ጥረት አድርጋ ነበር። ነገር ግን፤ በተጻራሪው፤ በተለይ የእንግሊዝና የፈረንሳይ መንግሥቶች ከኢጣልያ ጋር በማበር

ኢትዮጵያን ለመቀራመት ያድሙ ስለ ነበር ወረራውን የሚያበረታታው እንጂ የሚያቆመው ሐይል አልተገኘም። እንዲያውም፤ ሲልቪያን እጅግ ያስገረማት ክስተት፤ እ.ኤ.አ በ1935 የእንግሊዝ መንግሥት ስለ ጉዳዩ እንዲያጠና በሰር ጆን ማፊ የተመራ ኮሚቲ አቋቁሞ የቀረበለት አስተያየት፤ ኢጣልያ ኢትዮጵያን ብትወር እንግሊዝን የሚጠቅማት እንጂ የሚጎዳት አለመሆኑን መጠቆሙ ነበር። ከመንግሥታቱ ማሕበር አንዱዋ በነበረቺው ኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውን ወረራ ድርጅቱ በነበረበት ግዴታ መሠረት ባለማስቆሙ፤ ጠንቁ፤ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት በተከሰተው እልቂት፤ ለአውሮፓ ለራስዋም እንዲተርፋት ሆኑዋል።

ሲልቪያም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ እለተ ሞቷ ድረስ ለኢትዮጵያ መብትና ነጻነት ጸንታ ታገለች።

  1. የፋሺሽቶች ግፍና የሲልቪያ ትግል

      3.1 የፋሺሽቶች ግፍ

እ.ኤ.አ በ1935-40 ኢጣልያ፤ ለአምስት አመቶች፤ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ በተፈጸመው ግፍ እጅግ ብዙ እልቂትና ውድመት ደርሶ ነበር። በጥይት፤ በቦምብ እንዲሁም በአውሮፕላኖች በተነሰነስ የመርዝ ጋዝ ጭምር አንድ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተጨፈጨፉ። ከነዚሁ ውስጥ፤ በጥቂት ሰዓቶች ውስጥ፤ አዲስ አበባ ከተማ ብቻ 30,000 ሕዝብ ተገደለ። አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካኤል እንዲሁም ሌሎች ብዙ አርበኞች ተሰዉ። 2000 ቤተክርስቲያኖችና 525,000 መኖሪያ ቤቶች ተደመሰሱ። በተጨማሪም፤ በመርዙ ዝናብ፤ 14 ሚሊዮን እንስሶችና ብዙ እጸዋት ወደሙ። ይህ ሁሉ አሰቃቂ ግፍ ሲከናወን ኢትዮጵያ፤ በአርበኞቹዋ አማካኝነት፤ ከፋሺሽቶቹ ጥቃት የመከላከል ትግልዋን አላቁዋረጠችም ነበር። አጼ ኃይለ ሥላሴም በስደት አውሮፓ ሔደው የዲፕሎማሲ ጥረታቸውን አጠናክረው ቀጥለው ስለ ነበር ከሲልቪያ ፓንከርስት ጋር የተገናኙት በዚያን ጊዜ ነበር። (3)

3.2 የሲልቪያ ፓንከርስት ትግል፤ ኢትዮጵያ በተወረረቺበት ዘመን (እ.ኤ.አ 1935-40)

ኢጣልያ ወልወል ላይ ኢትዮጵያን መውረር ከጀመረችበት ጊዜ፤ በመጨረሻም እ.ኤ.አ በ1941 ድል ተመትታ እስከ ተወገደቺበት ድረስ፤ ሲልቪያ፤ ሙሉ የሕይወቷ ዓላማና ተግባር ያደረገቺው ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት ነበረ ማለት ይቻላል። ያከናወነቻቸው ተግባሮች እጅግ ብዙ ቢሆኑም አንዳንዶቹ ከዚህ በታች ይጠቀሳሉ።

3.2.1 ኢጣልያ የወልወል ትንኮሳዋን አከናውና ኢትዮጵያን በሙሉ ለመውረር በምትንቀሳቀስበት ጊዜ፤ ኢትዮጵያም መከላከል እንድትችል፤ የመንግሥታት ማሕበር በጋራ ደሕንነት (collective security) ግዴታው መሠረት ኢትዮጵያን እንዲደግፍ ከመጠየቁዋም በላይ፤ ፋሺዝም ለዓለም ጠንቅ የሚያመጣ መሆኑን አስገንዝባ ነበር።

(ሀ) ብዙ የአቤቱታ ደብዳቤዎችዋን ለእንግሊዝና ለሌሎች መንግሥቶች እንዲሁም ለመገናኛ ብዙሐን (ለምሳሌ ቢ.ቢ.ሲ፤ ዴይሊ ኤክስፕሬስ፤ ማንቸስተር ጋርዲያን፤ ዴይሊ ቴሌግራፍ፤ ኒውስ ክሮኒክል፤ ወዘተ) በመጻፍ በኢትዮጵያ ላይ ስለ ተቃጣው የፋሺሽት ወረራ ሰፊ ግንዛቤ እንዲገኝና ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ከፍተኛ ጥረት አድርጋ ነበር። “የአውሮፓ ሕሊና ሞቱዋል ወይ፡ በእንግሊዝ ሐገር ታማኝ አስተሳስብ ጠፋ ወይ” እያለች ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ የአውሮፓን ሕዝቦች ስሜት ለመቀስቀስ ሞክራ ነበር።

 (3)በዚህ አጋጣሚ መገለጽ ያለበት ታሪካዊ ሐቅ፤ የፋሺሽቶች ጦር ወደ ኢትዮጵያ የዘመተው በቫቲካን ተባርኮ፤ በጊዜው በነበሩት፤ በፖፕ ፓየስ 11ኛ ድጋፍ የነበረ መሆኑን ነው። ለዚህ የጦር ወንጀል ትብብሯ፤ ቫቲካን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ እንድትጠይቅ ለማድረግ ዓለም አቀፍ አቤቱታ እየተፈረመ ነው። ለዝርዝር ግንዛቤ፤ “ዓለም አቀፍ ሕብረት ለፍትሕ፤ የኢትዮጵያ ጉዳይ” (Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause) የተሰኘው አካል በማኪያሔድ ላይ ስላለው ጥረት ድረ-ገጹን www.globalallianceforethiopia.orgን መመልከትና አቤቱታውንም መፈረም ይቻላል።                   (ለ) ኢትዮጵያ በባሪያ ንግድ ትጠቀማለች በማለት ፋሺሽቶች ያሰራጩ የነበረውን ሐሰት ፕሮፓጋንዳ በመቃወም አጋልጣለች።

(ሐ) ለአፍሪካም የዘለቄታ ጥቅም በማሰብ፤ በጸረ-ፋሺሽትና ጸረ-ኮሎኒያሊስት መርሆ ተሠማርተው የነበሩትን

እነጆሞ ኬንያታን (ኬንያ)፤ ኤሚ አሽዉድ ጋርቪ (ጃሜይካ) እንዲሁም የሙሶሊኒ ተቃዋሚ የነበሩ ጣልያናዊ ታጋዮችን ጭምር በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲተባበሩ አድርጋ ነበር።

(መ) በጊዜው በለንደን የኢትዮጵያ አምባሳደር ከነበሩት ከዶር. ወርቅነህ ማርቲን ጋር በመተባበር እንዲሁም ከእቴጌ መነን ጋር በመጻጻፍ በኢትዮጵያ በኩልም ስለ ነበረው ሁኔታ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖራት ታደርግ ነበር።

(ሠ) ለኢትዮጵያ ነጻነት ታከናውነው በነበረው ትግል እንዲረዱዋት ታዋቂ ከነበሩ የእንግሊዝ ምሑራን፤ ለምሳሌ ፕሮፌሰር ኤፍ.ኤል.ሉካስ፤ እንዲሁም እንደ ፊሊፕ ኖዌል ካሉ የፓርላማ አባሎች ጋር በቅርብ እየተመካከረች ትሠራ ነበር።

3.2.2 እ.ኤ.አ ከጥቅምት 1935 ጀምሮ ኢጣልያ የኢትዮጵያ ወረራዋን ስትቀጥል በምእራባውያን በኩል በተለይ የእንግሊዝና የፈረንሳይ መንግሥቶች የጦር መሣሪያ ለኢትዮጵያ እንዳይደርሳት ማእቀብ ሲጥሉ በሌላ በኩል ለኢጣልያ ነዳጅ ጭምር በማቀበል የግፍ ወረራው እንዲሳካላት አድርገው ነበር። በመጨረሻም ኢጣልያ አዲስ አበባንና አብዝኛዎቹን የኢትዮጵያ ከተሞች ስትቆጣጠር የእንግሊዝ መንግሥት የኮሎኒ ሥልጣኗን አውቆላት ነበር። (4) እ.ኤ.አ. ከ1935-40 ኢጣልያ ኢትዮጵያን ከሞላ ጎደል በተቆጣጠረችበት ዘመን፤ ሲልቪያ ፓንከርስት ያላቁዋረጠ እጅግ ከፍ ያለ የተቃውሞ ጥረት ታከናውን ነበር። ካከናወነቻቸውም አያሌ ተግባሮች ውስጥ ሊጠቀሱ የሚገባቸው፤

(ሀ) ለዓለም መንግሥታት ማሕበር፤ ለዊንስተን ቸርቺል፤ ለእንግሊዙ ሊቀጳጳስ፤ ለአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሩዝቬልትና ለሌሎችም ሐያላን የአቤቱታ ደብዳቤዎች መጻፏ፤

(ለ) እ.ኤ.አ በ1936 “አዲስ ዘመንና የኢትዮጵያ ዜና” የተሰኘ ጋዜጣ አቁዋቁማ ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ግንዛቤ እንዲዳብር ማድረጓ፤

(ሐ) እ.ኤ.አ በየካቲት 1937 አዲስ አበባ ብቻ 30,000 ሕዝብ ሲጨፈጨፍ የጦር ወንጀሉ በይፋ እንዲታወቅ ማድረጓ፤

(መ) አጼ ኃይለ ሥላሴ ለንደን ሲደርሱ በክብር ተቀብላ በየጊዜው ቃለመጠይቆች እያከናወነች፤ ባቋቋመችው ጋዜጣ አማካኝነትና በነበራት ሰፊ ሕዝባዊ ግንኙነት ንጉሠ ነገሥቱ ድጋፍ እንዲያገኙ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጓ፤

(ሠ) የዓለም መንግሥታት ማሕበር ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ በሚወያይበት ጊዜ ጄኔቫ ድረስ በመመላለስ መልእክተኞቹን በማነጋገር ኢትዮጵያ ለጊዜው በኢጣልያ ብትወረርም የማሕበሩ አባልነቷ አንደተጠበቀ እንዲቆይና ሌላ ድጋፍም እንድታገኝ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጓ፤

(ረ) ብዙ ምሑራንን፤ የሰብአዊ መብት ደጋፊዎችን፤ የፓርላማ አባሎችን፤ የቤተክርስቲያን መሪዎችን፤ ወዘተ. በማስተባበር፤ ብዙ አቤቱታዎችንና መግለጪያዎችን በሰፊው በማሰራጨትና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማከናወን የእንግሊዝ መንግሥትን ፖሊሲ ለማስቀየርና እንዲያውም ከአርበኞቻችን ጋር በመተባበር ኢጣልያኖችን ከኢትዮጵያ ለማስወገድ እጅግ ከፍ ያለ ጥረት ማድረጓ፤

(ሰ) ያከናወነቺው ባለብዙ ዘርፍ፤ ያላሰለስ የፖለቲካ ትግል፤ እንግሊዞች የኢትዮጵያን አርበኞች ጦር ደግፈው የኢጣልያ ግፈኛ ጦር ድል ተመትቶ እ.ኤ.አ በ1941 የኢትዮጵያ ነጻነት እንዲረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቷና፤

ሌሎችም ብዙ ምሥጉን ተግባሮቿ ሁልጊዜም የማይረሱ ናቸው።

(4) ፋሺሽት ኢጣልያ በኢትዮጵያ ላይ “ድል” አገኘች በማለት እውቅና በመስጠት የመጀመሪያዋ ሐገር ፖላንድ ነበረች።                                          

  1. የእንግሊዞች መቋመጥና የሲልቪያ ትግል

እ.ኤ.አ በ1941 ኢትዮጵያ ከፋሺሽት ኢጣልያ ነጻ ከወጣች በሁዋላ ቀጥሎ ያጋጠማት ከባድ ችግር የእንግሊዝ መንግሥት ኢትዮጵያን በቁጥጥሯ ስር (protectorate) ለማድረግ፤ ይህ ሳይቻል ደግሞ ኤርትራን፤ ኦጋዴንንና ቦረናን ለመቆጣጠር መወሰኗ ነበር። በዚህም ረገድ፤ ሲልቪያ ከአጼ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ትግል አከናውና የእንግሊዝ መንግሥት እኩይ ዓላማ እንዲከሽፍ እጅግ ጠቃሚ የነበረ አስተዋጽኦ አድርጋለች፤

(ሀ) በዚያን ዘመን፤ ሲልቪያ ለእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ለፓርላማው፤ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራቸውና ለሌሎችም በምትጽፋቸው አቤቱታዎችና በምታከናውናቸው የማጋለጥና የተቃውሞ ተግባሮቿ እንደ ኮሎኔል ጊልበርት ማክበረት የነበሩ ቁልፍ ባለሥልጣኖች ስለ ሲልቪያ የሚሰማቸውን ቁጣ ይገልጹ ነበር። ቢሆንም ለኢትዮጵያ ነጻነት በነበራት ጽኑ እምነት ማንም ሊያንበርክካት አልቻለም።

(ለ) አስመራ ድረስ በመሔድ፤ በጊዜው የነበሩት የእንግሊዝ መሪዎች ቢቃወሙዋትም፤ ኤርትራ ከእናት ሐገርዋ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል አስደናቂ ጥረት አድርጋ ነበር። እ.ኤ.አ በሕዳር 1941፤ የእንግሊዝ መንግሥት ኤርትራን ለኢትዮጵያ ማስረከብ ይገባታል ብላ አጠንክራ ጠይቃ ነበር።

(ሐ) እንግሊዞች፤ ኤርትራ ውስጥ በተለይ ምጽዋ የነበረውን ጠቃሚ ንብረት እያወላለቁ ሲያግዙ ሲልቪያ ተቃውሞዋን አሰምታ ነበር።

(መ) ኢጣልያኖች ከኢትዮጵያ ከተወገዱ በሁዋላ እንግሊዞች የኢትዮጵያን ግዛቶች ለመቀራመት የነበራቸው ዓላማ በነሲልቪያ ጠንካራ የ14 ዓመቶች ትግልና በኢትዮጵያ መንግሥትም አልበገር ባይነት ሳይሳካ በመቅረቱ በመጨረሻው እ.ኤ.አ በ1954 ከኢትዮጵያ አካባቢ ለቀው ወጡ።

  1. ሲልቪያ ያከናወነቻቸው ሌሎች ከፍተኛ ተግባሮች

5.1 ከፋሺሽቶችና ከኮሎኒያሊስቶች ጋር በመታገል ካስገኘችው ከፍተኛ ውጤት በተጨማሪ፤

(ሀ) የኢትዮጵያ ፓርላማ እንዲሻሻልና ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሐገሩ የፖለቲካና የማሕበራዊ ጉዳዮች ያላቸው ተሳትፎ እንዲጠናከር በማሳሰብ ለአጼ ኃይለ ሥላሴ በመጻፍ አመልክታ ነበር። 

(ለ) ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፤ ባሕልና ሥልጣኔ እየጻፈች ስለ ሐገራችን ሰፊ ግንዛቤ እንዲገኝ አድርጋለች።

(ሐ) እ.ኤ.አ በ1956፤ በ74 ዓመቷ ከልጇ፤ ከሪቻርድ ፓንከርስት ጋር ወደ ኢትዮጵያ መጥታ ኑሮዋን በመቀጠሏ፤ ከራሷ እጅግ አስደናቂ አገልግሎት በተጨማሪ ይኸው ልጇም የልጅ ልጇም ቤተሰቡ በሙሉ ለኢትዮጵያ ከፍተኛ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

(መ) ኢትዮጵያ ከመጣች በሁዋላም “Ethiopia Observer” የተሰኘ ጋዜጣ አቋቁማ ነበር። ቀደም ብላ ግን ኢትዮጵያ ነጻነቷን ካገኘች አገልግሎቱ አብቅቷል በማለት እንግሊዝ አገር አቋቁማው የነበረውን “New Times and Ethiopia News” የተሰኘውን ጋዜጣዋን እንዲቋረጥ አድርጋለች።

(ሠ) አዲስ አበባ የሚገኘው፤ እጅግ ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ ያለው የልእልት ጸሐይ ሆስፒታል የተሠራው በሲልቪያ ጥረት በተገኘው ገንዘብ ነበር።

(5) ሲልቪያ ሪፐብሊካን መሆኗንና ኢትዮጵያንም ትደግፍ የነበረው በጸረ-ፋሺሽትነት እምነቷ መሠረት መሆኑን ለአጼ ኃይለ ሥላሴ ግልጥ አድርጋ ነግራቸው ነበር።

(6) የልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል “ወደ የጦር ኃይሎች ሆስፒታልነት ከመለወጡ በፊት የሐኪሞችና የሌሎች የጤና ባለሙያዎች የመጀመሪያው ማሠልጠኛ ተቋም ስለ ነበር ለሐገሪቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን” ዶክተር ወንዱ ዓለማየሁ ገልጸዋል።

  1. መደምደሚያና ማሳሰቢያ

6.1 በመጀመሪያ ፋሺሽቶችን ከኢትዮጵያ ለማስወገድ በኋላም ከኮሎኒያሊስቶች ጠንቅ ለማዳን ሲልቪያ ፓንከርስት ለሐገራችን ላከናወነቺው ከፍተኛ የ20 ዓመቶች ተጋድሎ የኢትዮጵያ ጀግና ልትባል ይገባታል።

6.2 አጼ ኃይለ ሥላሴ ለሲልቪያ ፓንከርስት በጻፉት ደብዳቤ ለሷ የነበራቸውን ከፍ ያለ የአድናቆትና የውለታ ስሜት ገልጸውላት ነበር። አዲስ አበባም አንድ መንገድ በሲልቪያ ስም እንዲሰየም ተደርጎላት ነበር። ይህ ሁሉ ግን መልካም ቢሆንም ካበረከተችው አገልግሎት ጋር የሚመጣጠን ስላልሆነ ከዚህ የሚከተሉት ሀሳቦች ቀርበዋል፤

(ሀ) ለሲልቪያ ፓንከርስት ተገቢ የሆነ መታሰቢያ እንዲቋቋምላት ያስፈልጋል። ለታገለቺለት ለኢትዮጵያ ሕዝብም የሚጠቅም በሷ ስም የሚሰየም ትምሕርት ቤት፤ የምርምር ማእከል፤ የሕክምና አገልግሎት ወይም የመሳሰለ ተገቢ የሆነ መታሰቢያ ቢሆን ይመረጣል።

(ለ) ያሁኑም ሆነ የወደፊቱ ትውልድ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው፤ ስለ ሲልቪያ ፓንከርስት ተጋድሎ በአማርኛና በሌሎችም ዋና የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተጽፎ እንዲሠራጭ ማድረግ ያስፈልጋል።

(ሐ) ከላይ የተጠቀሱትን ሀሳቦች ለመተግበር፤ የኢትዮጵያ አርበኞች ማሕበር፤ ዩኒቨርሲቲዎች፤ ምሑራን፤ የጥናት ማእከሎች፤ የመገናኛ ብዙኃን፤ የኢትዮጵያ ሴቶች መብት ታጋይ ድርጅቶች፤ ሐሳቡን የሚደግፉ ግለሰቦችና ግላዊ ተቋሞች፤ እንዲሁም የሚመለከታቸው መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካሎች የየበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱና በአፈጻጸምም እንዲተባበሩ በትሕትና አሳስባለሁ።

6.3  በመስከረም 2003 ዓ/ም፤ የኢትዮጵያ ጀግናዋ፤ ወለተ ክርስቶስ፤ ሲልቪያ ፓንከርስት፤ ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየች 50 ዓመት ይሆናል። ቸሩ የኢትዮጵያ አምላክ ነፍሷን ይማርልን እንላለን። እስከዚያው፤ ተገቢ መታሰቢያ እንደሚቆምላት ወይም በመቋቋም ላይ እንደሚሆን ይታመናል። ለማንኛውም፤ ለሐገራችን ለኢትዮጵያ ለፈጸመችው ከፍተኛ አገልግሎት ዘለዓለማዊ ምሥጋና ይድረሳት። (7)

(7) በዚህ አጋጣሚም፤ ለልጇ ለዶክተር ሪቻርድ ፓንከርስትና ለቤተሰቡ በሙሉ፤ የእናታቸውን ፈለግ በመከተል፤ ለኢትዮጵያ ላበረከቱትና በማበርከት ላይ ላሉት ከፍተኛ አገልግሎት ልባዊ ምሥጋና ይድረሳቸው።